በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናትን የሞት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያግዛል የተባለለት የመጀመሪያው የጡት ወተት ባንክ በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። ይህ የጡት ወተት ባንክ የተመረቀው፣ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ በፌዴራል መንግሥት እና በለጋሽ አካላት በ2.8 ቢሊየን ብር ወጪ ከተገነቡና ትናንት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለምረቃ ከበቁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በመሆን ነው።
አሠራሩ ከደም ልገሳ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፤ የጤና እና የደም ምርመራ ተደርጎላቸው ፍቃደኛነታቸውን በፊርማ ያረጋገጡ እናቶች ከልጆቻቸው የተረፋቸውን ትርፍ ወተት ይለግሳሉ። ወተቱ ከተሰበሰበ በኋላ «PiAstra» በተሰኘ ዘመናዊ ማሽን በሙቀት የማምከን (Pasteurization) ሂደት ውስጥ ያልፋል። በዚህም ተህዋስያኑ እንዲጠፉና ንጥረ ነገሩ ሳይቀንስ በሕክምና ማቀዝቀዣዎች ውስጥ ተከማችቶ ለሚፈልጉ ሕጻናት ይሰራጫል።
የጡት ወተት ባንክ በዓለም ላይ የ100 ዓመት ታሪክ ያለው ቢሆንም በአፍሪካ እስካሁን አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉት 8 ሀገራት ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት በይፋ በመጀመር ከአፍሪካ 9ኛዋ ሀገር ሆናለች።
ያለቀናቸው በመወለዳቸው ምክንያት ለምግብ እጥረትና ለሞት የሚዳረጉ ጨቅላ ሕጻናትን ሕይወት ለመታደግ ባንኩ ትልቅ ሚና ይጫወታል። የእናት ጡት ወተት በሽታን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከምግብ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን የጨቅላ ሕጻናት ሞት ከ30 እስከ 40 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል ተብሏል።

