ቡና ባንክ ከግብር በፊት 1.19 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

  • የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ብር 34.1 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
  • ለልማትና በጎ አድራጎት ተግባራት የ8.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

 ከ13 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ቡና ባንክ አ.ማ ዓመታዊውን የባለአክሲዮኖች 13ኛ መደበኛ እና 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እሁድ ሕዳር 25 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ሲያካሂድ በ2014 ዓ.ም ከግር በፊት 1.19 ቢሊየን ብር ማትረፉን ይፋ አድርጓል።

የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ የባንኩን የ2021/22 ዓመታዊ ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች እንዳቀረቡት  ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከግብር በፊት 1.19 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከ27 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ ችሏል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ እንደተደረገው ባንኩ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2022 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ6.7 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን በዚህም  የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ32.8 በመቶ  ከፍ በማድረግ 27.2 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰው ተነግሯል። ከዚህ ውስጥ የቁጠባ ሂሳብ ተቀማጭ 77.8 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ ይዟል።

አምባሳደር ዓለማየሁ በንግግራቸው እንዳሰመሩበት ከሆነ ቡና ባንክ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የራሽያ ዩክሬን ጦርነትና ሀገራችን ላይ የተፈጠረው የሰላምና ጸጥታ ችግር በአገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደሩትን ጉልህ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ተቋቁሞ አትራፊነቱ ማስቀጠልና በአጠቃላይ አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት በላቀ ደረጃ ላይ መገኘት ችሏል። ይህም ለባንኩ ባለአክሲዮኖችና ለአጠቃላይ ሰራተኞቹ   የሚያበረታታ ውጤት ነው ብለዋል።

በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት የባንኩን የብድር አፈጻጸምም አብራርቶታል። በዚህ መሰረት ባንኩ በዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአጠቃላይ 7.6 ቢሊዮን ብር ማበደሩ የተገለጸ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረው የገንዘብ መጠን በ41.3 በመቶ በማሳደግ 25.85ቢሊዮን ብር ያደረሰው መሆኑም ተገልፃል።

ከውጭ ሃገር የሚላክ ሀዋላ ከላይ በተገለጹት ዓለምአቀፋዊና ሃገራዊ ችግሮች ባስከተሉት  ተጽእኖ ሳቢያ መቀነሱ እንዲሁም የኤክስፖርት ስራ ጉልህ በሆነ መልኩ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩን አፈፃፀም በታቀደው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና አሳድሯል ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት በዓመቱ የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝት 149.1ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር መሆኑንም ጠቁሟል። ከዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ  51.3 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ቀዳሚ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ቁጥራቸው ከአስር የውጭ ሃገራት ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች  ጋር የቀጥታ ግንኙት መስርቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ሪፖርቱ አብራርቷል።

የባንኩ ጠቅላላ ሃብት በበጀት ዓመቱ የ8.16 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቶ 34.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል።የባንኩን ካፒታል በተመለከተ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንዳብራራው በበጀት ዓመቱ የብር 1.2 ቢሊየን ብር እድገት አሳይቷል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ የካፒታል መጠን 5.1 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ቡና ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል በበጀት ዓመቱ 58 አዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የከፈታቸውን ቅርንጫፎች መጠን 343 አድርሶታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምቹ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ በተደረገው እንቅስቃሴ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ወደ 572 334 ከፍ በማድረግ የ41.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉም ተብራርቷል። ይህም አፈጻጸም የባንኩን አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ወደ 1 ሚሊዮን 960 ሺ 853 ከፍ አድርጎታል።

ቡና ባንክ በበጀት ዓመቱ ከወለድ ነፃ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስተዋወቅ አገልግሎቱ የራሱ ልዩ መለያ እና የንግድ ስም እንዲኖረው ባደረገው ጥረትም “ኻዲም” (KHADIM)” የተሰኘ የአገልግሎት መለያ በህጋዊ መንገድ አስመዝግቦ መጠቀም መጀመሩን የገለጸው ሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ  መጨረሻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያገኘውን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን  ብር 896.6 ሚሊዮን አድርሶታል ብሏል። ይህም ካለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር የብር 272.5 ሚሊዮን ወይም የ43.7 በመቶ ጭማሪ ማሳየት መቻሉም ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በተጠናቀቀው

የበጀት ዓመት በደንበኞች የተከፈቱ 52 ሺ አራት አዳዲስ ከወለድ ነፃ ሂሳቦች አጠቃላዩን የባንኩን የወለድ ነጻ ደንበኞች ቁጥር  ወደ 111 ሺ 909  እንዲደርስ አድርጎታል ብሏል ሪፖርቱ። ሪፖርቱ የባንኩን የሰው ሃይል ልማት እድገት በማስቀመጥ፣ የባንኩ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑ ጠቁሟል፡፡

ሪፖርቱ በዋናነት ካካተታቸው አብይ ተግባራት መካከል የባንኩን የማህበራዊ ሃላፊነት የተመለከተው ክፍል ይገኝበታል። ቡና ባንክ በሃገር ግንባታ እንዲሁም የህዝብን ህይወት ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመንግስት በሚካሄዱ ጥረቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለቀረበለት ጥሪ በሰጠው ምላሽ በበጀት ዓመቱ በድምሩ ከ8.1 ሚሊዮን ብር በላይ የማህበራዊ ኃላፊነት ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

ይህ የባንኩ ሃገራዊ ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የቦርዱ ሊቀመንበር አምባሳደር አለማየሁ ሰውአገኝ አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ባንኩ ሀብቱን ከማሳደግ እና ገጽታውን ከመገንባት አንጻር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዲ አፍሪክ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለባንኩ የህንጻ ግንባታ አገልግሎት የሚውል 4ሺ 530 ካሬ ሜትር መሬት በሊዝ ይዞታ ለመረከብ የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቁን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት አመልክቷል።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe