አንድ ዶላር 153 ነጥብ 25 ብር የተሸጠ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ከተሸጠበት ዋጋ የ1 ነጥብ 87 ብር ቅናሽ ተመዝግቧል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለገበያ ያቀረበ ቢሆንም፤ የቀረበው የመጫረቻ ዋጋ ግን ከቀረበው አቅርቦት በታች ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚሁ በዛሬው ዕለት በተካሄደው ግዙፍ የገንዘብ ጨረታ ላይ በአጠቃላይ 30 የባንኮች ተሳትፈው ሁሉም ባንኮች አሸናፊ መሆናቸውን ባንኩ በመግለጫው አመልክቷል።
በጨረታው ሂደት ላይ ባንኮች ላቀረቡት ጥያቄ መሠረት 455 ነጠብ 29 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበ ሲሆን፤ ይህም ብሔራዊ ባንክ መጀመሪያ ካቀደው 500 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 44 ነጠብ 71 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ ሳይሸጥ መቅረቱን ያሳያል።
በዚህ ልዩ የጨረታ መርሃ-ግብር የተመዘገበው ከፍተኛው የመጫረቻ ዋጋ አንድ የአሜሪካ ዶላር 154 ብር ሲሆን፤ ዝቅተኛው ደግሞ 152 ነጥብ 0079 ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
የጨረታው አጠቃላይ ውጤት እንደሚያሳየው የአሸናፊ መጫረቻ ዋጋዎች አማካይ ተመን 153 ነጠብ 25 ብር ነው። ይህም ዋጋ በዚህ ሳምንት አንድ የአሜሪካ ዶላር ከተሸጠበት የ155 ነጠብ 12 ብር ዋጋ የ1 ነጠብ 87 ብር ቅናሽ ተመዝግቦበታል።
ብሄራዊ ባንክ ተመሳሳይ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ለልዩ ጨረታ ሲያቀርብ፤ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ይህንን ግዙፍ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ወደ ገበያው ያስገባው፤ የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማዎችን ለማሳካትና በገበያው ውስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማረጋጋት እንደሆነ ይታወቃል።
በቀጣይም መሰል የውጭ ምንዛሬ ጨረታዎች ቀደም ብሎ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ብሔራዊ ባንክ አረጋግጧል።

