አስከፊው የሴቶች ግርዛት በአውሮጳም እየተስፋፋ ነው ሲል ቴር ደ ፋም የተባለው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት አሳሰበ።በድርጅቱ ግምት በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ብቻ የተገረዙ ከ100 ሺህ በላይ ልጃገረዶች ይገኛሉ።ሌሎች ከ17 ሺህ በላይ እንደሆኑ የሚገመቱ ልጃገረዶች ደግሞ ለግርዛት የተጋለጡ ናቸው ብሏል ድርጅቱ።
በፕላን ኢንተርናሽናል የህጻናት መብቶች አዋቂ ኤዴል ኦትየኖ ዖኮት ከዚህ በመነሳት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ስለ ሴቶች ግርዛት አደገኛነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ድርጅት DPA ዘግቧል።በመላ ጀርመን የግርዛት ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ የምክር አገልግሎት መስጫዎች ቢኖሩም ለህክምና ባለሞያዎች ለአዋላጆች፣ለህጻናት ሐኪሞችና ለማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ግንዛቤ ማስጨበጥ ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሴቶች ግርዛት ጉዳይ በጤናና በማኅበራዊ ጉዳዮች ስርዓተ ትምሕርቶች ውስጥ እንዲካተቱ አሳስበዋል።ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ግብጽና ቡርኪናፋሶን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት የሴቶች ግርዛትን የመከላከል ዘመቻ ከሚያካሂዱ ድርጅቶች አንዱ ነው።

