ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ህክምና ማዕከላት ከሚያቀኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አብዛኛዎቹ የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለባቸው መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ቫይታሚን ዲ በስብ ከሚሟሙ የቫይታሚን አይነቶች አንዱ በተፈጥሮ በጥቂት ምግቦች የሚገኝ ነው፡፡እነዚህም እንደ አሳ፡የበሬ ጉበት፡የእንቁላል አስኳልና አይብን በመሳሰሉት የምግብ አይነቶች ሲሆን በጸሀይ ብርሃን ደግሞ ሰውነታችን በቂ ቫይታሚን ዲ እንዲያመርት ያደርጋል፡፡
ቫታሚን ዲ በደምና በአጥንት ውስጥ የካልሲየም ሚዛንን ለመጠበቅ፡የአጥንት ግንባታና ጥገናን ለመደገፍ ካልሲየምና ፎስፈረስ እንዲዋሃዱ የሚረዳ ነው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጽያ በርካታ ሰዎች ላይ የቫይታሚን ዲ እጥረት እየተስተዋለ መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ሚካኤል ዘወዱ ገልጸዋል፡፡
ባለሙያው ወደ ህክምና ተቋማት ከሚሄዱ ሰዎች ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት የቫይታሚን ዲ እጥረት እንደሚገኝባቸው ተናግረዋል፡፡የቫይታሚን ዲ እጥረት በነፍሰጡር ሴቶች ላይ የመታየት መጠኑ ከፍ ያለ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

