በኢትዮ-ሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

“በኢትዮ-ሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ “በሁለቱ አገሮች መካካል ያለው የድንበር ውዝግብ በአሁኑ ወቅት ውጥረቱ ቀንሷል” ብለዋል።

ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉት ቀጠናው እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ኃይሎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሱዳን የተወሰኑ ልሂቃኖችም ከእነዚህ ኃይሎች ጋር መወገናቸውን ተናግረዋል።

“እነዚህ ኃይሎች በግልጽ የሚታወቁ ናቸው” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በትርምሱ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸምና ጥቅማቸውን ለማስከበር ያለሙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህ ኃይሎች ለሱዳን ህዝብም ሆነ ለቀጣናው ጠቃሚ አለመሆናቸውን መንግሥት በተለይ ለሱዳን ህዝብ መልዕክት እየተላለፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም እነዚህን ኃይሎች በሂደት የማጋለጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቅሰው፤ ችግሮቹን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝ መንግስት በትግራይ ክልል ባከናወነው የሕግ የማስከበር ዘመቻ ክልሉ እየተረጋጋ እንደሆነና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

ያም ሆኖ አሁንም አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ክልሉ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በሚዛናዊነት መመልከት እንዳልቻሉ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

ይህም እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ወገንተኝነታቸው ከማን ጋር እንደሆነ በቅጡ ስለሚያሳይ ሊታረም የሚገባው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የእስራኤል፣ የህንድ፣ የዱባይ፣ የቻይናና የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከታቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

“ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተም ሚኒስቴሩ ዜጎች በሚኖሩባቸው አገሮች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ ነው” ብለዋል።

በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ ያሉትን ዜጎች ወደ አገራቸው ለመመለስ በተደረጉ ጥረቶች በዚህ ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያና ከሊባኖስ ዜጎች ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ገልጸዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe