ፕሬዝዳንት ትራውሬ ወደ ስልጣኑ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ከ18 በላይ የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባው ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ የስልጣን ሽኩቻው አሁን በርትቶ ስለመዝለቁ የሚያስረዱ መረጃዎች በስፋት እየተሰሙ ነው፡፡
የቀድሞው የቡርኪናፋሶው ፕሬዝዳንት ዳሚባ ትራውሬን ለማስገደል ሙከራዎችን አቀነባብረዋል በሚል ክስ ነው በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው የሚገልጹ ዜናዎች የተሰሙት፡፡ ካፒቴን ኢብራሂም ትራውሬ በ2022 የዳሚባን መንግስት በመፈንቅለ መንግስት አስወግደው ስልጣኑን መያዛቸው ይታወሳል፡፡ ዳሚባ ወደ ቶጎ ከሸሹ ጀምሮ የተለያዩ የመፈንቅለ መንግስት ሴራዎች በኢብራሂም ትራውሬ መንግስት ላይ ደርሷል፡፡
2026 አዲሱ ዓመት በገባ በሦስተኛው ቀን በሻምበል ኢብራሂም ትራውሬ ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞ እንደነበርም ታውቋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳሚባ ባለፈው ሳምንት በሮጎ ሎሜ በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ተነግሯል፡፡ በርግጥ ዋጋዱጉ በጉዳዩ ላይ ምንም የሰጠችው ማብራሪያ ባይኖርም ሰውየው ግን ስለመያዛቸው እና ወደ ቡርኪናፋሶም እንዲመለሱ መደረጋቸውን የሚገልጹ በርካታ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ፈርስት ፖስት ዘግቧል፡፡
ዳምቢ ቡርኪናፋሶን በሻምበል ኢብራሂም ትራውሬ ሃይል ከስልጣኑ እስኪነሳ ድረስ ለ8 ወራት ያህል በፕሬዝዳንትነት መርተዋል፡፡ ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላም ወደ ጎረቤት ሀገር ወደሆነችው ቶጎ ተሰደዋል፡፡
ከዚያ ጊዜ አንስቶ ዳምቢ በትራውሬ ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የግድያ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን የቅርቡም ከሁለት ሳምንት ከደማ በፊት የተደረገው የግድያ ሙከራ ነው ተብሏል፡፡ የቡርኪናፋሶ መንግስት ከሳምንታት በፊት የነበረው እቅድ መላ ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ለማስገባት ኢላማ ያደረገ እና በውጪ ሀገራት የተቀነባበረ ነበር ብሏል፡፡ ዓላማው ኢብራሂም ትራውሬ ላይ ግድያ በመፈጸም ሀገሪቱን ወደ ቀውስ መክተት ነበር ሲል የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በውጪ ሀገራት ያሉ አካላት በቡርኪናፋሶ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በገንዘብ በመግዛት ግድያውን ለማስፈጸም እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡
እንደ አብነትም የሀገሪቱ ነባር የአየር ሃይል አባል የሆነ ካፒቴን በዚህ ዘመቻ ተሳታፊ ለመሆን በቀጥታ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳሚባ 15ሺ ዶላር ተቀብሏል ተብሏል፡፡
የቡርካናቢ ባለስልጣናት አይቬሪኮስት እንዲህ አይነቱን ሴራ እየደገፈች ነው በሚል ይከሳሉ፡፡ አይቬሪኮስት የቀጠናው ዋነኛ የፈረንሳይ አጋር እና ወዳጅ ሀገር ናት፡፡
ምንም እንኳን ዋጋዱጉ ይህን ብትልም አቡጃን ግን እንዲህ አይነቱ ተግባር ላይ አለመሳተፏን ገልጻለች፡፡//

