በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው ድርድር ከዚህ በኋላ በስልክ እንደሚደረግ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገለጹ

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው ድርድር ከዚህ በኋላ በስልክ እንደሚደረግ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተደራዳሪ ቡድናቸው ብጣሽ ወረቀት ላይ የሚሰፍር የድርድር ሃሳብን ለመመልከት የ18 ስዓታት በረራ በማድረግ ወደ ፓኪስታን አይጓዝም ብለዋል፡፡ ይልቅ ንግግሮች በስልክ መሆን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ቴህራን እና ዋሽንግተን በኤፕሪል 11 በፓኪስታኗ ኢስላማባድ ለንግግር ተቀምጠው የነበረ ቢሆንም፤አሁን ሁለተኛ ወሩን የያዘውን ጦርነት ግን ለማስቆም ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም ነበር፡፡

ትራምፕ ትላንት ዕረቡ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ንግግሮች ከዚህ በኋላ በስልክ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊጠናቀቅ ተቃርቦ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ሳምንት እንዲራዘሙ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርጫቸው የፊት ለፊት ንግግር መሆኑን ቢገልጹም፤አንድ ብጣሽ ወረቀት ለመመልከት ግን ለ18 ስዓታት ያህል መጓዝ አድካሚ ነው ብለዋል፡፡

በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ግጭቱን ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የቀጠሉ ቢሆንም እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ሊመጣ አልቻለም፡፡ ትራምፕ ከስምምነት መድረስ የሚቻለው ኢራን ሙሉ በሙሉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፍላጎቷን ስትተወው ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡//

ኢራን እስካሁን ባለው ውጊያ ሙሉ አቅሜን አልተጠቀምኩም አለች፡፡ ያለኝ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን አቅም ከዚህ በኋላ ለዓመታት እየተዋጋሁ እንድዘልቅ የሚያደርገኝ ነው ብላለች፡፡

አንድ የኢራን ህግ አውጪ ግለሰብ ከታስኒም የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ቴህራን በዚህ ስዓት ወደፊት ለዓመታት እንድትዋጋ የሚያስችላት በቂ የሆነ የሚሳኤልና የድሮን ክምችት አላት ብለዋል፡፡ እስካሁን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ባለው ጦርነት ውስጥ ቴህራን ሙሉ አቅሟን አልተጠቀመችም በማለት ተናግረዋል፡፡

አክለውም እስካሁን አዲሱን ካርዳችን አላሳየናቸውም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አንድ ኮማንደር የባህር ሃይላችን ከአሜሪካ ለሚሰነዘር ጥቃት አዲስ አቅም ይጠቀማል ብለዋል፡፡ ባለስልጣናቱ አዲስ ካርድ እና አዲስ አቅም ብለው ከመናገር ውጪ በዝርዝር ሃይላቸው ምን እንደሚጠቀም ያሉት ነገር የለም፡፡

ኮማንደሩ ማክሰኞ እለት በሚናብ ከተማ ህዝብ በተሰበሰበት ቦታ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ አብዮታዊ ዘቡ በአዲስ የዘመቻ ስልት ጥቃት እንደሚፈጽም ሲናገሩ መደመጣቸውን የተርኩ የዜና ምንጭ TRT ዘግቧል፡፡

አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት 21 ላይ የተቀናጀ ጥቃት በኢራን ከከፈቱ በኋላ፤ቴህራንም ለዚህ አጸፋ ነው ያለችውን ጥቃት አድርሳለች፡፡ በዚህ ጥቃቷም የአሜሪካ ጥቅም አለባቸው ባለቻቸው የቀጠናው ሀገራት ላይ በልዩነት ደግሞ በገልፍ ሀገራት ይህንን አድርጋለች፡፡

በኤፕሪል 8 በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ተደርሶ፤በ11 እና በ12 ደግሞ በፓኪስታን አማካኝነት ያልተሳከ ንግግር ተደርጎ ነበር፡፡

ከዚያም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሰረት የተኩስ አቁሙ መራዘሙን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ያሳለፈነው ሰኞ እለት ኢራን ጦርነቱን ለማጠናቀቅ ያቀረበችውን ሃሳብ እንዳልተቀበሉት ገልጸዋል፡፡

ቴህራን ያቀረበችውና ትራምፕ ውድቅ ያደረጉት ሀሳብ የሆርሙዝ ሰርጥ እንዲከፈት እና የኒውክሌር ጉዳይ ደግሞ በኋላ ንግግር እንዲደረግበት የሚል ነበር፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe