በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አገር በቀል የቴክኖሎጅ ኩባንያ ተመሰረተ

ኩባንያው በሶስት ዘርፎች ፤ በሶፍትዌር ማበልጸግ፣ በሳይበር ደኅንነት ምርቶችና ማማከር አገልግሎቶችና በቴሌኮም መሰረተ ልማት ምርትና አገልግሎት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሥራ መጀመሩ ተገልጿል።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በቴክኖሎጂና የንግድ ሥራ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች በ200 ሚሊዮን ብር ካፒታል “ኢቴክ አክስዮን ማህበር” የተሰኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ድርጅት ሆኖ ተመስርቷል። ኩባንያው መቀመጫውን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርጎ ነገር ግን ዓለማቀፋዊ ተደራሽነትን ይዞ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ድርጅት ነው ተብሏል።

የኢቴክ ምስረታ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የተከናወነ ሲሆን በአስራ አንድ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ለመስራት አቅዶ መነሳቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ይፋ ተደርጓል።

ኩባንያው በሶስት ዘርፎች ፤ በሶፍትዌር ማበልጸግ፣ በሳይበር ደኅንነት ምርቶችና ማማከር አገልግሎቶችና በቴሌኮም መሰረተ ልማት ምርትና አገልግሎት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሥራ መጀመሩ በወቅቱ ተገልጿል። ኢቴክ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ (Fin Tech) ላይም ለመሰማራት ዝግጅት መጨረሱ ተነግሯል።

በይፋዊ የምስረታ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ” የዚህ የመጀመሪያው የሀገራችን የቴክኖሎጂ ኩባንያ መመስረቱ ታሪካዊ ነው። የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ ማገዝ በሚያስፈልግበት ትክክለኛ ሰዓት የመጣ ትክክለኛ አክስዮን ማሕበር ነው” ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ኢቴክን የመሰሉ በርካታ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች እንዲመሰረቱና ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በሕግና የአሰራር ማእቀፎች የተደገፉ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚዘረጋና  በቅርበት አብሯቸው እንዲሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው “የኢቴክ አ.ማ. መመስረት ኤጄንሲያቸው የሚሰራውን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ የሚያግዝ ትልቅ አቅም ሆኖ የመጣ ነው” ብለዋል።  ዶር ሹመቴ አክለውም ከዓለማችን ምጣኔ ሀብት ከሀምሳ በመቶ በላይ የሚሆነውን ብቻቸውን የተቆጣጠሩት አሜሪካና ቻይና በዋናነት እየተጋጩ የሚገኘው በሳይበሩ ዓለም ምክንያት እንደሆነ ገልጸው አይቀሬ የሆነውና ለዓለማችን አምስተኛ ስጋት ሆኖ የተቀመጠውን የሳይበር ጦርነት ለመመከት በተለይ ከሀገራቸው በተለያዩ ወቅቶች ተሰደው የወጡ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ባሉበት ሀገር ሆነው ያካበቱትን እውቀት፣ ልምድና ክህሎት ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ማካፈል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በስነ ስርዓቱ ቀጥታ የዙም ውይይት የተሳተፉት በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ ክቡር አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ተመርቀው ለተሻለ ትምህርት ወደተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ሄደው በዚያው የቀሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሰበሰበው ኢቴክ አ.ማ. ወደፊት ሌሎችን ባለሙያዎችንም እንደሚስብ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢቴክ ልክ እንደዓለማችን ስመ ጥር የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን በተለያዩ የቴክኖሎጅ ዘርፎች ለማስጠራት ቆርጦ የተነሳ ኩባንያ መሆኑን የገለጹት የአክስዮን ማሕበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው ናቸው። ሰብሳቢው እንዳሉት ኢቴክ ለኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ችግር ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ይዞ የመጣ የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ብቻ ቤት ነው ብለዋል። የሀገርን ዳር ድንበር በውጭ ሀገር ወታደሮች ማስጠበቅ እንደማይቻለው ሁሉ የሀገራችንን የሳይበር ቅጥርም በራሳችን የአይሲቲ ባለሙያዎች ማስከበር አለብን ያሉት ኢንጅነር መላኩ ባደጉት ሀገራትና ማይክሮሶፍት፣ አማዞንና ጎግልን በመሰሉ ግዙፍ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ የሳይበርና የአይቲ ኤክስፐርቶች የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ደጀኖች ናቸው ብለዋል።

የኢቴክ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ ገ/መድሕን ደግሞ “ዛሬ የተገናኘነው በአንድ የአክስዮን ማሕበር ምስረታ ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደቴክኖሎጅ አብዮት ለመግባት ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች ከሀገር ውስጥና ከባሕር ማዶ መሰባሰብ የጀመሩበትን አዲስ ምእራፍ ለማብሰር በተዘጋጀ ሀገራዊ መድረክ ላይ ነው” ብለዋል። “ለዚህም መንግስት በውጭ ሀገራት የሚገኙ ባለሙያዎች በሀገራቸው ዕድገት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያመቻቸውን ሕግና አሰራር በመጠቀም በአሜሪካ፣ አውሮፓና ሌሎች 17 የውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ሀገራቸው ኢትዮጵያን ባላቸው ነገር ሁሉ ለማገልገል የነበራቸውን ቁጭት የሚወጡበት ዕድል ስላገኙ ከሙያቸውና እውቀታቸው ባሻገር በገንዘባቸውም ጭምር ሀገራቸውን ለመደገፍ በርካታ የኢቴክ አክሲዮኖችን በውጭ ምንዛሬ መግዛታቸውን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

ኢቴክ አ.ማ. የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት ማስጠበቅ፣ ኢትዮጵያዊ መተግበሪያዎችን መስራት፣ የቴሌኮም ዘርፍ ላይ መሰማራት፣ የአይቲ ድጋፍ መስጠትን ጨምሮ ከ10 በላይ የቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ጥናት በማድረግ ወደስራ የገባ ሲሆን በቅርቡ በጠየቀው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚኖረው የመስሪያ ቦታ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።

ኢቴክ ኢትዮጵያዊ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በማቅረብ እስከ 2030 ድረስ የዓለም ታዋቂ የቴክኖሎጂ ተቋም የመሆን ራዕይ ይዞ የተነሳ ሲሆን ግብረገብ የተላበሰ በኢትዮጵያውያን የሚመራ ሁሉን አካታች የቴክኖሎጂ ድርጅት ለመፍጠርም ግብ አስቀምጧል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe