በኦሮሚያ የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበሩ እንዳሳሰበው ኢሰመኮ ገለጸ

በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበሩ እንደሚያሳስበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኢሰመኮ ይህንን ያለው ሙሐመድ ዴክሲሶ የተባለ ተማሪን የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ አለመሆኑ እንዳሳሰበው ባመለከተበት መግለጫ ነው።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት “በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ አፋጣኝ ትኩረትና እልባት ይሻል” ብለዋል።

ኮሚሽኑ ጨምሮም “በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል እስር ቤቶች የዋስትና መስፈርቶችን ያሟሉ ነገር ግን በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ” ጠይቋል።

ግለሰቡ በፖሊሶች በጥፊ እንደመቱት፣ በዱላ ሁለቱን እግሮቹን መደብደቡንና ጎኑ አካባቢም እንደተመታ ገልጾ፤ ኢሰመኮም በእግሮቹ ላይ መጠነኛ እብጠት እንደሚታይና የሚያነክስ መሆኑን መመልከቱን ገልጿል።

የጅማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16/2013 ዓ.ም ሙሐመድ ዴክሲሶ በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ የወሰነ ቢሆንም ተጠርጣሪው አስፈላጊውን የዋስትና መስፈርት ቢያሟላም እስከ የካቲት18 ቀን ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጿል።

ቢቢሲ የአስረኛው ጠበቃ የሆኑትን ኦብስናን ግርማ ዛሬ ሐሙስ [የካቲት 18/2013 ዓ.ም] ጠዋት በማናገር እንዳረጋገጠው ሙሐመድ ዴክሲሶ አሁንም እስር ላይ ነው።

“ግለሰቡ በፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቅ ከተወሰነና ለዋስትና አስፈላጊው ነገር ከተሟላ ወዲያወኑ ከእስር ሊለቀቅ ሲገባ፤ በእስር ላይ መቆየቱ የተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው ያለው” ኮሚሽኑ፤ እስረኛው በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቅ አሳስቧል።

በተጨማሪም እስረኛው በፖሊሶች ተፈጽሞብኛል ያለውን ድብደባ በተመለከተም ተገቢው ማጣራት ተደርጎ የድረጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ ጨምሮም ሙሐመድ ዴክሲሶ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት “ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሊነቀፍ ወይም ሊያስወቅስ ከሚችል በስተቀር፣ ከመነሻውም ለወንጀል ክስና አስር ምክንያት ሊሆን አይገባም ነበር” ብሏል።

የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም የፌደራልና የኦሮሚያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣንት በታደሙበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከተመራቂዎቹ አንዱ የነበረው ሙሐመድ ዴክሲሶ የድምጽ ማጉያ ተቀብሎ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲፈቱና አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን በማስመልከት መፈክሮችን ማሰማቱን ተከትሎ ነበር ለእስር የተዳረገው።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe