ብርቱካን የኦነግ አመራሮችን እስር በተመለከተ ‘ከሚመለከተው አካል ጋር’ እየተነጋገርን ነው አሉ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅዳ የኦነግ አመራሮችን እስር በተመለከተ ‘ከሚመለከተው አካል ጋር’ እየተነጋገርን ነው አሉ።

ሰብሳቢዋ ይህን ያሉት ቦርዱ ትናንት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በእጩዎች ምዝገባ እና ተያያዥ ጉዳያዎች ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።

በውይይቱ ላይ ብርቱካን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየተየ ያሉ እስረኞች በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በእጩነት መመዝገብ አይችሉም ብለዋል።

በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተዘጋ እነዲሁም ዐቃቤ ሕግ የማቀርበው ክስ የለም ያላቸው ነገር ግን በእስር ላይ የሚገኙ የኦነግ አባላት መኖራቸውን ገልጸዋል።

አቶ በቴ “በሕግ መብታቸው ያልተገፈፈ” ግን በእስር ላይ የሚገኙ አባላትን በዕጩነት ማቅረብ ይቻላል ወይ? ሲሉ ጥያቄያ ሰንዝረዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “በፍርድ ቤት ጉዳይ የሌላቸው” ነገር ግን በእስር ላይ የሚገኙ በተለይ የኦነግ አመራሮችን በተመለከተ “ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል።

“[የፍርድ ቤት] ቀጠሮ እስከሌላቸው ድረስ በእስር የሚቆዩበት ምክንያት የለም” የሉት ሰብሳቢዋ፤ በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

ነገር ግን በእስር ላይ ያሉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ እስረኞች በዕጩነት መቅረብ እንደማይችሉ ብርቱካን ተናግረዋል። ሰብሳቢዋ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ሰዎችን በእጩነት ለመመዝገብ የምርጫ ሕጉ እንደማይፈቅድም አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኦጋዴነ ነጻነት ግንባር ተወካይ አቶ አህመድ መሐመድ መንግሥት በፓርቲያቸው ላይ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረሰ እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።

አቶ አህመድ ጽህፈት ቤቶቻቸው መዘጋታቸውን እና ለዕጩዎች ዝግጅት ወደ ወረዳዎች የተጓዙ የፓርቲው አባላት ወደ ጅግጅጋ እንዲመለሱ ተደርገዋል ብለዋል።

ገዢውን ፓርቲ ወክለው በመድረኩ የተገኙት ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ “ያለ አግባብ ሰው መታሰር የለበትም። ምርጫ እናዳምቃለን፤ እናሳምራለን ተብሎ ደግሞ የሕግ የበላይነት መጣስ የለበትም” ብለዋል።

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ “የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የሚደርስ ጫና ካለ ችግሩ አጋጠመ የተባለበት ቦታ በትክክል ይጠቀስ እኛ ከማዕከል ሰው እንመድባለን፤ ቦታ ድረስ ሄዶ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ይወሰዳል። . . . ይህ በሌላ ቦታ እንዳይደገም የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጉ ነን” ብለዋል።

“ከክልሎች በቂ ድጋፍ እያገኘን አይደለም”

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ከክልሎች በቂ ድጋፍ እያገኘ እንዳልሆነ አስታውቋል።

ብርቱካን እያንዳንዱ ክልል ለምርጫ ቦርድ ሠራተኞች ተሽከርካሪ እንዲያቀርቡ ከአራት ጊዜ በላይ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተናግረው፤ እስካሁን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ያሉት የአማራ እና የሶማሌ ክልሎች ብቻ ናቸው ብለዋል።

ሠራተኞች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን መስራት ካልቻሉ ምርጫውን በታቀደው ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ያስጠነቀቁት ሰብሳቢዋ፤ ሆነ ተብሎም ይሁን በግዴለሽነት አስተዳደራዊ ትብብር አለማግኘት ለፓርቲዎች እና ለምርጫ ቦርድ ፈተና ሆኗል ብለዋል።

ጩዎች በበቂ ቁጥር አለመመዝገብ

በማክሰኞ ዕለት በተደረገው ውይይት ክፍት በተደረጉ የምርጫ ጣቢያዎች ዕጩዎች በበቂ ቁጥር እየተመዘገቡ እንዳለሆነ ብርቱካን ተናግረዋል።

ሰብሳቢዋ ክፍት በሆኑ ጣቢያዎች ፓርቲዎች ዕጪዎቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ይሁን እንጂ በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት ወጥነት የሌለው አሰራር በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት ችግር እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ ተናግረዋል።

የኢዜማ ተወካይ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ዕጩዎችን ለማስመዝገብ ቦርዱ በይፋ ከጠቀሳቸው መሠፈርቶች በተጨማሪ ዕጩዎች ሌሎች ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ እየተጠየቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች በዕጩነት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በሚያመሩበት ወቅት ከሚሰሩበት የመንግሥት መስሪያ ቤት የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዲያመጡ ይጠየቃሉ ብለዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ በበኩላቸው በዕጩነት ለመወዳደር መልቀቂያ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጋን እና የጸጥታ መዋቅር ሠራተኞች መሆናቸውን አስታውሰው፤ በዚህ ላይ ማስተካከያ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የኦነግ፣ የኢዜማ፣ የብልጽግና፣ የኦፌኮ እና የኦብነግን ጨምሮ የሌሎች ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የዕጩዎች ምዝገባ ከየካተቲት 8 ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ድረስ ይካሄዳል ተብሏል።

ይሁን እንጂ የቁሳቁስ አቅርቦት በተለያዩ ክልሎች በሁሉም ጣቢያዎች ማድረስ ባለመቻሉ፤ ይህን ተከትሎ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ባለመከፈታቸው ሁለተኛ ዙር የዕጩዎች ምዝገባ እስከ መጋቢት 6 ድረስ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe