በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የኢትዮ ቴሌኮም ሴኪዩሪቲ ዲቪዥን ኃላፊ በነፃ ተለቀቁ

በመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ ያገኙት ከነበረው ገቢ ጋር ሲነፃፀር፣ የማይመጣጠንና ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ ይዘው በመገኘት በአክሲዮንና በዝምድና በማስመሰል በውክልና ስም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና በዓቃቤ ሕግ ሥራ ጣልቃ የመግባት ሙከራ በማድረግ ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት፣ የኢትዮ ቴሌኮም የሴኪዩሪቲ ዲቪዥን ኃላፊ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በብይን በነፃ ተሰናበቱ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸው ከጥር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ሆነው ክርክራቸውን ሲያደርጉ ቆይተው ከተመሠረቱባቸው ሦስት የወንጀል ክሶች በነፃ የተሰናበቱት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ሴኪዩሪቲ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮሎኔል ጉደታ ኦላና ናቸው፡፡

በኮሎኔል ጉደታ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ አቅርቦ የሰነድና የሰው ምስክር በማቅረብ ሲከራከር የከረመው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ በሦስቱም ክሶች ተከሳሹን ጥፋተኛ ሊያሰኝ ወይም እንደ ክሱ ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድም ሆነ የሰው ምስክር ሊያቀርብ አለመቻሉን፣ የችሎቱ ዳኞች በሙሉ ድምፅ በሰጡት ብይን ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ በመሠረተው የመጀመርያ ክስ ኮሎኔሉ ቤት ለመሥራት በማኅበር ተደራጅተው በ460 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ባለ አራት ፎቅ መኖሪያ አፓርታማ ላይ ባለድርሻ መሆናቸውን፣ በባለቤታቸው ስም ሱሉልታ ከተማ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤት መኖሩን፣ በባለቤታቸው ስም አውቶሞቢልና የ50 ሺሕ ብር አክሲዮን መኖሩን፣ በወንድማቸው ስም የ500 ሺሕ ብር አክሲዮን መገኘቱን ጨምሮ በተከሳሹ፣ በባለቤታቸውና በልጃቸው ስም በተለያዩ ባንኮች የተቀመጠና ሲንቀሳቀስ የነበረ በአጠቃላይ 759,808 ብር መኖሩን አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ባደረገው ምርመራ ኮሎኔል ጉደታ ትዳር የመሠረቱበትን ጊዜና የጋብቻ ሰርተፊኬት መኖሩን አረጋግጦ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ ሲመረምር፣ በሱሉልታ ተገኝቷል የተባለው 200 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተሠራው ቤት ከጋብቻ በፊት መሆኑን፣ የ50 ሺሕ ብር አክሲዮንም በተመሳሳይ ከጋብቻ በፊት የነበረና የግላቸው መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ በወንድማቸው ስም ተገኘ የተባለው የ500 ሺሕ ብር የአክሲዮን ድርሻም የሕግ ችሎታ ካላቸው ወንድማቸው በውክልና የወሰዱት በመሆኑ፣ የተከሳሹ ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ በዓቃቤ ሕግ አለመቅረቡን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አስታውቋል፡፡

ሌላው በባንክ በአጠቃላይ 759,808 ብር ተገኝቷል ስለተባለውም ብር ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ኮሎኔሉ ለ19 ዓመታት ሲያገኙት የነበረው ጠቅላላ ገቢ 3,008,792 ብር ነው መባሉ ሲያንስ እንጂ፣ ከገቢያቸው በላይ ሀብት አከማችተዋል ሊያስብል አይችልም፡፡ በአግባቡ ቢሠላ ኮሎኔል ጉደታ ከ1983 ዓ.ም. እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ በአገር መከላከያ ሚኒስቴርና በኢትዮ ቴሌኮም ሲከፈላቸው የነበረ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም 4,351,828 ብር እንደሚሆን፣ ከ1997 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት በላይቤሪያ ሰላም ማስከበር ወታደራዊ ግዳጅ በወር 4,000 ዶላር ይከፈላቸው እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሹ ከተለያዩ ተቋማትና ቦታዎች የተበደሯቸው ገንዘቦች በዕዳነት ተደምረው መቅረባቸውንም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡

ኮሎኔል ጉደታ ከነበራቸው ገቢ አንፃር በማኅበር ተደራጅተው በ460 ካሬ ሜትር ላይ ከ16 ግለሰቦች ጋር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ቢኖራቸውም፣ የተጋነነ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሹ አሁን ካሉበት የኑሮ ደረጃ አንፃር ያላቸው ንብረት ‹‹ከገቢያቸው በላይ ነው›› የሚያስብል ማስረጃ አለማግኘቱንና እጅግ አነስተኛ ገቢ ነው ከማለት ባለፈ፣ ‹‹ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን አይደለም›› በሚል የቀረበው ክስ ሕግን የተከተለ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በብይኑ አስፍሯል፡፡  በአጠቃላይ ኮሎኔል ጉደታ ይዘውት የተገኘው ንብረትም ሆነ ገንዘብ ከሕጋዊ ገቢያቸው በላይ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምፅ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ ክሱ ተከሳሹ በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል ይዘው መገኘታቸውንና ለሌላ ማዘዋወራቸውን ቢገልጽም፣ ፍርድ ቤቱ ሕጋዊ መሆኑን በማረጋገጥ በሕጋዊ መንገድ ያገኙት ገንዘብ በመሆኑ ይዘው መጠቀም ወይም ለቅርብ ዘመዶች ማዛወሩ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1ሀ፣ ለ እና ሐ) ድንጋጌ አኳያ የወንጀል ፍሬ ነገር የሆነ የሕግ አግባብ ስላልተገኘባቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል፡፡

በመጨረሻ ዓቃቤ ሕግ በኮሎኔል ጉደታ ላይ የመሠረተው ክስ በምርመራ ላይ በነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባል ሞባይል ላይ በመደወል፣ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ዓለምአንተ አግደው፣ ኮሎኔል ጌትነት ጉደያን ለምን ያሳድደዋል?›› በማለት በዓቃቤ ሕግ ሥራ ላይ ጣልቃ ገብተዋል የሚለውንም ፍርድ ቤቱ መመርመሩን አስረድቷል፡፡ ስልክ ተደወለላቸው የተባሉ የፌዴራል ፖሊስ አባል በሰጡት ምስክርነት ከተከሳሹ ጋር በሥራ ምክንያት እንደሚተዋወቁ ገልጸው፣ ዓቃቤ ሕግ የገለጸውን እንደጠየቋቸውም መናገራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ኮሎኔሉ የደወሉላቸው ለትብብር መሆኑን ከመግለጻቸው አንፃር ከሳሽ ዓቃቤ ሕግም ያቀረበው ተጨማሪ ማብራሪያ ካለመኖሩና ሕጉም ሊደርስበት ከታለመለት ዓላማ አኳያ ፍሬ ነገሮቹ በተሟላ ሁኔታ ያልተረጋገጡ በመሆናቸው፣ ኮሎኔል ጉደታ በሦስተኛውም ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ብይን በመስጠት መዝገቡን መዝጋቱን በትዕዛዙ አስታውቋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe