‹በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደስተኛ ነኝ › አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ

የዛሬ 25 ዓመት በወጣችው ቁም ነገር መፅሔት ቁጥር 1 ላይ ከወጡ 8 ታዋቂ ሰዎች መሀከል ሁለቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ናቸው፡፡/አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁንን ገሠሠና የድሆች አባት አለባቸው ተካ/ ስድስቱ ታዋቂ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች በእግዚአብሔር ፈቃድ  በሰላምና በጤና በሙያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ከአምስቱ ባለሙያዎች ጋር (አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ፤ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፤ ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያ ሳምሶን ማሞና ላፎንቴኖች ብርሃኑ ተዘራና ታደለ ሮባ)ከ25 ዓመታት በኋላ 25 ልዩ ጥያቄዎች አቅርበን አዝናኝ ምላሾችን ሰጥተውናል፤

የዛሬ 25 ዓት በቁም ነገር መፅሔት ላይ ለወጡ እንግዶች የቀረቡ 25  ጥያቄዎች

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት ቁም ነገር መፅሔት ላይ የወጣው ቃለ ምልልስ የሰጠሽው የት ቦታ ነው?

ሙሉዓለም፡- ውይ አላስታውስም፤ እኔ እኮ አይደለም የቀድሞውን ትላንት ቁርሴን ምን እንደበላሁ የማስታውስ ሰው አይደለሁም፡፡ ግን የት ነበር በእናትህ?

ቁም ነገር፡- ለም ሆቴል አካባቢ ሰራዊትና ሙሉዓለም ፕሮሞሽን የሚባል ቢሮ ነበራችሁ፤ እዛ ነው፡፡

ሙሉዓለም፡- ውይ ልክ ነህ፤

ቁም ነገር፡- ስለ ቁም ነገር መፅሔት ሲነሳ ቶሎ ብሎ ወደ አዕምሮሽ የሚመጣው ነገር ምንድነው?

ሙሉዓለም፡- አንተ ነሃ!ታምራት ቁም ነገር ብዬ ነው ስልኬ ላይ ራሱ የመዘገብኩህ፡፡ ይህን ያህል ዓመት ቀጥ ብለህ ይዘህ የሰራኸው ስለሆነ አንተን ነው የማስታውሰው፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ  25 ዓመት በነበረችው ሙሉዓለም ታደሰና በአሁኗ ሙሉዓለም መሀከል ምን ልዩነት አለ? በምን ጉዳይ?

ሙሉዓለም፡- ረጅም ጊዜ ስለሆነ መብሰል አለ፤ መርጋት አለ፤ ማስተዋል አለ፤ መረጋጋት ድሮም ጀምሮ አለኝ፤ አሁን ግን የበለጠ ሆኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- መርካቶ ውስጥ ቦምብ ተራ የሚባል ቦታ አለ፤ምንድነው የሚሸጠው?

ሙሉዓለም፡- መቼም ቦምብ ነው የሚሸጠው እንዳትለኝ? ስሙ ራሱ እንዴት እንደወጣለት አላውቅም፤ ግን ቦምድ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤መጥፋት ያለበት ነገር ነው ቦምብ ከሀገራችን፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት ያሳካሽው ወይም ወደፊት ልታሳኪው የምትፈልጊው ነገር ምንድነው?

Artist Mulalem Taddess

ሙሉዓለም፡- በ25 ዓመት ውስጥ ጠንክሮ በዚህ ሙያ ውስጥ መቆየቴ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሙያውን በዲስፒሊን ይዞ ህዝቡን አክብሮ ለመቆየት መቻል ትልቅ ነገር ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት  ከመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሀከል እንኳንም መጣ የምትይው ምንድነው?

ሙሉዓለም፡- የሞባይል ስልክና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው፡፡ በስልክ ብዙ ነገሮችን መስራት ተችሏል፤ትናንሽ ንግዶችን ኦን ላይን መስራት ችለዋል ወጣቶች፡፡ በስልክህ ብቻ ከቤትህ ሳትወጣ ብዙ ስራዎችን የሚሰሩ ልጆች ተፈጥረዋል፡፡ በፊት አንድ ነገር ለመግዛትና ባንክ ሄደን ገንዘብ ማውጣት ነበረብን፤ አሁን ግን ገንዘብ በእጅ ስልክ ብቻ ማዛወር ይቻላል፡፡ ኢንተርኔት በመጠቀምም ዛሬ ማንኛውም ሰው ቴሌቪዥን ጣቢያ ሄደው አሳዩኝ አይሉም፤ራሳቸውን ቀርፀው በራሳቸው ገፅ ላይ ማስተዋወቅ ይችላሉ፡፡ ህይወትን በጣም አቅለውታል እነዚህ ሁለት ነገሮች፡፡ ሌላው ኤአይ ወደ መጥፎ ነገር እንዳይሄድብ እሰጋለሁ እንጂ በተለይ በህክምና ዘርፍ ላይ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በጣም የሚያስደስት ነው፤ ስራንም በማቅለል በኩል ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ባለፉት 25 ዓመታት በሞት ካጣናቸው ሰዎች በጣም ያስደነገጠሽ/ያሳዘነሽ ማነው?

ሙሉዓለም፡- በጣም ብዙ የኪነጥበብ ሰዎች ሲያልፉ ደንግጫለሁ፤ አዝኛለሁ፡፡ ማዲንጎ አፈወርቅና እንደ ኩራባቸው ደነቀ ሞት ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ፡፡ ከኩራባቸው ጋር እኮ አሜሪካ በእረኛዬ ድራማ ሄደን እንደመጣን ነው ያረፈው፤ የሁለቱም ሞት ድንገተኛ ስለነበር አስደንግጦኛል፡፡ የኤልያስ መልካም ሞት በጣም አሳዝኖኛል፤ያው መታመሙን ሁላችንም እናውቅ ነበር፡፡ ሞት ምንጊዜም ያስደነግጣል፡፡

ቁም ነገር፡- ውጭ ሀገር ካየሻቸው ነገሮች ምነው ይሄ ነገር እኛ ሀገር በሆነ የምትይው ነገር ምንድነው??

ሙሉዓለም፡- ለምሳሌ አሜሪካ የሄድን ጊዜ ቦታና ስም ማስታወስ ላይ ደካማ ነኝ እንጂ አንድ ቴአትር ለማየት ተጋብዘን የገባንበት ቴአትር ቤት ነበር፡፡ የዳዊትና ኦሪዮንን ታሪክ ላይ የተመሰረተ ቴአትር ነበር፤ እና ስንገባ ጀምሮ የመድረኩን ግዝፈት ስንመለከት ምነው ይሄ  አይነት ቴአትር መድረክ እኛ ሀገር በኖረ ብያለሁ፡፡ እንዲህ አይነት መድረክ ላይ ምነው ሰርቼ ባቆምኩ ነው ያልኩት፡፡ የሚገርምህ መድረኩ ግዝፈት ብቻ ሳይሆን በፊልም ሁሉ የጎሊያድን ምስል በ3ዲ ያመጡታል፤ዝናብ ሲዘንብ ተመልካች ላይ ይዘንባል፤ ስሜቱ እንዲኖርህ ማለት ነው፡፡ በረዶ ሲወርድም ይነካሃል፤ ይህንን መድረክ ለሀገሬ ተመኝቻለሁ፡፡ ሌላው ባቡር በጣም ነው የምወደውና፤ ፈጣን ባቡር ከከተማ ከተማ የሚከንፉ ሳይ ሀገሬ ላይ መቼ ነው የማየው እል ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- ነገን የማወቅ ችሎታ ከሚሰጥሽና የትላንትናውን ነገር መቀየር ብትችይ የቱን ትመርጫለሽ?

ሙሉዓለም፡- በጣም ከባድ ጥያቄ ነው ታሜ፤ ግን እኔ ባለፈ ነገር የምቆጭ አይነት ሰው አይደለሁም፤ስለዚህ  ባለፈ ነገር ላይ ጊዜ አላጠፋም፤ነገንም ለማወቅ የምጓጓ ሰው አደለሁም፤ ምክንያቱም ነገ አለማወቃችን ነው በተስፋ እንድኖር የሚያደርገን፤ ይሄ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ግን ለጥያቄህ የግድ አንዱን ነገር ምረጭ ካልከኝ ያለፈ አንድ ነገርን መለስ ብዬ ባስተካክል ይሻለኛል፡፡

ቁም ነገር፡- ፆታሽን መርጠሽ የመወለድ እድል ቢሰጥሽ አሁን ወንድ ወይም ሴት ሆነሽ መወለድ ትመርጫለሽ?

ሙሉዓለም፡- ሴትነቴን በጣም ነው የምወደው፤ ስለዚህ በዚሁ ነው ሴት ሆኜ የምቀጥለው፡፡ ለውጥ አይኖርም ታሜ፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት በዚህ ሙያ ውስጥ ባትገቢ ኖሮ ምን ሙያ ላይ ትገኚ ነበር?

ሙሉዓለም፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ለህክምና ሙያ የተለየ ስሜት ነበረኝና ሀኪም ልሆን እችል ነበር፡፡ ያው የህክምና ሙያ ትምህርት ይፈልጋል፤ ጊዜም ይወስዳል፤ ይህንን ስል የሰማ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰለህ? አሁን እኮ የኤአይ ቴክኖሎጂ መጥቷል፤ ሐኪም ለመሆን የግድ ሰባትና አስር ዓመት ዩኒቨርሲቲ መማር እየቀረ ነው፤ የፈለግሽውን የህክምና አይነት ቤትሽ ሆነሽ መማር የምትችይበት ሁኔታ መጥቷል ብሎ አስቆኛል፡፡

ቁም ነገር፡- በመጀመሪያ የመድረክ ስራሽ የተሰጠሽ የማትረሽው አበረታች ወይም አሳዛኝ አስተያየት ምንድነው? ማነው የሰጠሽ?

ሙሉዓለም፡- የመጀመሪያ ስራዬ የቬኒሱ ነጋዴ ቴአትርን ለመስራት ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተጋብዤ ነበር፤ የፖርሺያን ገፀባህሪ ነበር የምሰራው፤ ቀደም ሲል ይህቺን ገፀባህሪ የሰራችው ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ነበረች፡፡ ‹ይህችን አንድ ፍሬ ህጻን ልጅ አምጥተው መድረኩን ሊጫወቱበት ነው› ብለው የሆኑ አርቲስቶች እዛው ፊት ለፊቴ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ የቴአትሩ አዘጋጅ አቶ ሳህሉ አሰፋ ነበሩ፤ ደበበ እሸቱ ነው እኔን ሀገር ፍቅር መጥቼ እንድሰራ ያደረገኝ፤ እና ያንን ሲሰማ ደበበ በፍፅም ስሜትሽ አይነካ፤ ቦታ እንዳትሰጪ ለእዚህ አይነት አስተያየት፤ ብሎ ያረጋጋኝ ደበበ ነው ከጋሽ ሳህሉ ጋር ሆኖ፡፡ ደበብ የሻሎክን ገፀ ባህሪ አብሮኝ የሚጫወት ሰው ነው፡፡ ጋሽ ሳህሉ እንደውም አንድ አርቲስት በግሉ መጥቶ ‹እንዴት እቺን ልጅ የፖርሺያን ያህል ገፀ ባህሪ ትሰጣታለህ?› ብሎ ሲጠይቃቸው እንደውም ‹እሷ ናት በትክክል የምታመጣት፤ምክንያቱም ፖርሺያ ገና የ16 ዓመት ልጅ ነች፤ ስለዚህ ‹እውነተኛዋን ፖርሺያን አግኝቻለሁ› ብለው ነው ያሰሩኝ፡፡ ይሄ ነገር ለእኔ በጣም የሚያወድመኝ አስተያየት ነበር፤ እነዚህ ትላልቅ ሰዎች ባያበረታቱኝ ኖሮ ላልቀጥል እችል ነበር፡፡ የሚገርምህ ስራው ሲታይ ግን ከህዝቡ በላይ አድናቆት የመጣው ‹አትችለውም› ካሉት አርቲስቶች ነበር፡፡ መጥተው ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡ ብዙ ጊዜ በምሰራው ስራ ሰዎች በሚነቅፉኝ ጊዜ በስራ ነው የማሸንፋቸው፤ ቃል አላወጣም፤

ቁም ነገር፡- ዕድለኛ ሰው ነኝ ወይስ ዕድለ ቢስ ነኝ ብለሽ ታስቢያለሽ?

ሙሉዓለም፡- በጣም እድለኛ ሰው ነኝ፡፡ ልጅ ሆኜ መተሃራ እያለሁ የቢንጎ ጨዋታ አለ፤ እዛ ሄጄ ስጫወት የምትጠራው ቁጥር አለ፤ በእዛ ቁጥር አማካኝት የሚወጣ እጣ አለ፤ በግ፤ ልብሶች፤ ሸሚዞች ልዩ ልዩ ሽልማቶች አሉ፤ እኔ እዛ ካለሁ ብዙ ጊዜ እበላቸዋለሁና ሰላም ብለው ነበር የሚጠሩኝና ሰላምን አታምጧት እዚህ ይሉ ነበር፡፡ በህይወቴም ብዙ ፈተና ቢያጋጥመኝም በመጨረሻ ግን የማሸንፈው እኔ ነኝ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ በኩል ይጠብቀኛል፡፡ ህይወት የምንፈልገውን ብቻ አይደለም የምትሰጥህ፤ የሚያስፈልግህን ጭምር ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ስራ ስትጀምሪ ሞዴል አድርገሽ ከምታስቢያቸው ሰዎች ጋር አንድ መድረክ ላይ አብረሽህ የመስራት አጋጣሚ ገጥሞሸል? ከማን ጋር?

Artist Mulalem Taddess

 

ሙሉዓለም፡- በጣም በህይወቴ ዕድለኛ ሰው ነኝ ከምልባቸው አጋጣሚዎች መሀከል አንዱ ይሄ ነው፡፡ ወደ መድረክ ስመጣ በጣም ከማደንቃቸውና ከማከብራቸው አርቲስቶች ጋር አንድ መድረክ ላይ አብሬ በተደጋጋሚ የመስራት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ ደበበ እሸቱ፤ ጌትነት እንየው፤ተፈሪ ዓለሙ፤ ጀማነሽ ሰለሞን፤ ፍቃዱ ተ/ማርያም፤ ሲራክ ታደሰ፤ ጀምበሬ በላይ ስንቱን ልጥቀስልህ? በጣም ዕድለኛ ነኝ የምልህ ለዚህ ነው፤ልዩ ስሜት አለው ከእነዚህ ሰዎች ጋር አብሮ አንድ መድረክ ላይ መቆም፡፡በእዛ ላይ አሜሪካ ሀገር ቴአትር ለማሳየት የሄድኩት ገና እንደተቀጠርኩ ነው፡፡ ያንን ዕድል ብዙ ሰው አላገኘውም፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት በሀገራችን ላይ የሰላም እጦት ነበረ፤ አሁንም  ችግራችን ነው፤ ከዚህ ለመውጣት ሀሳብ አዋጭ ብትባይ ምን ትያለሽ?

ሙሉዓለም፡- እግዚአብሔር ሀገራችን ሰላም ያድርግልን ነው የምለው፡፡

ቁም ነገር፡- ባንክ ያለሽ ገንዘብ ተወርሷል ብትባይ ምን ታደርጊያለሽህ?

ሙሉዓለም፡- ምን አደርጋለሁ? መፀለይ ነዋ እንዲመለስ፤ እኔ በህይወቴ በምን አምናለሁ መሰለህ፤ በፀሎት፤ ምንም ነገር ሲገጥመኝ ለእሱ ነው የምነግረው፤ እና ይሳካል፡፡ ባለፉት  25 ዓመታት ማሸነፊያ መሳሪያዬ ፀሎት ስለሆነ ወደ እሱ ነው የምሄደው፡፡ እንደምታውቀው በጣም ታታሪ ሰራተኛ ነኝ፤ ችግር ሲገጥመኝ ግን ወደ እሱ ነው የምሄደው፡፡ እግዚአብሔር የየዋሆች አምላክ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሲበዛ የዋህነት ያጠቃኛል፤ ለዛ ይመስለኛል ፀሎቴን ይሰማል፡፡ በፀሎት አምናለሁ፡፡ስለዚህ በፀሎት አስመልሰዋለሁ፡፡ እንደውም እጥፍ አስደርጌ አመጣዋለሁ፤

ቁም ነገር፡- በተለምዶ የሴት ወይም የወንድ የሚባሉ ስራዎች አሉ በማህበረሰበችን፤ ከቤት ውስጥ የወንድ ስራዎች ምን ትችያለሽ?

ሙሉዓለም፡- እኔ እኮ ሁሉንም ነገር መድረክ ላይ መስራት እችላለሁ፤ አርቲስተ እኮ እንደዛ ነው፡፡ እንደውም ወንድ ሆኜ የሰራሁት ስራ አለ፡፡ ቅድም ያልኩህ የቬኒሱ ነጋዴ ላይ ያለችው ፖርሺያ እኮ ሴት ብትሆንም ራሷን ቀይራ ወንድ ጠበቃ ሆና ነው የምትሰራው፡፡ ቡትስ ጫማ አድርጌ፤ ድምፂን ቀይሬ፤ ፂም አድርጌ ነው ባሌን ለማስፈታት እዛ የምመጣው፡፡ ያንን በብቃት ተወጥቻለሁ፡፡ በቴአትር ሙያ የሴት የወንድ የሚባል ስራ የለም፡፡ በፊልምና በቴአትር ሙያ በአብዛኛውን የምታገናቸው የቴአትር አዘጋጆችና የፊልም ዳሬክተሮች ወንዶች ናቸው፡፡ በወንዶች የተያዘ ሙያ ነው ልትለው ትችላለህ፤ ሴቶች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ እኔ ግን በቴአትር ዝግጅቱም በፊልም ዳሬክቲንጉም በፕሮውዲውሰርነትም የሰራኋቸው ስራዎች አሉ፡፡ ድርሰት አንድ ፊልም ላይ ተሳትፊያለሁ፤ ስክሪፕትም ማዳበር እችላለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ ከወንድ ከሚባሉት ስራዎች ሸክም አልችልም፤ ረጅም የእግር ጉዞም አልወድም፤

ቁም ነገር፡- የዛሬ 25 ዓመት በሰጠሽው ቃለ ምልልስ ላይ የሚከተለውን መልሰሽ ነበር፤

(ከኢትዮጵያ መሪዎች አግቢ ብትባይ ማንን ታገቢያለሽ? ስትባይ አፄ ቴዎድሮስን ብለሽ ነበር፤ አሁን ለውጥ አለ?)

ሙሉዓለም፡- አፄ ቴዎድሮስ እኮ ያኔም ጀግና ናቸው፤ አሁንም ጀግና ናቸው፤ ያው ነው፤ ለውጥ የለም፤ አሁንም ከእሳቸው ጋር ነኝ/ሳቅ/፡፡

ቁም ነገር፡- እስከዛሬ ሰምተሽ ለማመን የተቸገርሽው ዜና/ወሬ አለ?

ሙሉዓለም፡- ብዙ ነገር ትሰማለህ፤ ግን ከዜናዎች ሁሉ አሁን ድረስ  የሚገርመኝና እንዴት ሊሆን ይችላል ብዬ አስበው የነበረው ኮረና ልክ እንደመጣ ማንም ሰው በተቻለ አቅም ከቤቱ አይውጣ ሲባል በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ እንዴት ከቤት ሳንወጣ እንኖራለን ነበር ያልኩት፤ እንደውም ለአንዳንድ ስራ ከቤት  ስወጣ የከተማውን ጭር ማለት ስመለከት በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ ዛሬ ኮረና አልፎ ስናወራው ቀላል ይመስላል፡፡

ቁም ነገር፡- ከ25 ዓመታት ጉዞሽን የህይወት ታሪክሽን በመፅሐፍ ወይም በፊልም የምትፅፊ ይመስልሻል? ሰዎች ከእኔ ታሪክ ይማራሉ የምትይው ነገር አለ?

ሙሉዓለም፡- እንግዲህ ከ30 ዓመት በላይ ሆኖኛል በዚህ ሙያ ውስጥ፤ እና በዚ ሁሉ ዓመት ውስጥ ብዙ ታሪኮች አስደሳችም አሳዛንም ታሪኮች አልፈዋል፤ ህይወት ቅብብሎሽ ናት፤ አንዳችን ከሌላኛችን እየተማማርን ነው የምንቀጥለው፡፡ እና ታሪኬን በመፅሐፍ ለመፃፍ አንዳንድ ሰዎች ይጠይቁኛል፤ የወደፊቱን እግዚአብሔር ያውቃል፤ ለጊዜው ግን ሃሳቡ የለኝም፤

ቁም ነገር፡- ብሳተፍ ይዋጣልኛል የምትይው የስፖርት አይነት ምንድነው?

ሙሉዓለም፡- ድሮ ድሮ ልጅ እያለሁ ዋና በጣም ነበር የምወደው፤ እዋኝ ነበር፤ ከሰፈር ልጆች ጋር ሁሉ እንወዳደር ነበር፤ አሁን እንግዲህ የዕድሜም ሁኔታ አለ እንጂ ዋና እወዳለሁ፡፡ ትምህርት ቤት እያለሁ ደግሞ ቦሊቦልና እግር ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በተለይ የእግር ኳስ ችሎታዬን ያዩ ሰዎች  ብትጠነክሪ ለእቱ መላምቺ ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነት ሁሉ ትገቢ  ነበር ይሉኝ ነበር፡፡ ብሔራዊ ቴአትር ከገባሁ በኋላ ደግሞ ኤሮቢክስ እሰራ ነበር፤ የኪሊዮፓትራ ገፀባህሪን የሰውነት ቅርፅ ለማምጣት ኤሮቢክስ በጣም  እሰራ ነበር፡፡ ምናልባት ያን ግዜ የሰራኋቸው ስፖርቶች ይሆናሉ ለአሁኑ ጥንካሬዬ ያበቃኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- በአሁኑ ወቅት የዓለማችንን አነጋጋሪ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕን  ጠዋት ከቤትሽ  ስትወጪ በርሽ ላይ ድንገት ብታገኛቸው ምን ትያቸዋለሽ?

ሙሉዓለም፡- ለፕሬዚዳንት ትራምፕ አንድ ወቀሳ አንድ ደግሞ ሙገሳ እንዳለኝ ነው የምነግራቸው፤ እንግዲህ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ያልሆነ ነገር ተናግረዋል፤ ግን ስለ ኢትዮጵያ የሚናገሩትን ውሸት እንዲያቆሙ እንዲተው ነው የምጠይቃቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ነው ስለ ኢትዮጵያ የሚናገሩት፡፡ ሙገሳው ደግሞ ይሄ ከባህላችንም ከሃይማኖታችንም ጋር የማይሄደውን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በማገዳቸው ደስተኛ መሆኔን ነው  የምነግራቸው፡፡ ከዛ ሻይ የሚጠጡ ከሆነ ወደ ቤት እንዲገቡ እጋብዛቸዋለሁ/ሳቅ/

ቁም ነገር፡- በመጨረሻም ለእግዚአብሔር ሁለት ጥያቄ ጠይቂ ብትባይ ምን ትጠይቂያለሽ?

ሙሉዓለም፡- አንዱ ሀገራችንን እስከመጨረሻው ሠላም አደርግልን ነው የምለው፤ ሁለተኛው ደግሞ የልጄ ጤና፤ ስኬትና ደስታ ሁሉ የእኔም ስለሆነ የልጄን ጤና ጠብቀህ ባርከህ አቆይልኝ ነው የምለው፡፡

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe