በጣሊያን ኤምባሲ ለ29 ዓመታት ለተጠለሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት መንግሥት ምሕረት እንዲያደርግላቸው ተጠየቀ

የደርግ መንግሥት በ1983 ዓ.ም. ሲወድቅ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ከነበሩት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩት ሌተና ጄኔራል ሀዲስ ተድላ፣ ላለፉት 29 ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው የቆዩ መሆናቸውን በማስታወስ መንግሥት ምሕረት አድርጎላቸው ቀሪ ሕይወታቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያሳልፉ የቀድሞ ባልደረቦቻቸው በደብዳቤ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ሁለቱ አዛውንቶች በአሁኑ ጊዜ ዕድሜያቸው ከ80 በላይ መሆኑን የጠቆሙት ባልደረቦቻቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይለ ሚካኤል ብሩና የምድር ጦር አባል የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳን የተሸነፈ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩና አሸንፎ ደርግን የተካው መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ቢሆንም፣ ላለፉት 29 ዓመታት ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና እንቅስቃሴ ተለይተው መኖራቸው የሚበልጥ ቅጣት የለም፡፡

ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ወቅቱ ዓለምን አንድ ያደረገው የኮሮና ወረርሽኝ የሚባል መቅሰፍት ከፍተኛ ሥጋት የሆነበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት እነዚህ ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸውን አዛውንቶች ዕድሜ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የወረርሽኙን ሥጋት በማገናዘብና ከሰብዓዊነት አንፃር ብቻ ተመልክቶ መንግሥት ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሁለቱም አዛውንቶች ዕድሜያቸው ከመግፋቱ ጋር ተያይዞ በደም ግፊት፣ በስኳርና በተዛማጅ ሕመሞች ተጠቂ በመሆናቸው በቤተሰብ፣ በወዳጅ ዘመድና በቅርብ ሐኪም ክትትል የሚያስፈልጋቸው ስለሆኑና ላለፉት 29 ዓመታት በብቸኝነት መኖራቸው የፈጠረባቸውን የሥነ ልቦና ጭንቀት ከግንዛቤ አስገብቶ፣ መንግሥት በቅን ልቦና ምሕረት እንዲያደርግላቸው ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

ምንም እንኳን የጣሊያን መንግሥት ላለፉት 29 ዓመታት ጥገኝነት ሳይሆን መጠለያ ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግላቸው የነበረ ቢሆንም፣ በጣሊያን ሕዝብ ላይ ኮሮና ባስከተለው ከፍተኛ ጉዳት ጥልቅ ሐዘን ውስጥ በመግባቱ፣ ለአዛውንቶቹ የሚደረገው ድጋፍና ትኩረት እንደ ቀድሞው ሊሆን አይችልም የሚለው እንዳሳሰባቸውም ባልደረቦቻቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የወረርሽኝ ዘመን ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ወንድም ሕዝብ ድጋፍ እንዲያገኝ ዓለምን በማሳሰብ ከፍተኛ ጥረት በምታደርግበት አስጨናቂ ወቅት፣ እነዚህ ሁለት አዛውንቶች ለ29 ዓመታት ከሰው እንዳይገናኙ ተገልለው ተቆርቋሪ ወገንና መንግሥት እንደሌለው አስታዋሽ ማጣታቸው ስላሳዘናቸውና መንግሥትም እንደማያሳፍራቸው በመተማመን ጥያቄውን እንዳቀረቡም በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አዛውንቶች ምንም እንኳን ወደ መጨረሻው አካባቢ ወደ ፖለቲካው የተቀላቀሉ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ዕድሜያቸውን በውትድርናው መስክ ተሰማርተው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ መኖራቸውንም ባልደረቦቻቸው አስረድተዋል፡፡ ሁለቱም አዛውንቶች በወጣትነታቸው ወቅት በ1956 ዓ.ም. የሶማሌ መንግሥት ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ ቶጎ ውጫሌ ላይ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲያደርስ ባደረጉት ተጋድሎ ተመትተው፣ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው መትረፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ የአየር ወለድ ሠራዊት አባል የነበሩ ሲሆን፣ ሌተና ጄኔራል ሀዲስ ተድላ ደግሞ የአየር ኃይል አባልና አብራሪ እንደነበሩም በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በቆየው አኩሪ የይቅርታ ዘመን ተሻጋሪ ባህልና በሰብዓዊነት ዕሳቤ ብቻ እነዚህ አዛውንቶች የሰቀቀን ኑሯቸው አብቅቶ ምሕረት ተደርጎላቸው የቀራቸውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ፣ በእግዚአብሔርና ዘንድ የሚወደደውን ይቅርታና ምሕረት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት አሁን በይቅር ባይነት መንፈስ በመተሳሰብ፣ በመመካከርና በመደመር የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት፣ እንዲሁም የዓለምን መኖር እየተፈታተነ ያለውን አስጨናቂ ጊዜ ይቅር በመባባል፣ ይህንን ክፉ ዘመን እንደ አንድ ቤተሰብ በፀሎትና በአምላክ ቸርነት ማለፍ ሲቻል ብቻ በመሆኑ፣ መንግሥት ለእነዚህ አዛውንቶች ምሕረት ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አዛውንቶች በሌሉበት በተመሠረተባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀልና 15 ዓመታትን በፈጀው ክርክር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ፣ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው (በሕይወት የሉም)፣ ከሻለቃ መላኩ ተፈራን ጨምሮ 16 ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ቢሆንም፣ በወቅቱ ርዕሰ ብሔር ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የሞት ቅጣቱ ወደ ዕድሜ ልክ ተቀይሮና በወንጀል ሕጉ ደግሞ ዕድሜ ልክ የተፈረደበት ወንጀለኛ 20 ዓመታት በእስር ካሳለፈ በምሕረት እንደሚፈታ በመደንገጉ ምክንያት፣ 20 ዓመታት በእስር ካሳለፉ በኋላ ምሕረት ተደርጎላቸው በ2004 ዓ.ም. ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ሁሉም ባለሥልጣናት የተመሠረተባቸው ክስ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቢሆንም፣ ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸው አይዘነጋም፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe