“ባለቤቴን እና ዘጠኝ ልጆቼን አጠገቤ ገደሏቸው” ከበኩጂ ነዋሪዎች አንዱ

ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ. ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ይፋ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ይህንን ጥቃት “ጭፍጨፋ” መሆኑን ገልጸው “በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ የክልልና የፌደራልም አመራሮች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ፤ 42 የታጠቁ ሽፍቶች እ እደተደመሰሱ፤ ስለትን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተናግረዋል።

ባለቤታቸውንና 9 ልጆቻቸውን ያጡት አርሶ አደር

የ41 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ በላይ ዋቅጅራ ነዋሪነታቸው ታጣቂዎች በድንገት ጥቃት ፈጽመው ከ120 በላይ ሰዎች በተገደሉባት የበኩጂ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በጥቃቱ በሰዓታት ውስጥ ባለቤታቸውና 9 ልጆቻቸው ተገድለዋል። አቶ በላይ “ባለቤቴ፣ 5 ሴት ልጆቼ እና 4 ወንድ ልጆቼ ናቸው የተገደሉት” ይላሉ በሐዘን በተሰበረ ድምጽ።

ቤተሰቡ በእንቅልፍ ላይ እንዳለ ቤታቸው ላይ በተከፈተው ተኩስ መላው ቤተሰባቸውን ያጡት አቶ በላይ ወገባቸው ላይ በጥይት ተመትተው አሁን ቡለን ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ።

“ረቡዕ ሌሊት 12 ሰዓት አካባቢ መጥተው ከበቡን። ከዚያም በር ሰብረው ገቡና ተኩስ ከፈቱብን። አስሩንም የቤተሰቤን አባላት አጠገቤ ነው የገደሏቸው” ይላሉ።

ለ27 ዓመት በትዳር አብረው በመኖር አስር ልጆች ያፈሩት የባለቤታቸው ስም ኦብሴ ፉፋ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ በላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ከገደሏት በኋላ አንገቷ ላይ የነበረውን ወርቅ ወስደው ሄዱ” በማለት ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ አቶ በላይ ሐዘናቸው ከባድ ነው። በግፍ የተጨፈጨፉትን የልጆቻቸውን ስም ደጋግመው ይጠራሉ።

ቢቢሲ ሲያናግራቸውም “ከትልቋ ጀምሬ የልጆቼን ስም ልዘርዝርህ. . . ሹመቴ በላይ የጀመሪያ ሴት ልጄ ናት። ከዚያ በኋላ ደራርቱ በላይ፣ ቀጥላ ሲዲቄ በላይ፣ ቀጥላ ጸሃይነሽ በላይ . . .” እያሉ ሳግ ቢተናነቃቸውም አላቋረጡም።

ከእንባቸው ጋር እታገሉ “የወንዶቹ ታላቅ መገርሳ ይባላል። ቀጥሎ አያና በላይ እና ደረጄ በላይ። ኤሊያስ የመጨረሻው ልጄ ነው” እያሉ እንባቸው ገነፈለ።

ብቻቸውን የቀሩት አባት ቆስለው ሆስፒታል ናቸው።

በጭካኔ የተገደሉት ባለቤታቸውና ልጆቻቸውን ማን እንደሚቀብራቸው ያሳስባቸዋል። “ሰው ሁሉ ከአካባቢው ሸሽቶ ወጥቷል። ማን ይቅርበራቸው? በሸራ ተጠቅልለው ነው ያሉት” ብለዋል።

የአስር ልጆች አባት የነበሩት አቶ በላይ አንዲት ልጃቸው ተርፋለች “እንደ አጋጣሚ አጎቷ ጋር ወንበራ ከተማ ሄዳ ነው የዳነችው። ከቤተሰቡ እሷ ብቻ ናት የተረፈችው።”

ረቡዕ ጎህ ከመቅደዱ በፊት የተኩስ ድምጽ በአካባቢያቸው መስማታቸውን የሚገልጹት አርሶ አደሩ “ባለቤቴን በጥይት ሲመቱ እሷን እከላከላለሁ ብዬ ስሄድ እኔንም መቱኝ። ከዚያ ሮጥኩ። እኔን ፍለጋ ሲመጡ ዝም ብዬ ተኛሁ። ሳያገኙ አለፉ” ይላሉ ከጥቃቱ እንዴት እንደተረፉ ሲያስረዱ።

ጥቃት አድራሾቹ ከሁኔታቸው ወታደር እንደሚመስሉና ጥይት በሻንጣ መያዛቸውን የሚናገሩት አቶ በላይ “በዓይን የምናቃቸው ሰዎች አሉበት። አንዳንዶቹን መልካቸውንም አይተን አናውቅም” ይላሉ።

ከጥቃቱ ለማምለጥ የሮጡ ሰዎችን በጥይት ተኩሰው እንደገደሏቸውና ከጎረቤታቸው ከሚገኝ አንድ ቤት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን “ከጎረቤቴ አንድ ጎጃሜ ቤት 13 ሰው ታርዷል” ብለዋል።

“ይሄ ይከሰታል ብለን አልጠበቅንም። መንግሥት አካባቢያችን ‘ሰላም ነው’፣ ‘የልማትና የእድገት ቦታ ነው’፣ ‘እናንተን የሚነካ የለም፤ ሥራችሁን ሥሩ’ ብለው አታለው ጨረሱን።”

በጥቃቱ ከአቶ በላይ ቤተሰብ በተጨማሪ በርካታ ሰው ተገድሏል። ቤቶች ተቃትለዋል። እሳቸው እንደሚሉት “መከላከያ ገባ እንጂ አንድም ሰው አይርፍም ነበር”።

“እኔ አካባቢ 80 አስክሬን ተቆጥሯል። ሜዳ ውስጥ ገና ያልተቆጠረ አስክሬንም አለ። እንዲህ አይነት ነገር አይተን አናውቅም። እኔ እንኳን የጦር መሳሪያ ጦር የለኝም። መንግሥት ሰላም ነው እያለ አታለለን። እኛ ምንም የምናወቀው ነገር የለም” ሲሉ በምሬት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለቤታቸውንና ዘጠኝ ልጆቻቸውን በግፍ የተነጠቁት አቶ በላይ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ።

“ከዚህ በኋላ ሰው እዚያ ይኖራል ብዬ አልገምትም። አንዳንዶች ንብረትም ሰብስበው ወጥተዋል። ሰው ተስፋ ቆርጧል። ከእንግዲህ ሰው እዚያ ሰፍሮ የሚኖር አይመስለኝም።”

“መአት ነው የወረደብን

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ የሚኖረው ሌላው የዓይን እማኝ አቶ ተስፋ [ስሙ የተቀየረ] ጥቃቱ ያልታሰበ ነው ይላል።

“መአት ነው የወረደብን” ያለው ጥቃት ይሆናል ብለው ባልጠረጠሩት ሰዓት ሊነጋ ሲቃረብ መፈጸሙን ይገልጻል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ የእሱንና የሌሎችንም ቤት ከበው “የጥይት በረዶ አዘነቡብን” በማለት መትረፋቸውን ተአምር ይለዋል።

“ነገር ግን ብዙዎችም ሞተዋል። ከአንድ ቤተሰብ 12 ሰው የተጨፈጨፈበት ሁሉ አለ” ሲል የነበረውን ሁኔታ ይገልጸል።

ለሱና ለቤተሰቡ ይህ ጥቃት የመጀመሪያው አይደለም። ከጥቂት ሳምንታት በፊት እናትና አባቱ ለሠርግ በሚጓዙበት ወቅት ድባጤ አካባቢ በተሳፈሩበት ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አሁን ደግሞ በኩጂ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሌሎች ዘመዶቻቸው ተገድለዋል። በሐዘናቸው ላይ ሌላ ሐዘን መጨመሩን ይናገራል።

“በዚህ ጥቃት ዘመዶቼንና ጓደኞቼን አጥቻለሁ። ዓይኔ እያየ አጠገቤ እንኳን ብዙ ናቸው ተመተው የሞቱት።”

በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቤተሰቦቹን ያጣው አቶ ተስፋ፤ ለግድያው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ምላሽ ያላገኙለት ጉዳይ መሆኑን በማንሳት “አላጠፋን። ምንም አላደረግን። በምን እንደሆነ እንጃ። እንግዲህ ይሄ ሁሉ ነገር የሚደርስብን ምን ባደረግነው ነው?” ይላል።

በሚኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ጨምሮ የክልሉን ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዘው ጥቃት ሲያደርሱና የሳር ቤቶችን በውስጡ ካሉ ሰዎች ጋር ሲያቃጥሉ እንደነበር ይገልጻል።

“ጉልበት ያላቸውን በጥይት ሲገድሉ፤ ሌሎቹን ደግሞ ሳር ቤት ላይ በለኮሱት እሳት ጨርሰዋቸዋል” በማለት ከእንዲህ አይነቱ ጥቃት መትረፋቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አቶ ተስፋ፤ በቀበሌው ከተወሰኑት በስተቀር በአካባቢው ያሉ አብዛኞቹ የሳር ቤት በእሳት መውደሙን፣ ጥቃቱም ለሊት 11 ሰዓት ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት እስኪደርስ መቀጠሉን ይገልጻል።

“መከላከያ ብዙ ሰው ከተገደለና ቤቶች በእሳት ከወደሙ በኋላ ነው የደረሰው። እኛን የረዳን ከአዲስ ዓለምና ከአካባቢው የመጣው ሕዝብ ነው” ሲል በአቅራቢያው ያሉ ነዋሪዎች በቻሉት የተወሰኑትን እንዳተረፉ ይናገራል።

ከጥቃት ፈጻሚዎቹ መካከል የሚያውቋቸው እንዲሁም የማያውቋቸው ታጣቂዎች በአንድ ላይ በቡድን በቡድን ሆነው “ግማሹ ቤት ያቃጥላል፣ ሌላው ያገኘውን በጥይትና በስለት ይገድል ነበር” ብሏል።

በድርጊቱ ውስጥ የመንግሥት አካላት እጅ አለበት ብሎ እንደሚያስብ ለቢቢሲ ገልጿል።

“በአካባቢው መንግሥትም አለ ብዬ አላስብም። ምንም ያላደረገ ሰው በማንነቱ ተለይቶ ሲጨፈጨፍ በጣም ያሳዝናል። ከአንድ ቤተሰብ 12 ሰው የታረደው ከጎረቤቴ ነው። ግድያው በጣም በጣም ነው የሚዘገንነው። በጣም ብዙ አስከሬን ነው የቆጠርኩት፤ ከ120 በላይ የተሰበሰበ አስከሬን ነበር። በእርግጠኝነት የማውቀው ቁጥር ግን የለም።”

“አሁን ግን [ሐሙስ] አካባቢው ተረጋግቷል። የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ ተሰማርቷል። ጭላንቆ ከሚባለው ቦታ ግን የተኩስ ድምጽ ይሰማል” ብሏል።

“የሚታወቁ ሰዎችም አሉበት”

ሌላው ቢቢሲ ያናገራቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ በቡለን ወረዳ 02 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ፤ በጥቃቱ ተገደሉ የሚባሉ ሰዎችን አስከ 150 ሊደርስ እንደሚችል ይናገራሉ።

እኚህ ነዋሪ እንደሚያረጋግጡት ጥቃት ፈጻሚዎቹ በየቦታው ቤት እያቃጠሉ ሰዎችን ገድለዋል።

“በኩጂ ላይ የእኔ ቤተሰብ በአጠቃላይ፤ አባትና ልጅ፣ የእኔ እህትና የአጎቶቼ ቤተሰብ እዚያው አልቀዋል። ከነልጁ እነሱን የሚያስተምራቸው መምህር አጎቴ [ስም ጠቅሰዋል] ጭምር ነው የተገደለው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ጥቃት አድራሾቹ የልዩ ኃይል ልብስ ያላቸው ናቸው። ሽፍታ ናቸው ይባል እንጂ የሚታወቁ የአካባቢው ሰዎችም አብረው አሉ” ሲሉ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች እንደነገሯቸው የዓይን እማኙ ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ “ማንንም ከማንም አይለዩም። ህጻንን በቀስት ከመምታት ጀምሮ አዋቂዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ነው የጨፈጨፉት። ሆስፒታል ያለው ነገር ከባድ ነው። ሆስፒታሉም ከአቅሙ በላይ ነው አሁን። ቁስለኛው የት እንደሚታከም ከባድ ሁኔታ ላይ ነው።”

ረቡዕ ማለዳ በርካታ ሰዎች ከተገደሉበት ከበኩጂ ወጣ ብሎ በሚገኝ ዶሊ በሚባል ቦታ ረቡዕ ማታ ጥቃት ተፈጽሞ 5 ሰው መገደላቸውን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከተገደሉትና ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ቀበሌዎች መሸሻቸውን የሚገልጹት የዓይን እማኙ፤ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል ስጋትና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኘው የመተከል ዞን ውስጥ በታጣቂዎች እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ወራትን አስቆጥሮ፤ አሁንም ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

አሁን ያጋጠመው ጥቃት ደግሞ ከዚህ በፊት ከተፈጸሙት ጥቃቶች አንጻር እጅግ የከፋውና በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ሲሆን፤ ነዋሪዎች በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች ጥቃት በመፈጸሙ መሳተፋቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ጥቃቱን ተከትሎም ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሰባት ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው ባደረጉት አሰሳ ከ40 በላይ ታጣቂዎችን መግደላቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሳውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች አስመልክተው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሉት “ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት ያደረግነው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም” በማለት መንግሥታቸው ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት “አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” በማለት ገልጸዋል።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት የመተከል ዞን፤ ሠላምና መረጋጋት ለማስከበር የፌደራል መንግሥት ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል በጋራ በሚመሩት ኮማንድ ፖስት ከሚተዳደሩ አካባቢዎች አንዱ እንዲሆን ቢደረግም ጥቃቱ ሳይገታ ቆይቷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኘውና ተደጋጋሚ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸምበት የመተከል ዞን ሰባት ወረዳዎች ያሉት ሲሆን በዋናነት የጉሙዝ፣ የሽናሻ፣ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞና የበርታ ብሔሮች የሚኖሩበት አካባቢ ነው።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe