አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት አዲስ ጥቃት በኢራን ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ፡፡
ከሟቹዎ ውስጥ ስድስት ያህሉ ህጻናቶች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ ጥቃቱን ለመበቀል ኢራን በእስራኤል ላይ በወሰደችው እርምጃም ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አራት ያህሉ ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል፡፡
ዋሽንግተና እና ቴላቪቭ ዛሬ ሰኞ በኢራን ባደረሱት የጋራ ጥቃት 25 የሚደርሱ ኢራናዊያን መሞታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቴህራንም ለደረሰባት ለዚህ ከፍተኛ ጥቃት የሚሳኤል ናዳ በእስራኤል እና በገልፍ ሀገራት ላይ ማድረሷም ተሰምቷል፡፡ ኢራን በሰሜን እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች በሃይፋ መገደላቸው ተነግሯል፡፡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተጨማሪ ጉዳት መኖር አለመኖሩን በማጣራት ላይ መሆናቸውም ተገልጻል፡፡
ከገልፍ ሀገራት መካከል ደግሞ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ኩዌት ሚሳኤሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በአየር መከላከያ ስርዓታቸውም እያከሸፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት እንድታደርገው የሰጡት የጊዜ ገደብ ዛሬ ሌሎት ያበቃል፡፡ እስከዚያው ድረስ ኢራንን ወሽመጡን ካልከፈተችው ጦርነቱ ገና አሁን ይጀመራል የሚል ዛቻ ትራምፕ አሰምተዋል፡፡
ነገ ማክሰኞ ነገሮች ወደ መለሳለስ ካልተመለሱ የኢራን የሃይል እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ወደ አመድነት ይለወጣሉ ብለዋል፡፡ በዚህ መሃል ነው አደራዳሪ ሀገራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የ45 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ እየጠየቁ የሚገኙት፡፡
በርግጥ የሆርሙዝ ወሽመጥ የተፈጥሮ ባለቤት የሆነችው ሌላኛዋ ሀገር ኦማን ወሽመጡን ዳግም ለመክፈት በሚቻልበት ዙሪያ ከኢራን ጋር እየመከረች እንደሆነ በይፋ አስታውቃለች፡፡
ከዚህ ባለፈ ግብጽ፡ሩሲያ እና ሌሎችም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረጉ መሆናቸውን ቢገልጹም መሬት ላይ ያለውን የጦርነት እውነታ ግን እስካሁን አልለወጠውም፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ በኢራን ከ1ሺ900 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤በሊባኖስ፡በእስራኤል ቀላል የማይባል ውድመት ደርሷል፡፡
የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፤የባህረ ሰላጤው ሀገራትም በውጥረት ውስጥ እንዲያልፉ ተገደዋል፡፡//

