አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ትግራይ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈተፅሟ ብለዋል፤
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ገብተው በቆዩባቸው ወቅት የፈፀሟቸው ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ወንጀሎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ሪፖርት ያቀረበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አዲስ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሁለቱ ተቋማት ላለፉት 15 ወራት ያካሄዱትን ምርመራ ውጤት ተከትሎ በአካባቢው ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ የአማራ ኃይሎች እና ባለስልጣናት በምዕራብ ትግራይ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ ከጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መጠነ ሰፊ ወንጀሎች ፈጽመዋል ብሏል ሪፖርቱ።
ሪፖርቱ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ምዕራብ ትግራይ የሚንቀሳቀሱት የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም ሚሊሻዎች “የዘር ማጽዳት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን ገልጿል።
የዛሬው ሪፖርት በጦርነቱ የመጀመሪያ ጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ጭምር የዳሰሰ ሲሆን የትግራይ ሚሊሻዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪ ሲቪሎች በ ማይካድራ ከተማ አካባቢው ነዋሪ በሆኑ እና ለቀን ስራ በመጡ የአማራ ተወላጆች ላይ “የጦር ወንጀሎችን” መፈጸማቸውን አስታውሷል።
በሌላ በኩል ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በአካባቢው ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ጠይቀዋል።
እንደ መብት ተሟጋቾቹ ከሆነ የሰላም አስከባሪ ኃይል በስፍራው መሰማራት፤ የሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ፣ የሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እና በትግራይ አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመድረስ ቁልፍ እርምጃ ይሆናል ብለዋል።
በአካባቢው ያለው ችግር ውስብስብ እና በቀላሉ የማይፈታ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በሁለቱም ወገን ያሉ ሲቪሎችን ሊከላከል ይችላል ብለዋል።

