በወላይታ አለመረጋጋት ቢያንስ አስር ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

ባለፈው እሁድ ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች በተያዙ ሰዎች ሰበብ በተከሰተ አለመረጋጋት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ።

ዞኑን በክልልነት ለማደራጀት ከተቋቋመው ሴክሬታሪያት ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህግ ባለሙያዎችና የአገር ሽማግሌዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነው ችግሩ የተከሰተው።

በተለይ አለመረጋጋቱ ከፍተኛ ነበር በተባለባትና ከሶዶ ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦዲቲ ከተማ የሟቾች ቁጥር ከሰባት በላይ እንደሆነና በሶዶም ሰዎች መገደላቸውን ከሆስፒታሎችና ከአካባቢው ነዋሪዎች አገኘሁት ያሉት መረጃን ጠቅሰው የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ማቴዎስ ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሶዶ ሦስት ሰዎች እንደሞቱና በቦዲቲም ሌሎቹ እንደተገደሉ አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል። ከሰበሰቧቸው መረጃዎች ተረዳሁት ያሉት አቶ ማቴዎስ ብዙዎቹ በእድሜ ታዳጊ እንደሆኑና “መንግሥት ያለ አግባብ ኃይል ተጠቅሟል” ሲሉም ወንጅለዋል።

“የሚያሳዝነው እነዚህ ልጆች ጠንከር ያለ አርጩሜ ይበቃቸው ነበር። አስለቃሽ ጋዝም መርጨት ይቻል ነበር። አንዳንዶቹ እየሮጡ አሳዶ መተኮስ በጣም የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር የግለሰቦቹ ሕይወት የጠፋው መሳሪያ ለመንጠቅ ባደረጉት ትንቅንቅ ነው ማለታቸውን ጠቅሰው ይሄ ትክክል እንዳልሆነ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ስለግለሰቦቹ ሞት ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ውስጥ ከትናንት በስቲያ በጥይት ተመትቶ የመጣ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ አልፏል።

ግለሰቡ የ30 ዓመት እድሜ እንደሆነ የሚናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያ ሦስት ግለሰቦችም በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የ22 ዓመት እድሜ ያለው አንደኛው ግለሰብ በጥይት አንገቱ ላይ ተመትቶ በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኝ ሲሆን በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም እኚሁ የጤና ባለሙያ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሌላኛው የ25 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን እግሩ ላይ በጥይት ተመትቶ ደም ስሩም በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል። በተጨማሪም ሌላኛው ህመምተኛ በጥይት ሳይሆን በዱላ ከፍተኛ ድብደባም ደርሶበታል ብለዋል።

ከፅኑ ማቆያ ህሙማን ክፍል በተጨማሪም ሦስት ግለሰቦችም በጥይት ተመትተው የአጥንት ህክምና ክፍል ውስጥ ተኝተው እየታከሙ ነውም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና አድርገው የተመለሱ ወደ አምስት ሰዎች መኖራቸውንም እኚሁ ባለሙያ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን ሆስፒታል ውስጥ መጥቶ ህይወቱ ያለፈ ባይኖርም በቦዲቲ አምስት ሰዎች መሞታቸውን መረጃ ማግኘታቸውን እንዲሁም በሶዶ ከተማም ውስጥ ሆስፒታል ሳይመጡ በጥይት የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የንግድ እንቅስቃሴዎችም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ገልፀው ሶዶ ብትረጋጋም በቦዲቲ መጠነኛ ውጥረት እንዳለ አስረድተዋል።

የሶዶ ከተማ ፀጥ ረጭ እንዳለችና ከመከላከያና የፀጥታ ኃይሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በስተቀር ምንም እንደሌለ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ነዋሪ አስረድተዋል።

ምንም እንኳን ከትናንትናው ጋር ሲነፃፀር አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም ስጋቶች እንደነገሱ ይኸው ነዋሪ ይናገራሉ።

እሳቸው ሰማሁ ባሉት መረጃ በቦዲት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን በሶዶ ደግሞ የሶስት ሰዎች ሕይወት አልፏል ብለዋል። በዛሬው ዕለት በሶዶ እንዲሁም በቦዲት ከተሞች የቀብር ስነ ስርአቶች እየተካሄዱና ነዋሪው ለሃዘን ተቀምጠዋልም ብለዋል።

ባለው የመንገድ መዘጋት የተነሳ ከአዲስ አበባ ወደ ቦዲቲ ለመሄድ ያልቻለው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የቦዲቲ ከተማ ነዋሪም አንድ አክሊሉ የተባለ ጓደኛው በጥይት መገደሉን ተናግሯል። አክሊሉ በሃያዎቹ እድሜ ላይ የሚገኝ እንደሆነም ለቢቢሲ አስረድቷል።

ከትናንት ጀምሮ ለደቡብ ክልል ፖሊስና ለሰላም ፀጥታ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ደጋግመን በመደወል ቀጠሮ ቢሰጡንም ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም።

የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በወላይታ ዞን የተከሰተውን አለመረጋጋት በተመለከተ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች 10 መሆናቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ትናንት ገልጸው እነሱም “የክልል እንሁን ጥያቄ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዳይፈታ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች” መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይል እነዚህን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ “መንገድ የመዝጋትና ግርግር የመፍጠር አዝማሚያ መታየቱን” ገልጸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውንም ኃላፊው አቶ አለማየሁ ትናንት ተናግረው ነበር።

ለግጭቱ መነሻ ምክንያት የሆነው በዞኑ የተቋቋመው የክልል ምስረታ ሴክሬታሪያት ካውንስል አማካሪ ቦርድ አባላት፣ በሕግ ኮሚቴው የተዘጋጀውን የሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ እንዲወያዩ ስብሰባ ላይ የተጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ነው።

ከታሰሩትም ውስጥ የዞኑ አስተዳዳሪ ዳጋቶ ኩምቤ፣ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስ፣ የዞኑ ከፍተኛ አመራር ወ/ሮ እቴነሽ ኤልያስ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጎበዜ አበራ፣ የወላይታ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት ኤልያስ ይገኙበታል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአገር ሽማግሌዎች አቶ ሰይፉ ለታና አቶ ዳንኤል ደሳለኝ፤ የንግድ ምክር ቤት ዋናና ምክትሉ አቶ በተላ ቦረናና አቶ አክሊሉ ደስታ፤ የመብት ተሟጋቾችና ከሕግ ባለሙያዎች መካከል አቶ አሸናፊ ከበደ፣ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ አቶ ተከተል ለቤና በአጠቃላይ 26 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላችውን አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል።

እሳቸውም አባል የሆኑበት የዚህ ሴክሬታሪያት አባላት መታሰር እንዳሳዘናቸው ጠቅሰው ግለሰቦቹን ከመፍታት በተጨማሪ፣ የሞቱ ግለሰቦችንም አሟሟት ነፃና ገልልተኛ የሆነ አካል ሊያጣራ ይገባል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15/2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የክልሉን መንግሥት ለማደራጀት የሚያስችል ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤትም እንዲቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንዲከናወኑም በዚሁ ወቅት ወስኖ ነበር።

ምንጭ፡ ቢቢሲ

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe