‹‹በካናዳ ስደተኛ ለመሆንና ተቀባይነት ለማግኘት መጠየቅ መብት ነው›› ጠበቃ ተክለ ሚካኤል አበበ

የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው ተክለሚካኤል አበበ በአሁኑ ወቅት በካናዳ የታወቀ ጠበቃና የህግ አማካሪ ነው፤ ለዘመናት በነጮች ብቻ ተይዞ የኖረውን የጥብቅና አገልግሎት በትምህርት ታግዞ የተቀላቀለው ተክለሚካኤል  ከአዲስ አበባ አልፎ የክልል ዩኒቨርሲቲዎችን ያካለለውና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መብት በመጠየቃቸው የተነሳ ለስደት ከተዳረጉ የ1992 ዓ.ም የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ተማረዎች መሀከል አንዱ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በካናዳ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ተክለሚካኤል በልዩ ልዩ ምክንያት ከሀገር ወጥተው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሚጠይቁ ኢትዮጵያውያን የህግ ድጋፍ በማድረግ ብቻ ሳይወሰን ኢትዮጵያውያንን በማስጠጋት የወገን አለኝታነቱን እያሳየ ያለ ወጣት የህግ ሰው ነው፤ ከአዲስ አበባ የሐመረ ኪን የስነ ፅሑፍ ማኅበር የጀመረው የተክለሚካኤል አበበ የህይወት ጉዞ እስከ አሜሪካ የኢሳት ቢሮ ዘልቋል፤ በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ በሚሰነዝራቸው በሳል አስተያየቶቹ የሚታወቀው ተክለሚካኤልን ቶሮንቶ ላይ ጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ አግኝቶት ቆይታ አድርጓል፡፡

ቁም ነገር፡-  ተክሌ ካናዳ ቶሮንቶ ነው የተገናኘነው እና ወደ ኋላ ወደ ትውልድ መንደርህ ወደ ነገሌ ቦረና ልመልስ፤ የልጅነት ህይወትህ ምን ይመለስል ነበር? ስለ ቤተሰቦችህ ንገረኝ እስኪ?

ተክለ ሚካኤል፡-አመሰግናለሁ ታሜ፤ እንደጠቀስከው ነገሌ ቦረና ነው የተወለድኩት በሐምሌ ወር በ1969 ዓ.ም ፤ ነገሌ ቦረና 27 ሻለቃ ይባላል፤ 4ኛ ክፍለ ጦር አብዮቱ የተቀሰቀሰበት አካባቢ ነው ይባላል ያ አካባቢ፤አባቴ ሃምሳ አለቃ አበበ ሳህለማርይም የሸዋ ቡልጋ  ሰው ነው፤እናቴ ደግሞ ወሎ የየጁ ቆንጆ ነች፤ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተጋቡና አባቴ ወዲያውኑ ወደ ኮንጎ ዘመተ፤ከኮንጎ ከተመለሰ በኋላ ወደ ኦጋዴን ሄዱ፤ከእዛ ወደ ነገሌ ቦረና ተዛውሮ ለረጅም ጊዜ  ከ25 ዓመታት በላይ የኖርነው እዛ ነው፤ከሁለት ልጆች በቀር እዛ ነው የተወለድነው፤

ቁም ነገር፡-ስንት ናችሁ እህትና ወንድም?

ተክለ ሚካኤል፡-ስድስት ነን፤ የልጅነት ህይወታችን በጣም ደስ ይል ነበር፤ አባታችን ወታደር ቢሆንም ነገሌ ቦረና  ብዙ ከብቶች ነበሩን፤የቦረና ከብቶች ጋር ነው ያደግነው ላሞች ይታለባሉ፤ ጥጆች ይልዳሉ፤ከአካባቢው ህዝብ ጋር ጥሩ ህይወት ነበረን፤

ቁም ነገር፡-የት ተማርክ?

ተክለ ሚካኤል፡-እስከ አንደኛ ደረጃ ድረስ ሾላ የሚባል ትምህርት ቤት ነበረ፤እስከ ስድስት ማለት ነው፤ከእዛ በአባታችን በ1978 ጡረታ ሲወጣ ከሶስት ዓመታት በኋላ ወደ አርሲ ነገሌ መጣን፤ በእዛን ወቅት አንድ የጦር ሰራዊት በአባል ጡረታ ሲወጣ ወደ ሻሸመኔ ወይም ወደ አርሲ ነገሌ በነበር ወታደሩ ሄዶ የሚኖረው፤ከሰባተኛ ጀምሮ እንግዲህ የተማርኩት አርሲ ነገሌ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ነው፤በ88 ዓ.ም ለተወሰነ ጊዜ አዲስ አበባ መጥቼ ነበር፤

ቁም ነገር፡-ለምን?

ተክለ ሚካኤል፡- 11ኛ ክፍል ስገባ ትንሽ ጉርምስናንም ብጤ መጣ መሰለኝ አመፀኛ ነበርኩ፤ትምህርት ቤት ውስጥ የተማሪዎችን መብት ለማስከበር እንቀሳቀስ ነበር፤ በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ለምሳሌ የመመዝገቢያ ተማሪዎች ሃያ ሃያ ብር ክፈሉ ሲል እኛ መክፈል ስለማንችል እናሳምፃለን፤እኛ ቤት ሶስት ልጆች አሉ አባታችን ጡረታ ስለወጣ ደሞዙ 109 ብር ብቻ ነው፤ከእዛ ደሞዝ ላይ ስልሳ ብር ከከፈለ የሚቀረው 49 ብር ነው፤ ከእዛ ላይ የእድር ተከፍሎ፤ለምግብ ለሌሎች ወጪዎች መክፈል አይችልም፤ስለዚህ መከፈል የለብንም በሚል እንቃወም ነበር፤ እንደውም መከፈል ካለበትም ከአንድ በላይ ተማሪ በአንድ ትምህር ቤት ያለው ወላጅ ለእንዱ ተማሪ ብቻ ነው መክፈል ያለበት ብለን እንታገል ነበር፤ያንን በማለታችን ታሳምፃላችሁ፤ወላጅ አምጡ ሲባል ከመምህራን ጋር በተለይ እኔ ተጣላሁ፤ በዚህ የተነሳ አባረሩኝ፤ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በዚህ ሰበብ ነው፤ መልቀቂያ አውጥቼ በ1988 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህር ቤት መጣሁ ማለት ነው፤ አዲስ አበባን የማውቃት 11ኛ ክፍልን ለመማር የመጣሁ ጊዜ ነው፤ 12ኛ ክፍልን ግን እዛው አርሲ ነገሌ ሄጄ ነው ማትሪክ የተፈተንኩት፤ በ1990 ዓ፣ም እንደገና ውጤት አምጥቼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመድቤ ድጋሚ አዲስ አበባ መጣሁ ማለት ነው፤

ቁም ነገር፡-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማርከው ህግ ነው፤ እንዴት ዕድሉን አገኘኸ?

ተክለ ሚካኤል፡-ይመስልኛል አርሲ ነገሌ እያለሁ ቤተክፈርስቲያን መሄድ አዘወትር ነበር፤ደስ ይለኛል፤ድቁናም  ተቀብዬ ነበር፤

ቁም ነገር፡-ትቀድስ ነበር ማለት ነው?

ተክለ ሚካኤል፡-በሚገባ፤ አንድ ሁለት ሶስት ዓመት አልቀደስኩም ብለህ ነው?ቅዱስ ጊዮዎርጊስ፤ ወዮ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን፤ቀርሳ ኢላላ ሁሉ ቀድሻለሁ፤ እንደውም ቀርሳ ኢላላ በ15 ብር ሁሉ ተቀጥሬ ነበር፤/ሳቅ/በነገራችን ላይ ከዚህችውም ደሞዝ ላይ እሁድ እሁድ ያረፈድኩ ከሆነ ወይም እንቅልፍ ጥሎኝ ያልቀደስኩ ከሆነ አምስት ብር ገደማ ይቆረጥብኝ ነበር፤ቀርሳ ኢላላ አካባቢ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የምኖርበት ቦታ ነው፤ ለእሁድ ቅዳሴ ቅዳሜ ማታ ሁሉ ሄደን አንዳንድ ጊዜ የምናድርበት ጊዜ አለ፤እስካሁን ድረስ የአካባቢውን ህዝብ ሳስብ በአይኔ ላይ የሚመጣ አንድ ነገር አለ፤ ለቅዳሴ ወደ ቤተክርስቲያን ስንሄድ ህዝቡ ማታ ተቀብሎ ራት ያበላን ነበር፤ጠጅ ሁሉ ያቀርቡልናል ሀብታም ገበሬ ከሆነ ደግሞ  በግ ሁሉ ይታረድልን ነበር፤እርጎ አለ፤ደስ የሚል ህዝብ ነበር፤

ቁም ነገር፡-ግዕዝ ላይ እንዴት ነህ ታዲያ ?

ተክለ ሚካኤል፡-እሞካክር ነበር፤መልካ እየሱስ፤መልካ ጊዮርጊስንም እሞካክር ነበር፤ሰዓታት ማህሌት እንቆም ነበር፤ዳዊትም እደግማለሁ፤ያው እንደ ዲያቆን እሞካክር ነበር፤እንግዲህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ማለፌ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ወደ ህግ ትምህርት ክፍል እንግድገባና ስለፍትህ እንዳውቅ ፍላጎት ሳያሳድርብኝ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፤ቤተክርስቲያንም ውስጥ ብዙ ነገሮችን ትማራለህ፤በጣም የሚገርም ደግነት የምትማረውን ያህል ፅንፍ የወጣ ስስትነት ታያለህ፤ በተለይ ድግስ ሲኖር ብዙ ህይወት ታያለህ፤ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላም ዩኒቨርሲቲ አጠገብ ያለው ማርቆስ ቤተክርስቲያን እሄድ ነበር፤ ግን እንደበፊቱ ለመሳተፍ ምናምን ያስቸግር ነበር፤

ቁም ነገር፡-ዩኒቨርሲቲ እንደገባህ እንደ ክፍለ ሀገር ልጅ አልነበርክም ይባላል፤ በብዙ ነገሮች ውስጥ ትሳተፍ ነበር፤ ፖለቲካውን ጨምሮ ፤እንዴት ነበር ሁኔታው?

ተክለ ሚካኤል፡-እንግዲህ የወታደር ልጅ ነኝ ብየሃለሁ፤ ማድረግ የፈለኩትን ነገር ለማድረግ ፍርሃት የሚባል ነገር የለኝም፤ ያሰብኩትን እጠይቃለሁ፤ እሞክራለሁ፤ እንዳልከው በእኛ ጊዜ የነበረው ባች በተለያዩ ነገሮች ውስጥ ይሳተፍ ነበር፤ የስነ ፅሑፍ ክበብ ውስጥ እንሳተፋለን፤ የመብት ጥያቄዎችም ሲነሱ እንሳተፋለን፤

ቁም ነገር፡-እነማን ነበሩ?

ተክለ ሚካኤል፡- እንግዲህ እኔ 1990 ገብቼ በ1993 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የነበረበት ጊዜ ነው፤ በፀረ ኤድስ ክበብ፤ በስፖርት፤ በስነ ፅሑፍ፤ በፖለቲካ አስተሳሰብ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረበትና በክበባት መስክ ብዙ ተሳታፊዎች የነበሩበት ወቅት ነው፤  እንደ በዕውቀቱ ስዩም፤ ፍቅር ይልቃል፤ ብዙ ልጆች ይሳተፉ ነበር፤ በተለይ በስነ ፅሑፉ ዘርፍ፤ ከግቢ ውጭ ደግሞ እንደ በሃይሉ ገ/እግዚአብሔር፤ ሁሴን ከድር፤ በፍቅሩ ዳኛቸው፤ መስፍን፤ አበበ ቶላ /አቤ ቶክቻው/ ጋር ሐመረ ኪን የሚባል ክበብ ሁሉ አቋቁመን ብዙ ስራዎችን የሰራንበት ጊዜ ነበር፤

ቁም ነገር፡-የ1993ቱን የዩኒቨርሲቲ ህይወት ስታነሳ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ነበርክና ትልቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር፤ እስኪ ምንድን ነበር የሚመስለው ያ ወቅት?

ተክለ ሚካኤል፡-የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ሆኜ የተመረጥረኩት በ1992 ዓ.ም ነው፤ የህግ የ3ኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ማለት ነው፤የተመረጥኩት በግንቦት ወር 1992 ነው፤እንደተመረጥኩ ለረጅም ጊዜ ሳትታተም የቆየችውን ‹ህሊና› የሚል ርዕስ ያላትን ጋዜጣ ማሳተም ጀመርን፤የመጀመሪያዋን ዕትም አውጥተን ሁለተኛውን እትም ለመስራት ስንዘገጃጅ ማሳተም አትችሉም ተብለን ታገድን በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ማለት ነው፤እንግዲህ ከመንግስት ጋር ጠብ  ውስጥ የገባነው ለጋዜጣ ማሳተሚያ ያለንን ገንዘብ ዩኒቨርሲቲው አለቅም ሲል ነው፤ ማህበራችን ሌላ ገንዘብ ማንቀሳቀሻ ዘዴ ስለሌለው አለመግባባቱ እየጨመረ መጣ፤ግቢያችን ውስጥ በወቅታዊ ጉዳይ ራሱ መሰብሰብ አልቻልንም፤ ምንም አይነት ማስታወቂያ ለተማሪዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ስንለጥፍ ይቀዱብናል፤የተወንን ተማሪዎች በኋላ ላይ ተከሰስን፤ እኔና መስፍን ገ/ስላሴ የሚባል ልጅ አሁን አውስትራሊያ የሚኖር ልጅ ተከሰስን፤

ቁም ነገር፡-በምን ምክንያት?

ተክለ ሚካኤል፡-ያው በተማሪዎች መሀከል አመፅ ለመቀስቀስ ትሞክራለችሁ ታነሳሳላችሁ በሚል እዛው ግቢው ውስጥ ባለው ፖሊስ ተከሰስን፤ እየጠሩም ሊያስፈራሩን ይሞክሩ ነበር ፖሊሶቹ፤ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ሲመጣ ያው ሀገር ለቀን እስከ መሰደድ የሚደርስ ውሳኔ ላይ ደረስን ማለት ነው፡፡

ቁም ነገር፡-ያ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የወቅር ቤቶች ዘረፋ ሁሉ ተከናውኖ ምንጩ የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው በሚል ከፍተኛ የሚዲያ ዘገባ ሁሉ ይሰራባችሁ ነበር፤

ተክለ ሚካኤል፡- ወርቅ ቤቶቹ ይዘረፉ አይዘረፉ በወቅቱ አናውቅም፤ መንግስት በቴሌቪዥን ሲናገር ነው የሰማነው፤በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ወርቅ ቤቶች በከፍተኛ ጥበቃ ስር ንግዳቸውን እንደሚያካሂዱ ይታወቃል፤ በኢትዮጵያ ግን ያለውን እውነታ ህዝቡ ያውቀዋል፤ እላይ ወርቅ እየተሸጠ በሩ ላይ የተራበ ድሃ ፀጥ ብሎ የሚተኛባት ከተማ ናት፤መንግስት ለምን የተማሪዎች ጥያቄ ከእንደዚህ አይነት ጉዳይ ጋር ለማያያዝ እንደፈለገ አላውቅም፤ ያም ሆኖ ግን በወቅቱ በከተማው በተነሳው ግርግር መንግስት እንኳ ባመነው መሠረት ወደ 41 ሰዎች ተገድለዋል ነው የተባለው፡፡አመፁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቢጀምሩም በጠቀስኩልህ ምክንያት የተፈሪ መኮንን፤ የመነን፤ የወንዲራድ፤ የኮከበ ፅባህ ተማሪዎች የተቀላቀሉት እንቅስቀሳሴ ነበር፤

ቁም ነገር፡-ጥያቄችሁ በወቅቱ ምን ነበር?

ተክለ ሚካኤል፡-ግልፅና ቀጥተኛ ሆነ ጥያቄ ነበር ያቀረብነው፤ የመጀመሪያው የተቋረጠው የጋዜጣችን ህትመት ይቀጥል የሚል ነው፤ ሌላው የተማሪዎች ማህበር የመጀራጀት መብቱ ይከበር የሚል ነው፤ሶስተኛው የዩኒቨርሰቲው አስተዳደር ሙሰኛ በመሆኑ ይለወጥ፤ አራተኛውና ዋናው ጥያቄያችን የዩኒቨርሲቲው ፖሊስ ከግቢያችን ይውጣ  የሚሉ ጥያቄዎችን ነው ያቀረብነው፤ዩኒቨርሲቲው የሲቪል ተቋም ነው፤ ስለዚህ ፖሊሶች ይውጡና በሲቪል ፖሊሶች ግቢው ይጠበቅ ነበር ያልነው፤ፖሊስ በወቅቱ የሚፈልገውን ተማሪ ከዶርሙ ወስዶ እዛው ያስራል ፤ ከግቢ ውጭም ባለው መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ያስር ነበር፤ እነዚህ ነበሩ ጥያቄዎቹ፤

ቁም ነገር፡-ግን በወቅቱ ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምና ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ ስብሰባ ስለመቀመጣችሁና መመሪያም ስለመቀበላችሁ መንግስት ይናገር ነበር፤ ምንድነው እውነታው?

ተክለ ሚካኤል፡-የተማሪዎች ህብረት አባላት እንደረመረጥን የተማሪዎችን መብት ለማስከበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተን ነበር፤ መስከረም ላይ አዳዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች እናደርግ ነበር፤ ጋዜጣዋንም አሳትመን ስለነበር በየዶርሙ አሰራጭተን ነበር፤ የተለያዩ ፅሁፎችንም በእንደ ጦቢያ፤ኢትኦጵ ባሉ ጋዜጦች ላይ  በመፃፍ የተማሪዎች ህብረቱን ለማጠናከር እንሞክር ነበር፤ከእነ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ጋር የተገናኘነው ደብዳቤ ፅፈን ነው፤ እሳቸው የእዛን ጊዜ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ፕሬዚዳንት ናቸው፤ ስለ ሰብኣዊ መብቶች ለመወያየት ፖናል መድረክ አዘጋጁልን አልናቸውና በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ አዘጋጁልን፤ አስታውሳለሁ መጋቢት 30 ነበር ውይይቱ የተካሄደው፤ በእለቱ ፕሮፌሰር መስፍንና ዶ/ር ብርሃኑ መጥተው ንግግር አድርገዋል፤ ውይይቱ ላይ  ዶ/ር ብርሃኑ እንደውም ስለ አካዳሚክ ነፃነት ምንነት ነበር የተናገረው፤ ይሄ የሆነው እሁድ ነው፤ ሰኞ ጠዋት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እንቅስቃሴ ተጀመረ፤ቁጣ ተቀሰቀሰ፤ ቀደም ሲል የነበሩት ጥያቄዎች ይመለሱ የሚሉ ጥያቄዎች መጡ፤ ማክሰኞን  ውሎ ረቡዕ ተቃውሞው ፈነዳ ማለት ነው፤ ብዙ ተማሪዎች ተደበደቡ፤ ፖሊስ ግቢውን ሰብሮ ገባ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  በተማሪዎች አይወደድም ነበር፤

ቁም ነገር፡- ለምን?

ተክለ ሚካኤል፡- ያው  የሚታወቅ ነው፤ አንድን ዘገባ እንዴት እንደሚዘግበው ይታወቃል፤ በዚህ የተነሳ ያ ሁኩ ተማሪ ተደብድቦ ታስሮ ገነት ዘውዴን ተከትሎ ኢቲቪ መጣ፤ አስታውሳለሁ ያንን ዘገባ ለመዘገብ የመጣው ስለሺ ሽብሩ ነበር፤ ተማሪዎች ኢቲቪ ግቢ አይገባም ሲሉ ስለሺ ወደእኔ መጥቶ ግድየለህም ያለውን እውነታ አሳያለሁ፤ አስፈቅድልንና እንግባ አለኝ፤ ከእዛ እንዲገቡ አደረግንና ዜናው ተሰራለ የነበረው ዜና ቀለል ያለ ነበር፤ ግን የታየው ፊልም በየዶርሙ ውስጥና በረንዳ ላይ ብዙ ተማሪዎች በፖሊስ ቆመጥ ይደበደቡ ስለነበር ደማቸው በየመንገዱ ፈሶ የነበረው በቲቪ ሲታይ ከተማው በማግስቱ ቀውጢ ሆነ፤ ወላጆችም ልጆቻቸውን ፍለጋ ወደ ዩኒቨርሲቲው መጡ፤ ረብሻው ሰፋ፤ እነ ፕሮፌሰር መስፍንም ታሰሩ፤ ብዙ ተማሪዎችም ታሰሩ፤በሳምንቱ ያ ሁሉ ተማሪ ታስሮ የትምህርት ሚኒስትሯ ገነት ዘውዴ ልታነጋግረን መጣች፤ ግን ሳንስማማ ተለያየን፤በእዛ መሀል እንደውም አንድ ተማሪ መቀሌ ላይ ተገድሎ ተገኘ፤ ያ እንደገና የተማሪውን ቁጣ አባባሰው፤መንግስት ከዚህ በኋላ ትምህርተ እስከዚህ ቀን ድረስ ጀምሩ ብሎ ቀነ ገደብ አወጣ፤ ተማሪው አልተቀበልም አለ፤ ከእዛ ዩኒቨርሲቲውን ለቃችሁ ውጡ አለ መንግስት፤ዓመቱ ሊያልቅ ሁለትና ሶስት ወር ሲቀረው ነው ይሄ ችግር የተፈጠረው፤ዩኒቨርሲቲው ተዘጋ፤

ቁም ነገር፡-ይህንኑ ተከትሎ ነው ከሀገር የተሰደድከው ማለት ነው?

ተክለ ሚካኤል፡-ጓደኞቼ በሙሉ ታሰሩ፤እኔም እየተፈለኩ ስለነበር ተደበቅሁ፤ ወደ አርሲ ነገሌ ሊሄድ ይችላል ብለው ወደ እዚያ ሄደው ቤታችን በወታደሮች ተከቦ እናቴንና ወንድሜን አሰሯቸው፤ እናቴን ከየእዛኑ እለት ለቀቋት ወንድሜ ግን በእኔ ሰበብ ታሰረ፤በአጋጣሚ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት አላውቅም፣ እኔን ፍለጋ ወደ አርሲ ነገሌ ወታደሮች ሲሄዱ ሄሊኮፍተርም በከተማው ላይ ሲያልፍ ታይቷል መሰለኝ፤ እና በግል ፕሬሱ ላይ ‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተክለ ሚካኤል አበበን ፍለጋ መንግስት ሄሊኮፍተር አሰማራ› ተብሎ መዘገቡን አስታውሳለሁ፡፡

ቁም ነገር፡-ግን ላንተ ተብሎ ነበር ሄሊኮፍተሩ የመጣው?

ተክለ ሚካኤል፡-እኔ አላውቅም፤ አይመስለኝም፤ መንግስት ለአንድ ተማሪ ብሎ ሄሊኮፍተር ሊሰራማ የሚችል አይመስለኝም፤ ግን በጋዜጦቹ ላይ የወጣው ዜና እንደዛ አይነት ስለነበር እውነት ይሆን እንዴ ብዬ እኔ ራሴ መፍራት ጀምሬ ነበር፤

ቁም ነገር፡-የት ነበርክ የዛን ጊዜ?

ተክለ ሚካኤል፡-አዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ ነበርኩ፤ አሁን ብናገረው ደስ ከሚሉኝ ነገሮች መሀከል የነበርኩበት ቤት የዛን ጊዜ የዩነቨርሲቲው የሴኔት አባል የነበረ ሰው ቤት ውስጥ ነበር የተደበቅሁት፤በኋላ ይህ ሰው ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆኖ ነበር አቶ ተስፋዬ ብሩ ይባላል፡፡በጣም ባለውለታዬ ሰው ነው፡፡ በራሱ መኪና እኔን ፋሲካን እንዲሁም ትዕግስት የምትባል ልጅን ይዞን ወደ ቤቱ የወሰደን፡፡ ትልቅ ሰው ነው በእውነት፡፡ከእዛ ወደ ቤት ስደውል እናቴ ነገረችኝ ሁኔታውን፤ ወንድምህ አሁንም ባንተ የተነሳ እንደታሰረ ነው አለችኝ፤ ከእዛ ከአቶ ተስፋዬ ቤት ወጥቼ ወደ ሌላ ቦታ ሄድኩ፤ አንድ 15 ቀናት ከቆየሁ በኋላ ወደ ኬኒያ ተሰድድኩ፡፡

ቁም ነገር፡-ሁኔታውን ትከታተል ነበር እዛ ሆነህ?

ተክለ ሚካኤል፡-በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ብቻ ነበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ዜና እከታተል የነበረው፤ አንድ ቀን ግን ፋሲል የሚባል ተማሪ እንደታሰረና በራዲዮና በቴሌቪዥን እንዳቀረቡት ሰማሁ፤ያንን የሰማሁት በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ፕሬሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ተጠይቀው ሲናገሩ ነው፤

ቁም ነገር፡- ከዚያ በፊት ግን የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ሆነህ ስትመረጥ ከሀገር ልሰደድ እችላለሁ ብለህ ታስብ ነበር?

ተክለ ሚካኤል፡-ከሀገር እንድትወጣ የሚስገድዱህ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ችግሮችም ነበሩ፤በዚያ ቅፅበት አይሁን እንጂ የሀገሪቱ ፖለቲካ እየተበላሸ እንደሆነ ይታይ ነበር፤ ግን ትምህርቴን  ጨርሼ ምናልባት ሁኔታው የማይሆን ከሆነ ነበር እወጣለሁ ብዬ አስብ የነበረው፤ ግን መንግስት ገና ትምህርት ቤት እያለን ውጡ አለን ማለት ነው፤/ሳቅ/

ቁም ነገር፡-የኬኒያ የስደት ህይወት ምን ይመስላል? ምን ያህል ጊዜ ቆየህ ኬኒያ?

ተክለ ሚካኤል፡-አራት ዓመት ነው የቆየሁት ኬኒያ፤ከ1993 እስከ 1997 ድረስ ማለት ነው፤የኬኒያ ቆይታዬን እንደ ትምህርት ቤት ነው የምቆጥረው፡፡በቤተሰብ ውስጥ በእንክብካቤ ላደገ እንደገና በዩኒቨርሲቲ በዶርም ውስጥ ለኖረ ተማሪ የኬኒያ ህይወት ብዙ የተማርኩበት ነው፡፡እዛ ቦታ በተለያየ ምክንያት የተሰደደ ሰው የምታገኝበት ቦታ ነው፡፡ ተማሪዎች ብቻ  ወደ 200 ያህል እንሆናለን፤የምንኖረው ካምፕ ውስጥ ነው፤ ካምፑ ውስጥ ደግሞ ወባ አለ፤ ትታመማለህ፤ምግብ በቂ አቅርቦት የለም፤አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፤ህይወት አስቸጋሪ ነበር፤ ባይገርምህ ኬኒያ እያለሁ ቢያንስ ለ10 ጊዜ ታስሬያለሁ፤ ፖሊሶች ይደበድቡሃል፤ ሻይ እሸጥ ነበር፤ ፑል አጫውት ነበር፤ ግን ከፖሊሶች እስር ማምለጥ አስቸጋሪ ነው፤ እንዳዛም ሆኖ ዩኤን ያስፈታናል፤ እንደገና እንታሰር ነበር፤

ቁም ነገር፡-ቤተሰብ ጋር በስልክም ቢሆን መገናኘት አልሞከርክም?

ተክለ ሚካኤል፡-አስቸጋሪ ነው ስጋትም አለ፤ እየተፈለክ ነው እየተባለ የቤተሰብህ አባል ታስሮ አንተ ስልክ ለመደወል አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ኬኒያ እንደገባሁ በ15ኛው ቀን መስለኛል በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ቀርቤ ተናገርኩ፤ደህና መሆኔን በዚህ አማካኝነት አሳወቅሁ ለቤተሰብ ማለት ነው፡፡ትንሽ አረፍ አሉ፤

ቁም ነገር፡-ከኬኒያ ወደ ካናዳ እንዴት ሄድክ?

ተክለ ሚካኤል፡-አብረን ከተሰደድን ተማሪዎች መሀከል እሸቱ የሚባለው ልጅ ቀድሞን ካናዳ ገብቶ ነበር፤ እና በአንድ ጀስዊቶች የስደተኞች ድርጅት አማካይነት ከለላ ድርጅት ጋር አገናኝተውን ወደ ካናዳ ሄድን ማለት ነው፡፡ካናዳም ህይወት ቀላል አልሆነም፤ የጉልበት ስራ እሰራሁ  መኖር የመጀመሪያ ምርጫዬ ነበር፤

ቁም ነገር፡- ሀገሬ ካልገባሁ ፀጉሬን አልቆረጥም ብለህ አምፀህ ነበር ይባላል?

ተክለ ሚካኤል፡- አዎ፤እኔ  በዚህ መልክ ከሀገሬ ብወጣም ወደ ሀገሬ ተምልሼ እገባለሁ የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ፤ ለዚህ ነው ፀጉሬን አልቆረጥም ብዬ ድሬድ ያደረኩት፤ ፀጉሬ ለረዥም ዓመታት ድሬድ ነበር፤ግን ወደ ሀገሬ ስገባ  ቢያንስ ስራ የምሰራበት ትምህርት መማር አለብኝ ብዬ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ ከሀገር የወጣሁት ልመረቅ አንድ ዓመት ሲቀረኝ ቢሆንም ምንም ማስረጃ ስለሌለኝ ከባዶ ነበር የጀመርኩት፡፡ከእዛ ከብሪትሽ ስኩል ኦፍ ኮሎምቢያ በህግ ተመረቅሁ ኤልኤል ቢ ዲግሪ ማለት ነው በኢትዮጵያ፤ እዚህ ግን ጄዲ ጁሪስ ዶክተር ነው የሚባለው፤ ይህንን የህግ ዲግሪ ለማግኘት በአሜሪካና በካናዳ መጀመሪያ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ዲግሪ ሊኖርህ ይገባል፤

ቁም ነገር፡- በጋዜጠኝነትም ኢሳት ወስጥ ነበርክ አይደል?

ተክለ ሚካኤል፡-ልክ ነህ፤ እንደተመረቅሁ ወደ አመስተዳም ሂሄጄ ኢሳት እንደተከፈተ ሰሞን እዛ መስራት ጀምሬ ነበር፤ ብዙም ሳይቆ መንግስት ጃም አደረገው፤ሚዲያ ላይ መስራት በጣም እወዳለሁ፤ ማስተርስ ድግሪን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦቶዋ ውስጥ ቀጠልኩና ስጨርስ ነው ለእንድ ዓመት ያህል ወደ አሜሪካ ሄጄ 2011 ላይ ኢሳት ውስጥ መስራት የጀመርኩት፤ሳየው ጣቢያው በብዙ መንገድ የሚያስኬድ አልመሰለኝም፤ ትግሉም ረዘመብኝ መሰለኝ፤መለስ ሞቶ ሀይለማርያም ሲሾም ወጣሁና ወደ ካናዳ ተመልሼ የግል የጥብቅና ፈቃድ ለማውጣት እንቅስቃሴ ጀምርኩ ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ  በ2014  ፈተናዎቹን ጨርሼ ፈቃድ አገኘሁ፤ ከእዛ ወደ ጥብቅናው ስራ ገባሁ ማለት ነው፡፡ከዚህ በኋላ ጥያቄህን ስታቀርብ ጠበቃ ተክለሚካኤል ማለት ትችላለህ ማለት ነው፤/ሳቅ/

ቁም ነገር፡- እንግዲህ ወደ ጥብቅና ሙያ ከገባህና ይህ ቢሮ ከተከፈተ በኋላ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በአንተ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ስደተኞችን ወደ ህጋዊነት የማምጣቱ ስራ ምን ያህል ፈታኝ ነው?

ተክለ ሚካኤል፡-በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡እንደምታውቀው በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ ስማ በለው ይበዛል፤ በመረጃ ላይ ከመመስረት ይልቅ በልማድ መመራት ይበዛል፤ዘመናዊውን ህግ ከማክበር ይልቅ እንደውም በባህላዊ መንገድ ያለውን ህግ መከተል ይቀናናል፤ አሁን ለምሳሌ ትልቅ ሰው ሲመጣ ብድግ ትላለህ፤ ይህ ባህላችን ነው፤በዚህ የስደት ህይወት ሰዎች የሰሙትን ያምናሉ ከእውነታው ይልቅ፤ ወይም በሌላ አባባል አንድ ሰው በሆነ መንገድ ጉዳዩ ተቀባይነት ካገኘ ያንን ያምንና በእዛው መንገድ መሄድ ይፈልጋል፡፡ጭራሽ እነዛ ሰዎች የህግ መካሪ ይሆናሉ፤ ሌላው ችግር በዚህ ስራ ላይ የኮሚዩኒኬሽን ትልቅ ክፍተት አለብን፤ብዙ ሰዎች ምሳ በልተሃል ወይስ አልበላህም? ተብለው ሲጠየቁ አዎ ወይም አልበላሁም አይሉህም፤ 90 ከመቶ አይ ችግር የለም፤ ተወው፤ ዛሬ እኮ ፆም ነው ነው የሚሉህ፤ የምትጋብዘው ይመስል፤ ጥያቄው ግልፅ ነው ፤ መልሱም በግልፅ መስጠት ይገባል፤ስለዚህ የእኛ ሰዎች እዚህ ሀገር ከመጡ በኋላ ያለው ችግር ምንድነው ብትለኝ  ሀ/ የኮሚዩኒኬሽን ችግር፤ለ/ ህግን የማክበር ጉዳይ ሐ/ በባህላዊ ዕውቀት ላይ መመስረት ነው ልል እችላለሁ፤

ቁም ነገር፡- በስደት የሚመጡ ሰዎች ህጋዊ ለመሆን ይፈልጋሉና ያለው ችግር ምንድነው?

ተክለ ሚካኤል፡- በአብዛኛዎቹ ሰዎች ጉዳያቸው የሚበላሽባቸው የተሳሳተ መረጃ በመስጠታቸው ነው፡፡ እዚህ ሀገር ስደተኛ ለመሆንና ተቀባይነት ለማግኘት መጠየቅ መብት ነው፡፡በማንኛውም መልኩ ካናዳ  አሳይለም መጠየቅ ትችላለህ፤ገና ኤርፖርት እንደደርስክ ምንም ሳትሸማቀቅ ላገኘኸውን ኦፊሰር ሰላም ብለህ ‹እኔ የመጣሁት አሳይለም ለመጠየቅ ነው› ብትለው ደስታውን አይችለውም፤ከእዛ ደቂቃ ጀምሮ ህጉን ነው መተግባር የሚጀምሩት፡፡ስራቸውን ነው የምታቀልላቸው፤ ጥያቄ ሲጠይቁህ ትክክልኛውን ምለሽ መስጠት ነው ካንተ የሚጠበቀው፡፡ትልቁ ችግር የሚመጣው ለተጠየቁት ጥያቄ የተሳሳተ ወይም የውሸት ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡ ለምሳሌ እዚህ ሀገር የምታውቀው ሰው ወይም ዘመድ አለህ? ተብለህ ከተጠየቅህ ሰው ካለ ‹አዎ› ነው ማለት ያለብህ፤ ብዙ ሰዎች ሰው እያወቁ ይዋሻሉ፤ ዘመድ እንዳለህ ማወቅ ለኢሚግሬሽን ኦፊሰሮች ስራቸውን ያቀልላቸዋል፤ ስትዋሽ ግን ጉዳይን ከባድ ያደርገዋል፡፡ስማቸውን ሁሉ ቀይረው የሚናገሩ አሉ፤ዶክመንት የለንም ብለው ዶክመንት ይገኝባቸዋል፤ አሻራቸውን ሌላ ሀገር ላይ ሰጥተው ከነበር ይያዝባቸዋል፤ነገሩን ውስብስብ ያደርገዋል፤ ሌላው ደግሞ የማይሆን መረጃ ይዘው የፖለቲካ ድርጅት አባል ነኝ ይላሉ፤  ለምሳሌ የግንቦት ሰባት አባል መሆን፤ የኦነግ አባል መሆን በካናዳ ተቀባይነትን አያስገኝም፤

ቁም ነገር፡-ለምን?

ተክለ ሚካኤል፡-በበሀይል መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ የሚታገል ድርጅትን የካናዳ መንግስት በስደተኝነት አይቀበልም፤የፖርቲው አባል መሆን ትችላለህ፤ ጉዳህን ግን ተቀባይነት አያስገኝም፤ ይህንን ባለመረዳት የዛኛው ድርጅት አባል ነኝ፤ የዚህኛው ድርጅት አባል ነኝ የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡አልበሽር ለምሳሌ አምባገነን መሪ ነበር፤ ግን አልበሽርን በመሳሪያ ለመጣል ነው የምታገለው ብትል የካናዳ መንግስት አይቀበልህም፤ በሀይል የሚያምኑ ድርጅቶችን የካናዳ መንግስት አይደግፍም ነው ህጉ የሚለው፤አንድ ጊዜ ኬዝህ ከተበላሸ በኋላ ለማቃናት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ልጅ እያላቸው ልጅ የለንም ያሉ ሰዎች ልጃቸውን በኋላ ለማምጣት ይቸገራሉ፡፡ብቻ የእውቀት ማነስ ነው፤በእዛ ላይ የምትይዘው ጠበቃም ማንነት ይወስነዋል፤ አሁን እንደውም እየበዛን መጣን እንጂ ሀበሾች በፊት ነጮቹ ነበሩ ጉዳዩን የሚይዙት፤ እኛ ብንሆን ባህላችንን ስለምናው አንዳንድ ኬዞችን ለማቃናት እንችላለን፤ ፈረንጆቹ ግን ቀጥተኞች ስለሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠኸውን ቃል ብቻ ተከትለው ነው የሚሄዱትና አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል፤

ቁም ነገር፡- በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ የካናዳ መንግስት የስደተኞች ጥያቄ ላይ  የአቋም ለውጥ አድርጓል ወይስ?

ተክለ ሚካኤል፡-ለመጀመሪዎቹ አራትና አምስት ወራት ነበር፤ በሀገራችሁ ለውጥ በጥቷል፤ የፖለቲካ እስረኞች ተፈትተዋል፤ አሁን ህዝቡ ለመንግስት ድጋፍ እያሳየ ነው ይሉ ነበር፤ ለዚያውም ሁለትና ሶስት ዳኞች ናቸው እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው፤ በእኔ ኬዝ አሁን  ነገሮች ተመለስሰው ወደነበሩበት እየተመለሱ ስለሆነ ያን ያህል የአቋም ለውጥ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለውጥ በአንድ ጊዜ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለተቀየረ የሚመጣ አይደለም፡፡ ስድስት ሚሊየን አባል አለኝ የሚለው ኢህአዴግ እኮ አልተቀየረም፤ካድሬው እንዳለ ነው፤እኔ በግል የለውጡ ደጋፊ ነኝ፤ ግን ስትራክቸራል ለውጥ መትቷል ብዬ ለመናገር አልችልም፤የፖሊሲ ለውጥ ያመጣ ለውጥ አይደለም ለውጡ፡፡

ቁም ነገር፡- በተለያዩ አጋጣሚዎች በምትሰጣቸው አስተያቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ መሆንህን እየተናገርክ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ከሚሉት ወገን ነህ፤ ለመጡት ለውጦች ግንባር ቀደም ሰው ዶ/ር አብይ ከሆኑ እየታዩ ላሉ ተግዳሮቶችስ ሀላፊነቱ የማነው?

ተክለ ሚካኤል፡- ጥያቄ የለውም፤ መንግስት እየታየ ላለው ችግር ሀላፊነት መውሰድ አለበት፤ግን አንድ ሰው ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ወይ ካልከኝ አይችልም ነው መልሴ፤ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል፤በአንድ ጊዜ ብዙ ሺ ችግር ያለባትን ሀገር አንድ ሰው ሊፈታው አይችልም፤እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ ቆርጠው ወደ ድሮው መንገድ በመሄድ ሀይል ወደመጠቀም ሊገቡ ይችላሉ የሚል ፍርሃት አለኝ፤ አሁን በቅርቡ እየታየባቸው ያለው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያ ነው፤ ሲቆጡ ታያለህ፤ ሊያስፈራሩ ሲሞክሩ ታያለህ፤የመንግስት ችግር እንዳለ ሆኖ እኛም ሀላፊነት መውሰድ ይገባናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላልቅ ስኬቶችን ይዞ ጊዜ መስጠት ለሁላችንም ይጠቅማል እላለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የስደተኞችን ጉዳይ በጥብቅና መያዝ ብቻ ሳይሆን ቤትህ ውስጥ ሁሉ በማሳደር ብዙዎችን እንደምትታስተናግድ አውቃለሁና ይሄ ልምድ ከምን መጣ ?

ተክለ ሚካኤል፡-ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በግ ታርዶ ብቻውን የሚበላ ሰው የለም፤ የእኛ ባህል እኮ እዚህ ሀገር ካለው የተለየ ነው፤ እዚህ ሀገር ለምሳሌ መሰላል ካለህ የብቻህ ነው፤ መዶሻ ለካለህ የራስህ ነው፤ ሌላውም ራሱን ገዝቶ ቤቱ ያስቀምጣል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እንደዚህ አይደለም፤እኔ እንደውም እኛ ቤት አንድ የታወቀ አፊፍ መጥረቢያ ነበር፤አባታችን ያንን መጥረቢያ በጣም ነበር የሚወደው፤ እና የጎረቤት ሰዎች አባታችን ጥሩ መጥረቢያ እንዳለው ስለሚያውቁ ለመዋስ ይመጡ ነበር፤ እሱ ደግሞ እንዳያበላሹት በማለት ራሱ ነበር ሄዶ እንጨታቸውን የሚፈልጥላቸው፤በሀዘን ጊዜ፤ በደስታ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በጋራ ነው የምናሳልፈው፤ ልሂቃኑ አሁን በተለያየ ጊዜ እየመጡ በሚናገሩት ነገር አበላሹት እንጂ ህዝቡ እኮ የዋህ ነው፤ለእንግዳ ቅቤና እርጎ እየሰጠ ያሳደገን የነገሌ ቦረና ልጅ ነኝ፤ ስለዚህ እኔም እያደረግሁ ያለሁት ያንኑ ነው፤ በነገርህ ላይ እኔም እዚህ ሀገር ስመጣ በኢትዮጵያውን እርዳታ ነው ስራ ገኘሁት፤ መጀመሪያ ላይ የፅዳት ስራ ነው ያገኙልኝ፤ በኋላ ደግሞ በጋዜጠኛ ልዑል ከበደ አማካይነት ሴኩሪቲ ስራ ነው የገባሁት፤እኔም በተራዬ የተለያዩ ሰዎች አስቀጥሬያለሁ፤ አሉታዊው ነገራችን እየጎላ ስለሚነገር ነው እንጂ ብዙ ኢትዪጵያዊ ይረዳዳል፤ ተባብሮ ተከባብሮ የሚኖር ህዝብ ነው፤ስለዚህ ደግ ሆኜ ከሆነ ከኢትዮጵያ ህዝብ ነው የወረስኩት ነው የምለው፤

ቁም ነገር፡-በካናዳ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ነህ፤ ኮሚኒቲውም ምንድነው እየሰራ ያለው?

ተክለ ሚካኤል፡-ለረዥም ጊዜ የተዳከመ ነበር፤ በፊት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቶሮንቶ ውስጥ ወደ 2 ሚሊየን ዶላር ይመደብለት ነበር፤ ወደ 20 ሰላሳ ሰራተኞች ነበሩት፤ በተለያዩ ፕሮጅቶች እየሰራ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ካላፉት 7 እና 8 ዓመታት ወዲህ ግን ተዳክሞ ነበር፤አሁን አንድ ህንጻ አለው እሱን ብቻ ይዞ ይህ ነው የሚባል ስራ መስራት ያልቻለበት ጊዜ ነበር፤ባመት አንድ ቀን ነው የኢትዮጵያ ቀን እየተባለ ያከብራል፤ አሁን እንግዲህ አዳዲስ ሰዎች ተመርጠናል፤ የተሻለ ስራ  ለመስራት እንሞክራለን፤ህዝቡን አስተባብረን ለሀገርም የተሻለ ነገር ለመስራት እናስባለን፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይም የውይይት ፕሮግራሞችን እያዘጋጀን መረጃ ለመለዋወጥ እንጥራለን፤ ህዝቡ ስለ ሀገሩ በቂ መረጃ እንዲኖረው እንሰራለን፤ ለምሳሌ በቅርቡ  ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ በጌዲዮ ህዝብ ጉዳይ ላይ፤ ዶ/ር ዮናታን ተስፋዬ በአይደንቲቲ ዲተርምኔሽን ጉዳይ እንዲሁም ዶ/ር ሰሚርም እንዲሁ የተለያዩ ገዳዮች ላይ ውይይቶችን አዘጋጅተን አካሂዳናል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮችንም አዘጋጅተን ለእስረኞ ቤተሰቦች የገንዘብ እርዳታ እንዲያገኙ እናደርጋለን፤ ለካናዳ መንግስትም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ ስላሉ ነገሮች መረጃ እንሰጣለን፤መግለጫዎችን እነናወጣለን፡፡

ቁም ነገር፡-የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ምን መስላል?

ተክለ ሚካኤል፡-በጣም ደካማ ነው ለማለት እችላለሁ፤በንፅፅር ከነናይጄሪያና ፊሊፒንስ አንፃር ደካማ ነው፤ ከሱማሌ አንፃር እንኳ ካየኀኸው የትና የት ነው፤ እነርሱ የፖርላማ አባል ከማስመረጥ አልፈው የኢሚግሬሽን ሚኒስትሩ የሱማሌ ተወላጅ ነው፡፡ በ16 ዓመቱ የመጣ ልጅ ነው፡፡ ኮሚኒቲው እንደዚህ አይነት ብሪላንት ሰዎች ካሉ ማስመረጥ ይቻላል፤ በመገናኘትና መተባበር ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ኤርትራውያን ራሳቸው ከእኛ የተሻለ ይንቀሳቀሳሉ፤ባለፈው እንደውም አንዲት ኤርትራዊት ለከተማው ምክር ቤት ለማስመረጥ ሲሞክሩ ነበር፤እኛም እንደዚህ አይነት ነገሮችን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

ቁም ነገር፡-ሀገራችን ለውትጥ ላይ ነች፤ አንተ እዚህ ሆነህ ብዙ ኢትዮጵያውያንን እያገለገልክ እንደሆነ እረዳለሁ፤ ግን በተወሰነ ደረጃ ወደ ሀገር ቤት መጥተህ በሙያህ የመስራት እድል ሊኖር የሚችል መስልሃል?

ተክለ ሚካኤል፡- ይመስለኛል፤ ሀገር ለመርዳት ግን የግድ ሀገር ቤት መሄድ ላያስፈልግ ይችላል፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፤ በተለይ የህግ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን ለመስጠት ማንዋሎችን ለማጋጀት ብዙ መንገዶች አሉ፤ ሀገርንና ወገንን ለመርዳት፤በመመላለስም መስራት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት እየፈለጉ ቢሮክራሲው አላሰራ ላላቸው ሰዎች በሩ ቢከፈት በጣም ጠቃሚ ነው እላለሁ፤ ስለዚህ ይሄ ሙስናውና ቢሮክራሲው አደብ ቢበጅለት ብዙ ሰዎች ለመምጣት የሚፈልጉ ይመስለኛል፤ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ሰው ሲነግረኝ  አንድ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ሄዶ ወንዝ በየዓመቱ እየሞላ ሰው ይወስዳል እና፤ እዛ ወንዝ ላይ ድልድል እንስራላችሁ ስንል የአካባቢው አመራሮች ለእኛስ ስንት ስንት ነው የምትሰጡን? አሉን ብሎ ሲነግረኝ ነበር፤ለእኛ ካልሰጠኸን ስራ አትሰራም የምትባልበት ሀገር መሆኑ ያሳዝናል፤ ያም ሆነ ይህ ግን በእኔ ደረጃ ላደርግ የምችለው አስተዋፀኦ ትንሽ ሊሆን ይችላል፤ ግን የግድ እዛ መሄድ አይጠበቅብኝም፤እዚህም ሆኜ በተለይ በህጎቹ ውስጥ ያሉትን አሳሪ ድንጋጌዎች ላይ ሀሳብ መስጠት የምችል ይመስለኛል፤

ቁም ነገር፡-     ከሙዚቃ የማን  አድናቂ ነህ?

ተክለ ሚካኤል፡-ጥላሁን ገሠሠ፤ጂጂ ዘሪቱ ከበደ ይመቹኛል፤

ቁም ነገር፡-      አመሰግናለሁ፤

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe