በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ21 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ እንደሚያዙና 26 ሺህ ሰዎች ኤች አይ ቪን ጨምሮ ተያያዥ በሆኑ የጤና እክሎች እንደሚሞቱ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ከሁለት አመት በፊት በተከሰተው የኮንዶም እጥረት ምክንያት በአንዳንድ የክልል ከተሞች ምርቱ በውድ ዋጋ ሲሸጥ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ250 ሚሊዮን በላይ የኮንዶም አቅርቦት እና ስርጭት እንደሚያስፈልግ በኤም ኤስ አይ ሪፕሮዳክቲቭ ቾይዝ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው ስርጭት ከ50 በመቶ በታች እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የአቅርቦት እጥረቱ በተለያዩ ክልሎች የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እና እንዲስፋፋ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
ዶ/ር አበበ አክለውም፤ አቅርቦት እና ፍላጎት ባለመመጣጠኑ ምክንያት በክልሎች እና በሃገሪቱ የገጠር ክፍል በተጋነነ ዋጋ እንዲሸጥ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ በተለይም የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት ከፍተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎች እጥረቱ እና የዋጋ ውድነቱ እንደሚስተዋል አመላክተዋል፡፡
በዚህም ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በማህበራዊ ግብይት አማካኝነት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2022 እና በ2023 በተሠራው አገራዊ የኤች.አይ.ቪ ሥርጭት ግምታዊ የዳሰሳ ጥናት 8ሺ 257 ሰዎች በኤች.አይ.ቪ መያዛቸው መገለጹ ይታወቃል፡፡
(መናኸሪያ ሬዲዮ)

