በኢትዮጵያ የመጀመሪያው “የባሎች ትምህርት ቤት” ተከፈተ

* ትምህርት ቤቱ ለወንድ የቤተሰብ አባላት ስልጠና በመስጠት ላይ ነው ተብሏል
* ማሰልጠኛው በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥም ለ8 ሺህ ሰዎች ስልጠናዬን እሰጣለሁ ብሏል
በሲዳማ ክልል በህፃናት አድን ድርጅት ድጋፍ ባሎችን በልጆች አያያዝ፣ ምግብ ማብሰል ፣ንጽህና አጠባበቅ እና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ ትምህርት ቤት ተከፍቷል።
የህጻናት አድን ድርጅት ለአል ዐይን እንዳለው ወንዶች ቤተሰባቸውን በማስተዳደሩ ሂደት ሚናቸውን በሚገባ ተገንዝበው በልበ ሙሉነት እና በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ለወንድ የቤተሰብ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብሏል።
ድርጅቱ አክሎም በሲዳማ ክልል በሚተገበረው የአመራር ክህሎት እና የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ፕሮግራም ወጣት ሴቶችን በጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ስራዎች እንዲሰማሩና ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ብሎም በማህበረሰባቸው ውስጥ የለውጥ ወኪሎች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የተለያዩ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሷል።
ለሴቶች ከሚሰጡ ስልጠናዎች እና ድጋፎች በተጨማሪ በማእከላቱ ከ519 በላይ የሚሆኑ የወንድ አጋሮቻቸው እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ደግሞ በባሎች ትምህርት ቤት የስልጠና መርሃ ግብር እንዲካተቱ ተደርጓል ተብሏል።
በህጻናት አድን ድርጅት በህጻናት አድን ድርጅት የሀዋሣ አካባቢ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ካዬሣ “በእነዚህ ማእከላት በምግብ ማብሰል፣ በቤት ፅዳት እና በንጽህና አጠባበቅ፣ በልጆች እንክብካቤ እና ሌሎች የቤት ውስጥ ስራዎች ዙርያ ለወንድ የቤተሰብ አባላት (በቀዳሚነት ለባሎች) ስልጠና በመስጠት ላይ ነው” ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ ባሎች በስልጠናው ወቅት የቤት ውስጥ ስራዎችን እንዲለማመዱ በማድረግ ለአሰልጣኞቻቸው ስራዎቻቸውን እንዲያሳዩ የሚደረግ ሲሆን ስልጠናው በተግባራዊ ልምምድ የታገዘ እንዲሆን መደረጉም ተገልጿል።
በባሎች ስልጠና እንዲካተቱ የሚደረጉት ሁሉም ወንድ የቤተሰብ አባላት (ባል፣ አባትና ወንድም) ሲሆኑ በቀዳሚነት ለባሎች ሆኖ እንደ አማራጭ በክህሎት ማሳደግ ፕሮግራም ውስጥ የታቀፈቸው ሴት ሰልጣኝ ያላገባች ከሆነች ስልጠናው የሚሰጠው ለአባቷ/ወንድሟ እንዲሆን እናደርጋለን›› ብለዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ የባሎች ትምህርት ቤት በሚል ስያሜ ስልጠና መስጠት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በአብዛኛው የማህበረሰባችን ክፍል ዘንድ የቤት ውስጥ ስራ እና የልጅ እንክብካቤ የሴቶች ስራ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ እና በተግባርም የሚስተዋል በመሆኑ ነው።
የባሎች ትምህርት ቤት ስልጠናም ዋነኛ የትኩረት ነጥብም ይሄው ወንዶችን በቤተሰብ አስተዳደር ዙርያ ቀዳሚ ተዋናይ ማድረግ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በቀጣይ ሦስት አመታት በአመራርነት ክህሎት እና የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ፕሮግራም አማካኝነት በመደበኛው የሴቶች የአቅም ማጎልበት ስልጠና ተሳታፊ ከሚሆኑት ሴቶች በተጨማሪ የቤተስብ አጋሮቻቸውን እና ባሎቻቸውን ጨምሮ በሚሰጡ ስልጠናዎች የተጠቃሚዎችን ኣሃዝ ከስምንት ሺህ በላይ ለማድረስ አቅደናል‹‹ ሲሉ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe