ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የልዑል አለማየሁን አጽም ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ

ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በዊንድሶር ካስል ውስጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበረውን የኢትዮጵያዊ ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን አጽም እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበል ገለፀ።
ቤተሰብ፣ የልዑሉ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ እና መንግሥት የልዑሉ አጽም ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አጥብቀው ቢጠይቁም፣ የእንግሊዝ ንጉሥውያን መልስ ግን “ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አይቻለንም” የሚል ሆኗል።
የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ልዑል አለማየሁ ተቀብሮ ባለበት ስፍራ “አርፈው የሚገኙት ሳይረበሹ አጽሙን ማውጣት የሚቻል አይደለም፤ ስለዚህ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት እንደማንችል እናሳውቃለን” ሲል ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።
ልዑል አለማየሁ እግሩ የእንግሊዝ ምድርን ሲረግጥ ገና የሰባት ዓመት ታዳጊ የነበረ ሲሆን፣ እናቱ በጉዞ ላይ መሞታቸውን ተከትሎ ወላጅ አልባ ሆኖ ነበር።
በጎንደር ያሉት የልዑሉ ቤተሰቦች ግን አጭር ዕድሜውን በሰው አገር በብቸኝነት አሳልፎ በሐዘን ሕይወቱ ያለፈው ልዑል፣ ከእንግሊዝ ነገሥታት ጎን መቀበሩ ብቻ “ለነፍሱ እረፍት አይሰጥም” ይላሉ።
በጎንደር የሚገኙ የአጼ ቴዎድሮስ ሦስተኛ እና አራተኛ ትውልድ ቤተሰብም ልዑሉ “የዘላለም እረፍት” ያገኝ ዘንድ አጽሙ ወደ ትውልድ አገሩ መመለስ አለበት ሲሉ ለባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ይፋዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
የአጼ ቴዎድሮስ አራተኛ ትውልድ ቤተሰብ የሆነው ፋሲል ሚናስ፣ ልዑሉ ማረፍ ያለበት በባዕድ አገር ሳይሆን በአባቱ አገር ጎንደር ነው ይላል።
“በዊንዘር መቀበሩ መልካም አስበው እንደሆነ እረዳለሁ፣ ከእንግሊዛውያን ነገሥታት ጎን መቀበሩም እኔን አይደንቀኝም። ምክንያቱም እርሱም ልዑል ነበር” ይላል።
ወደ ብሪታንያ ከተወሰደ በኋላ እኤአ በ1879 በ18 ዓመቱ በመተንፈሻ አካላት ሕመም የሞተው ልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ከንጉሣውያን ቤተሰቦች የገንዘብ እገዛ ይደረግለት ነበር።
የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ የልዑሉን አጽም ሌሎች በስፍራው አጽማቸው ያረፉትን ሳይረብሹ ለማውጣት አዳጋች መሆኑን ገልፀዋል።
“አጽሙን ሌሎች በስፍራው ያረፉ በርካቶችን ሳይረብሹ ማውጣት እጅግ በጣም አዳጋች ነው።”
አክለውም በቤተክርስቲያኒቱ የሚገኙ አስተዳዳሪዎች የልዑል አለማየሁ ትውስታዎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ጠቅሰው፣ “እንዲሁም ደግሞ የሟችን ክብርም የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።
ቤተ መንግሥቱ ከዚህ ቀደም “ኢትዮጵያውያን ልዑካን ስፍራውን ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ” ማስተናገዱንም አስታውሰዋል። BBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe