ቡና ባንክ የውጭ ገንዘብ ለመነዘሩ ደንበኞቹ የ2020 ሱዙኪ ዲዛየር የቤት አውቶሞቢል ሸለመ

ለገና በአል ወደአገራቸው የሚገቡ ዳያስፖራዎች ገንዘባቸውን በባንክ ብቻ እንዲመነዝሩ የሚያበረታታ ዕድል በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
ቡና ባንክ ላለፉት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን ዘጠነኛውን ዙር “የውጭ ምንዛሬ ይቀበሉ ፣ይመንዝሩ ይሸለሙ” መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ ምክንያት በማድረግ ዕጣ ለወጣላቸው ደንበኞቹ ያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በዛሬው ዕለት አስረክቧል።
ባንኩ ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በዋና መስሪያ ቤቱ ባካሄደው በዚሁ የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ የዕጣ አሸናፊዎች ለሆኑት ባለዕድሎች የቤት አውቶሞቢል፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣ ማቀዝቀዣዎች፣ የውሃ ማጣሪያዎች፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዠኖች እና ስማርት ስልኮችን በሽልማት አበርክቷል።
ደንበኞች ከውጭ የሚላክላቸውንም ሆነ በእጃቸው የሚገኝ የውጭ ገንዘብ በቡና ባንክ ቅርንጫፎች በኩል ሲቀበሉና ሲመነዝሩ ተሸላሚ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ኩፖን የሚቀበሉበት አሰራር የዘረጋው ቡና ባንክ ባለፉት ዓመታት ባካሄዳቸው ዘጠኝ ዙሮች በርካታ ቁጥር ላላቸው ደንበኞቹ ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸውን ሽልማቶች ሲያበረክት ቆይቷል።
ባንኩ ዛሬ ባካሄደው የ9ኛው ዙር የይቀበሉ ፣ ይመንዝሩ ፣ ይሸለሙ መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር የዕጣ ባለእድል የሆኑ ደንበኞቹን በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ ፕሮግራም የሸለመ ሲሆን በዚህም ለአንደኛ ዕጣ አሸናፊ ዘመናዊ የ2020 ሱዙኪ ዲዛየር የቤት አውቶሞቢል ፣ለሁለተኛ ዕጣ አምስት የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣ሶስተኛ ዕጣ አምስት ፍሪጆች፣ አራተኛ እጣ አምስት ፍላት ስክሪን ቴሌቪዠኖች፣ አምስተኛ እጣ አምስት የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች፣ እና ስድስተኛ ዕጣ አስር ስማርት ሞባይል ቀፎዎችን ለባለዕድሎች አስረክቧል።
የቡና ባንክ ኢንተርናሽናል ባንኪንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጠና ሃይለማርያም ለባለዕድሎች ሽልማቱን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት “የውጭ ምንዛሪ ይቀበሉ ፣ይመንዝሩ፣ይሸለሙ” መርሃ ግብር በህጋዊ መንገድ የሚካሄድ የውጭ ምንዛሪ ለውጥን በማበረታታት ሃገሪቱ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በማረጋገጥ ረገድ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ቡና ባንክ ያምናል” ብለዋል።
በተለይም በዚህ ወቅት የምዕራባውያን መንግስታት በሚያሳልፏቸው ኢፍትሃዊ ውሳኔዎች በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ጫና በኢኮኖሚያችን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ተቋቁመን ለመሻገር በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለገና በዓል ወደሃገር ቤት ሲገቡ ገንዘባቸውን በህጋዊ መንገድ በባንክ እንደመነዝሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ወደሃገር ቤት መምጣት ያልቻሉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን ለወዳጅ ዘመድ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በባንክ በማስተላለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ቡና ባንክ ይህንን ሃገራዊ ጥሪ ተቀብለው ለገና በአል ወደሃገራቸው የሚገቡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገንዘባቸውን በባንክ እንዲመነዝሩ ለማበረታታት ካዘጋጀው አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶች በተጨማሪ በልዩ በልዩ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን አጓጊ ዕድሎችን በቅርቡ ይፋ በማድረግ ወደስራ ለመግባት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ባንኩ ከብሄራዊ ሎተሪ ባገኘው ፍቃድ 10ኛውን ዙር የውጭ ምንዛሪ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ መርሃ ግብር በቅርቡ በይፋ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።
“ደንበኞች በቡና ባንክ በመመንዘር እና በመቀበል የአገልግሎቱና የማበረታቻ ሽልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቡና ባንክ በዚህ አጋጣሚ ይጋብዛል” ነው ያሉት ሃላፊው።
ከተመሰረተ 12 ዓመታት ያስቆጠረው ቡና ባንክ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በከፈታቸው 330 ቅርንጫፎቹ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe