በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተን ግጭት ተከትሎ አንድ ተማሪ ሲገደል በርካታ ተማሪዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደረሰባቸው።
ስለክስተቱ ከዩኒቨርስቲው አመራር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአክሱም ከፍተኛ ሆስፒታል ሰራተኛ አንድ ተማሪ እንደሞተ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ጨምረውም በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውንም ባለሙያው ተናግረዋል።
ትናንት ከክስተቱ ቀደም ባለፈው ሳምንት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን ድርጊት በመቃወም ተማሪዎች በከተማው ውስጥ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ፖሊስም ሰልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙም ተነግሯል።
ግርግሩና ጥቃቱ ተከስቶ ተማሪው የተገደለውና በሌሎች ላይ ጉዳት የደረሰው ከዚህ በኋላ መሆኑን የአይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ተማሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ላይ መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በተማሪው ሞት ጥልቅ ሐዘን በክልሉ ሕዝብና በመንግሥት ስም ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ድርጊቱን አስነዋሪ ሲል የገለጸው ሲሆን፤ ግድያውን ጥብቆው እንደሚኮንነውና ፈጻሚዎቹን ወደ ህግ ለማቅረብ እየተደረገ ላለው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
Source: BBC Amharic

