ቡና ባንክና የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ስምምንቱ ባንኩ በውልክና ዶክመንቶች የሚፈጸሙ የሰነድ ማጭበርብሮችን ለመከላከል ያግዘዋል።

ከግል ባንኮች ውስጥ ስምምነቱን በመፈረም ቡና ባንክ የመጀመሪያው ነው

ቡና ባንክ በሃገራችን እየተስፋፋ የመጣውንና በተለይ ባንኮችን ተጋላጭ  የሚያደርገውን በውክልና ሰነዶች የማጭበርበር ወንጀል ለመከላከል የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ከፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር መፈራረሙን ለቁም ነገር መፅሔት በላከው መግለጫ   ተረድቷል።

በቡና ባንክ . ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና በፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ የተፈረመው ይኸው ስምምነት ባንኩ የሚገጥሙትን የማጭበርበር ወንጀሎች ከመከላከል ባሻገር ከኤጀንሲው ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ የውክልና ዶክመንት ማረጋገጥ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል  ተብሏል።

በቡና ባንክ . ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው በዚሁ የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ስነስርዓት ላይ  የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ  ባደረጉት ንግግር ቡና ባንክ የመግባቢያ ሰነዱን በመፈረም ከግል ባንክች ቀዳሚ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ይህም ባንኩ ለደንበኞቹ የተቀላጠፈ  አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ደንበኞቹን በውክልና ሰነድ ከሚከሰት ማጭበርበር ለመጠበቅ ዋስትና ይሆነዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አንድ ግለሰብ የባንኩን ደንበኛ ሂሳብ ለማንቀሳቀስ የውክልና ሰነድ ይዞ ሲመጣ የሰነዱ ትክክለኝነት የሚጣራበት ሂደት ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እንደነበር አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል። ከአዲሱ አሰራር ጋር ሲነጻጸርም የቀደመው ዶክመንት የማጣራት ሂደት የማጭበርበር ወንጀልን  በመከላከል በኩልም ውስንነት እንደነበረውም  ነው የገለጹት።  ኤጀንሲው የዘረጋው አዲስ አሰራር እነዚህን ሁሉ ችግሮች በማቃለል የባንኩን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ከወንጀል ስጋት ነጻ የሚያደርግ በመሆኑ ባንኩ ስምምነቱን በመፈረሙ ደስተኛ መሆኑንም ነው አቶ ሙሉጌታ የተናገሩት።

የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ በበኩላቸው ኤጀንሲው ጊዜ ቆጣቢና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ ከተጓዘባቸው ርቀቶች አንዱ የውክልና ሰነድ ትክክለኝነትን ለማረጋገጥ የዘረጋው አዲስ አሰራር ቀዳሚ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።ይህ አሰራር በተለይ ባንኮችን በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውና በውክልና ሰነድ ማጭበርበር የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እንደሚያስችላቸው ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

አቶ ሙሉቀን እንዳሉት ኤጀንሲው ከባንኮች የሚደርሱትን የውክልና ሰነዶች ትክክለኝነት ለማረጋገጥ   ከዋናው ሰነድ ጋር በማመሳከር ከሚሰጠው ምስክርነት ውጪ ውክልናው ስለመሻር አለመሻሩ  ማረጋገጥ የሚችልበት አሰራር አልነበረውም። በዚህ ሳቢያም በተሻሩ ውክልናዎች በርካታ የማጭበርበር ወንጀሎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል ብለዋል። አዲሱ አሰራር ግን አስትማማኝ ከመሆኑ በተጨማሪ ባንኮች ወደኤጀንሲው ቅርንጫፎች መምጣት ሳያስፈልጋቸው በተዘረጋው ሲስተም መሰረት ባሉበት ሆነው የውክልና ዶክመንቱን ትክክለኝነት በማረጋገጥ ለደንበኞቻቸው ቀልጣፋ መስተንግዶ መስጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤጀንሲው ባሉት 14 ቅርንጫፎች በቀን ከሚያስተናግዳቸው 6ሺህ 100 የአገልግሎት ጥያቄዎች ውስጥ 52 በመቶው ከውክልና ሰነድ ጋር የተያያዘ ነው። ኤጀንሲው ከባንኮች የሚቀርቡለትን የሰነድ ማረጋገጫ ጥያቄዎች ኮፒ በማመሳከር ብቻ ምላሽ ይሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል። ያም ሆኖ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኤጀንሲው የተረጋገጠ ውክልና በማንኛውም ሁኔታ ተሽሮ ቢሆን የሚያረጋግጥበት አሰራር ባለመዘርጋቱ ሳቢያ በተሻሩ ውክልናዎች በርካታ የማጭበርበር ስራዎች ይፈጸሙ እንደነበርም አስታውሰዋል። ይህ ክፍተት በተለይ ባንኮችን ተጠቂ አድርጓቸው እንደነበር የተናገሩት አቶ ሙሉቀን አዲሱ አሰራር ይህንን ችግር በመቅረፍ ወንጀልን የሚቀንስና ባንኮችም ለደንበኞቻቸው ቀልጣፋና ደህንንቱ የተጠበቀ  አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ባንኮች የውክልና ሰነድ ማረጋገጫ ጥያቄ ሲያቀርቡ ኤጀንሲው ምላሽ ለመስጠት እስከ ሰባት ቀናት ይፈጅበት እንደነበር የሚገልጹት አቶ ሙሉቀን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተዘረጋው ይህ አዲስ አሰራር ከመስከረም 2012 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩንም አስታውሰዋል።

ይህንን አሰራር በማስተዋወቅ ወደስራ ለመግባት ከባንኮች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከቡና ባንክ ጋር ስምምነት የተፈረመ መሆኑን ገልጸው መግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ወደፊት ከሌሎች ባንኮች ጋርም እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በመታወቂያ የሚካሄዱ ማጭበርበሮችን ለመግታት የሚያስችል ሲስተም መዘርጋቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ባንኮችን በልዩ ሁኔታ የሚያስተናግድ አዲስ አሰራር በቅርቡ ተግባራዊ እናደርጋለን ነው ያሉት

የቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ በፊርማ ስነስርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ኤጀንሲው ይህንን ተነሳሽነት ወስዶ  ከመደበኛ ስራው ባሻገር የጋራ ደንበኞችን ደህንነት ለመጠበቅ በቴክኖሎጂ ታግዞ  ወደተግባር በመግባቱ በባንኩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በስነስርዓቱ ላይ የባንኩና የኤጀንሲው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe