ሦስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የድንበር ግጭት ምክንያት እስካሁን 13 ሰዎች ሲገደሉ ከ500ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ማድረጉ ሲሰማ ግጭቱም ወደ አምስት ግዛቶች እየተስፋፋ ነው ተብሏል፡፡
ሁለቱም ሀገራት ለመቶ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በድንበር ላይ ውዝግብ ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤አዲሱ ግጭት ከተቀሰቀሰ ግን ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
አንድ የታይላንድ ወታደርን እንዲሁም የካምቦዲያን ንጹሃን ጨምሮ እስካሁን የ13 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ በድንበር አካባቢ የነበሩና ቁጥራቸውም ከ500ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከስፍራው ለቀው መውጣታቸው ሲሰማ፤ድንበሩ በተዋጊ ጄቶች፡ታንኮች እና ድሮኖች እንቅስቃሴ ተሞልቷል መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ ተጎራባቾቹ ሀገራት በቅኝ ግዛት ዘመን በተካለለው ግዛት ምክንያት ግጭት ውስጥ በማሳለፍ በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡
የዚህ ሳምንቱ ግጭት ግን ሀገራቱ ባለፈው ሀምሌ ወደ ጦርነት ገብተው ለአምስት ቀናት ያህል ከተዋጉ በኋላ የተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት ነው፡፡
የሃምሌው ወር ግጭት በደርዘን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና ከ300ሺ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀል ምክንያት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የአሁኑን ግጭት ዳግም እንዲያገረሽ በማድረግ ረገድ ሁለቱም ሀገራት እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው፡፡
ካምዲያ በየትኛውም ስዓት ግጭቱን ለማስቆም ለንግግር ዝግጁ እንደሆነች ገልጻለች፡፡ የሃምሌውን ወር ግጭት በተኩስ አቁምም ስምምነት እንዲገታ ያደረገችው አሜሪካ ዳግም ያገረሸው የሁለቱ ሀገራት ግጭት እንዳሳሰባት ገልጻለች፡፡//

