ቢል ጌትስ “ኮቪድ-19 ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል ችግር አይደለም”

ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥን ሲያስቡ እነዚህን ሁለት ቁጥሮች እንዲያስታውሱ ያሳስባሉ፣ ቢሊየነሩ ቢል ጊትስ።

እርሳቸው እንደሚሉት የሰው ልጅ የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠር ከቻለ በሰው ልጅ ዝርያ ታሪክ ትልቁ ስኬት ሆኖ ይመዘገባል።

የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠር ከባድ እንደሆነ ሲያስረዱም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ማቆም እጅግ ተራ ጉዳይ እንደሆነ በአንጻራዊነት በማስረዳት ነው።

የቢል ጌትስ አዲሱ መጽሐፍ ርእሱ “How to Avoid a Climate Disaster” ይሰኛል። የአየር ንብረት ለውጥ ጥፋትን እንዴት መከላከል ይቻላል? የሚል ትርጉም አለው።

መጽሐፉ ዓለማችን ወደ አየር ንብረት ውጥንቅጥ ጨርሶዉኑ ከመግባቷ በፊት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ያትታል።

በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ዓለም የሚገጥማትን ፈተና በሰው ልጆች ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቀው ነው ይላሉ ቢሊየነሩ ቢል ጌትስ።

ይህን በድጋሚ ሲያስረዱም ሁለት ቁጥሮችን ያነሳሉ። 51 ቢሊዮን ለዜሮ!

የእነዚህ ቁጥሮች ትርጉም ዓለም በዓመት ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው የግሪንጋስ መጠንን የሚያሳይ ነው። 51 ቢሊዮን ቶን የግሪንጋስ በካይ ልቀት ሲሆን የሰው ልጆች ይህን ቁጥር ወደ ዜሮ ማውረድ ይኖርባቸዋል።

የሰው ልጅ ይህን ካሳካ በሰው ልጆች ፍጥረት ታሪክ ትልቁ ስኬት ይሆናል ይላሉ ቢል ጌትስ።

የቢል ጌትስ ትኩረት አሁን ቴክኖሎጂዎች ወደ ዜሮ ግስጋሴን እንዴት ሊያግዙ ይችላሉ የሚለው ነው።

እንደ ንፋስ ኃይልና የጸሐይ ብርሃንን የመሰሉ ታዳሽ ኃይሎችን መጠቀም የካርቦን ልቀትን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳሉ። ይህ ግን ከልቀቱ 30 ከመቶ ብቻ ነው መቀነስ የሚያስችለው።

የዓለም ኢኮኖሚን 70 ከመቶ በሌላ ታዳሽ ኃይል እየተኩ መሄድ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ዓለም ቅርቃር ውስጥ ትገባለች ይላሉ ቢልጌትስ።

70 ከመቶ የዓለም ኢኮኖሚ በተለይም የብረት፣ የሲሚንቶ፣ የትራንስፖርት ዘዴዎች እንዲሁም የማዳበርያ ምርት በሙሉ አዲስና ከካርቦን ነጻ የሆነ ዘዴ ሊተካቸው ይገባል ነው የሚሉት ቢል ጌትስ።

ይህ ሥራ በፍጹም ለሰው ልጅ ቀላል ነው ተብሎ አይገመትም ባይ ናቸው።

ቢል ጌትስ እንደሚሉት ይህን የዓለምን 70 ከመቶ ኢኮኖሚ የያዘ ዘርፍ ብድግ ብለን በአዲስ ለመተካት አቅሙም ሐሳቡም የለንም፤ ቀላልም አይሆንም ይላሉ።

አሁን የሰው ልጅ የነዳጅና ናፍጣ መኪና በማሽከርከሩ፣ ኤሌክትሪክ በመጠቀሙ እየከፈለ ያለው ዋጋ አይታየውም። መንግሥታት ግን ዓለምን ከጥፋት ለመታደግ ሥራ መጀመር አለባቸው ሲሉ ይወተውታሉ ቢል ጌትስ።

ተራ ዜጋ በዓለም የአየር ንብረት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት፣ እየደረሰበት ያለውንም ጉዳት ለማየት፣ ሕመሙ ሊሰማው አይችልም። ለዚህም ነው መንግሥታት ጣልቃ መግባት ያለባቸው ብለው ይከራከራሉ።

የግል ዘርፉ ታዳሽ ኃይል ላይ ብቻ እንዲያተኩርና የአካበቢ ብክለትን እንዲያቆም ከባድ ቅጣቶችን በመንግሥታት ሊጣልበት ይገባልም ይላሉ።

የሪፐብሊካን ፓርቲ በአሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠውን ዝቅ ያለ ግምትም ማስተካከል ይገባዋል ባይ ናቸው።

ቢል ጌትስ በ1975 ማይክሮሶፍትን በሽርክና የፈጠሩ ሰው ሲሆኑ አሁን በ124 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የዓለም 4ኛው ሃብታም ሰው ናቸው።

ከሀብታቸው 50 ቢሊዮኑን ለበጎ አድራጎት በመስጠት በሜሊንዳ ፋውንዴሽን በርካታ የጤና ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

ቢል ጌትስ በአሁን ሰዓት በጤናና በትምህርት ዘርፍ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ትልቅ ተሰሚነት ያላቸው ባለሀብት ናቸው።

ቢልጌትስ በዓለም ላይ ኮቪድ-19ኝን የመሰለ የጤና እክል እንደሚከሰት ቀደም ብለው መተንበያቸውን ተከትሎ ተህዋሲውን እሳቸው ናቸው የፈጠሩት የሚሉ የሴራ ፖለቲከኞች ትኩረት ሆነው ቆይተዋል።

ሐሳዊ መረጃዎችን በመገጣጠም የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ ቡድኖች ቢል ጌትስ ኮቪድ-19ኝ ወረርሽኝን ፈጥረው የዓለም ሕዝብን ቁጥር ለመቀነስ ይፈልጋሉ ብለው ያሟቸዋል።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe