በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ 25 ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ታዘዘ

በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 8 ሺህ 35 ካሬ ሜትር የመንግስት ይዞታን አርሶ አደር ባልሆኑ ሰዎች ስም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማዘጋጀት እና በተለያየ መጠን መሬት በመውሰድ በከባድ ሙስና ወንጀል የተከሰሱ 25 ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ታዘዘ።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ ባልሆኑ ሰዎች ስም ያለአግባብ 8 ሺህ35 ካሬ ሜትር የተለያዩ መጠን ያላቸው የይዞታ ማረጋገጫ በማዘጋጀት በግለሰቦች እንዲወሰድ በማድረግ እና በመውሰድ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ 43 ግለሰቦች ላይ ባሳለፍነው ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በየደረጃው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።ክስ ከተመሰረተባቸው 43 ተከሳሾች መካከ 18ቱ በቁጥጥር ስር ውለው በዛሬው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ቀርበዋል።
ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡ ተከሳሾች መካከል 1ኛ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ግርማ፣ 2ኛ የወረዳ 14 አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት ሃላፊ እና የአርሶ አደር ኮሚቴ ሰብሳቢ አየለ ጉቱ፣ 3ኛ የወረዳ 14 አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ እና የአርሶ አደር ኮሚቴ ጸሃፊ ጎሳዬ ደሜ ጅማ፣ 4ኛ በፍቃዱ ወንድወሰን፣ 5ኛ ሮባ ደበሌ፣ 6ኛ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስተዳደር የአርሶ አደር ኮሚቴ አባል ወ/ሮ መታሰቢያ አባተ፣ 7ኛ የለሚ ኩራ ክ/ከ አስተዳደር የወረዳ 14 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ለምለም አባይነህ እሸቴ ይገኙበታል።
በዛሬው ቀጠሮ ችሎት የቀረቡ 18 ተከሳሾች በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ እንዲሻሻልላቸው በዝርዝር ጠቅሰው የክስ መቃወሚያ በጽሑፍ አቅርበዋል።
ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾች በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ በቀጣይ ቀጠሮ አስተያየት (መልስ) እንዲሰጥበት የታዘዘ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር ባለመዋላቸው ምክንያት ችሎት ያልቀረቡ 25 ተከሳሾችን ፖሊስ ካሉበት አፈላልጎ ለጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ቀደም ሲል በታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በዓቃቤ ሕግ የተመሰረተው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር በአካባቢው ነዋሪ እና አርሶ አደር ያልሆኑ ይዞታ የሌላቸውና በይዞታቸው ላይ ገንብተው የማይኖሩ ግለሰቦችን በይዞታቸው ገንብተው እየኖሩ የሚገኙ በማስመሰል ያለአግባብ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተዘጋጅቶ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
በዚህም የሕዝብን ሃብት በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ እንዳይውል ከ200 እስከ 500 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለአግባብ 22 ግለሰቦች እንዲወስዱ በማድረግና በመውሰድ በየደረጃው በልዩ ወንጀል ተካፋይነትና በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሚለው ይገኝበታል።
ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል18ኛ፣ 31ኛ፣ 33ኛ፣ 34 ኛ፣ 40ኛ ተከሳሾች በአርሶ አደር ስም ያለአግባብ እያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር መሬት መውሰዳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል።
በተመሳሳይ 35ኛ እና 39ኛ ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው 200 ካሬ ሜትር መሬት ያለአግባብ መውሰዳቸውን ነው ዓቃቤ ሕግ ያስረዳው።
ሌሎች ተከሳሾችም በየተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን÷ በአጠቃላይ 8 ሺህ 35 ካሬ ሜትር የመሬት ይዞታን በአርሶ አደር ባልሆኑ ሰዎች ስም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማዘጋጀት እና በተለያዩ መጠን ያላቸው ይዞታዎችን በመውሰድ በመንግስት ላይ ከ8 ሚሊየን 69 ሺህ ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተመላክቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe