በመላ ሀገሪቱ ለእንጀራ፡ለዳቦ እና ለተለያዩ የሸቀጥ እቃዎችን ለመያዝ የሚያገለግለውን ፊስታል ይዞ መገኘት ከ5ሺ ብር ቅጣት እስከ 5 ዓመት እስራት ያስቀጣል ተባለ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማንኛውም ሰው ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፌስታሎችን ይዞ መገኘት በገንዘብ እና በእስራት እንደሚያስቀጣ የሚደነግገውን አዋጅ አጽድቋል፡፡ አንዳንዶች ቀደም ባለው ጊዜ ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ውሳኔ ሲወስኑ የተከተሉትን ሂደት በማንሳት ውሳኔው በጥድፊያ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ተችተውታል፡፡ ኬኒያ በ2017 ፌስታል ጥቅም ላይ እንዳይውል ስትወስን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራቷንና በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ አምራቾችም ወደ ወረቀት ማምረቻው እንዲዘዋወሩ የሚረዳ ተግባራትን ማከናወኗን በማንሳት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ይህ አዋጅ በጸደቀበት ወቅት ዜጎች በማያውቁት ጉዳይ ለቅጣት የሚያጋልጣቸው ነው፤ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ አይደለም የሚል ትችት እንደቀረበበት ቢሰማም አዋጁ ግን ጸድቋል፡፡
የም/ቤቱ አባላት አንዲት የ10 ብር ዳቦ እና የ20 ብር ስኳር ገዝታ በፌስታል ወደ ቤቷ የምትገባን እናት 2ሺ እና 5ሺ ብር መጠየቅ ከባድ ነው ከየትስ አምጥተው ይከፍሉታል በሚል ጥያቄ ቢቀርብም፤በመንግስት በኩል ይህንን ከግምት አስገብተን ነው ቅጣቱን ያስቀመጥነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ አዋጁን በተመለከተ ነገ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል የተባለ ሲሆን አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

