ታረቀኝ ሙሉ፡- ‹ለጥላሁን ገሠሠ ልደቱ ሲከበር የእሱን ዘፈን ዘፍኜለታለሁ›

ድምፃዊ ታረቀኝ ሙሉ የጨርቆስ ልጅ ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም አንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ‹እንቆቅልሽ› በሚል ርዕስ ባወጣው አልበም ላይ ካሉት ዘፈኖች መሀከል ‹ባይተዋር ጎጆ› የተሰኘውን ዘፈን በድጋሚ በመጫወት ነው ከሙዚቃ አድማጩ ጋር በይበልጥ የተዋወቀው፡፡ ከሳምንት እስከ ሳምንት በተለያዩ የምሽት ክለቦች ውስጥ ከሚሰሩና የመስራት አቅማቸውን ካስመሰከሩ  ድምፃውያን መሀከል የሚጠቀሰው ታረቀኝ በአዘፋፈን ስልቱ በቅላፄውና በመድረክ አያያዙ ተስፋ የተጣለበት ወጣት አርቲስት ነው፡፡ ‹እናቴ ወደ ሙዚቃ እንድገባ ታግዘኝ ነበር› የሚለው ታረቀኝ በዚህም ‹የእናቴን ህልም እያሳካሁ ነው› ይላል፡፡

ቁም ነገር፡- ታረቀኝ ማነው?

ታረቀኝ፡- ታረቀኝ ሙሉ እባላለሁ፤ ጨርቆስ ላይ ተወልጄ ያደኩ  ልጅ ነኝ፤

ቁም ነገር፡- ልጅነት ጨርቆስ ላይ እንዴት ነው?

ታረቀኝ፡-ጨርቆስ ያው የታወቀ ነው፤ በጣም ደስ የሚል ሰፈር ነው፤ በልጅነትህ  ብዙ ነገሮችን የምትማርበት ሰፈር ነው፤ ፍቅሩም፤ ጉርብትናውም ትማራለህ፤ጨርቆስ ከሰፈርም በላይ ሀገር ነው፤

ቁም ነገር፡-ትምህርትስ የት ተማርክ?

ታረቀኝ፡- እዛው ሰፈር ፈለገ ዮርዳኖስ ነው አንደኛ ደረጃ የተማርኩት፤ ስምንተኛ ክፍል ወደ ናዝሬት ሄጄ ነው ሚኒስትሪ የተፈተንኩት፤

ቁም ነገር፡- ሙዚቃ ትምህርት ቤት እያለህ ትሞክር ነበር?

ታረቀኝ፡- ፈለገ ዮርዳኖስ ሚኒ ሚዲያ ውስጥ እዘፍን ነበር፤ ናዝሬት ደግሞ የቤተሰብ መምሪያ ክበብ ውስጥም እሳተፍ ነበር፤

ቁም ነገር፡- ቤት ውስጥ ስታንጎራጉር ቤተሰብ ምን ይልህ ነበር?

ታረቀኝ፡-  ቤተሰብ በተለይ የመጀመሪያው የቤታችን ልጅ ሙሉ ትኩረቴን እንዳደርግ የሚፈልገው ትምህርቴ ላይ ነበር፤ዘፈኑን ባይጠላም ትኩረቴን ወደ እዛ እንዳላደርግ ይፈልግ ነበር፡፡ በሙዚቃ ው ላይ እንዳተኩር ትፈልግ የነበረችው ወላጅ እናቴ ናት፡፡ወ/ሮ በየነች ትባላለች፡፡በጣም ዘፋኝ እንድሆንላት ትፈልግ ነበር፤ አንድ እርምጃ ህልሟ እውን ሆኗል  ለማለት እችላለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የመጀመሪያ መድረክን ለእናትህ አሳየሃቸው ታዲያ?

ታረቀኝ፡-ምን ጥያቄ አለው? ጨርቆስ ክበብ ውስጥ ካውንስሊን ለመጀመሪያ ጊዜ ስዘፍን መጥታ አይታኛለች፤እሷንና ወንድሜን ጋብዣያቸው አይተውኛል በሙሉ ባንድ ስዘፍን፡፡

ቁም ነገር፡-የማንን ዘፈን ነበር የዘፈንከው?

ታረቀኝ፡-የእዛን ጊዜ የዘፍንኩት የአክሊሉ ስዩምን ‹መለየት ክፉ ነው› የሚለውን ዘፈን ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- ምሽት ክለብስ  መጀመሪያ የት ሰራህ?

ታረቀኝ፡- የመጀመሪያ ምሽት ክለብ ከናዝሬት እንደመጣሁ መስራት የጀመርኩት መረሳ የሚባል የትግርኛ ዘፋኝ አለ እሱ ጋር ነበር፡፡የተወሰነ ጊዘ ጊዜ እሱ ጋር ከሰራሁ በኋላ የቀረኝ ቦታ የለም፤ መዞር ጀመርኩ ፤ኒያላ፤ ሐረር መሶብ ብዙዎቹ ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የእነማንን ትዘፍን ነበር?/ የጥላሁን ገሠሠ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው/

ታረቀኝ፡-የጥላሁን ያው የታወቀ ነው፤ የሌሎቹንም እዘፍን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ምሽት ክለብ መስራት ለድምፅ በጣም ጥሩ ነው፡፡አሁን ለምሳሌ በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ማታ ማታ የተለያዩ ክለቦች ውስጥ እሰራለሁ፡፡ ካሳንቺስ ቪ ላውንጅ፤ ቤልቪው መገናኛ፤ስቶኮሆልም ከሸዋንዳኝ ጋር ሰኞ ሰኞ እሰራለሁ፡፡ድምፅ ሁለት ሶስት ቀን ዘፍነህ ስታርፍበት የለመደው ነገር ሲቀር ይቀየራል፤እና መስራቱ ድምጽህን ጠብቀህ ለመቆየት ያግዛል፡፡ በእዛ ላይ ብዙ ነገሮችን ትማራለህ ፡፡

ቁም ነገር፡- ‹ባይተዋር ጎጆ› የጥላሁን ገሠሠ ስራ ይሁን እንጂ በአንተ ነው የሚታወቀው ዘፈኑ፤ እንዴት ሰራኸው?

ታረቀኝ፡-የክቡር ዶ/ር ጥላሁንን ገሠሠ  ዘፈን ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀኝ ዘፈን ነው፡፡ ከእዛ በኋላ አቤል ሙሉጌታ የሰጠኝ ‹ፍቅርሽ ገብቶ በደሜ› ከእዛ ደግሞ የአህመድ ዲንቢ የሰጠኝ‹ስሚያቸው›በቅርቡ የለቀቅሁት ስራ አለ፤የዚህ ግጥም ደራሲ ናትናኤል ግርማቸው የሚባል ጎበዝ ልጅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከህዝብ ጋር በደንብ የተዋወቅሁት ጋሽ ጥላሁን ዘፈን ይሁን እንጂ ከእዛ በፊት የሰራሁት ነጠላ ዜማ አለኝ በማህራዊ ጉዳይ ላይ የሚያረኩር፡፡ዘፈኑ ጥሩ ቢሆንም ብዙም የመሰማት ዕልድ አልገጠመውም ነበር፡፡የጥላሁንና ከሰራሁና ሌሎቹን ከለቀቅሁ በኋላ ሰው ውስጥ መግባት ጀምሯል፡፡

ቁም ነገር፡-ይሄ የጥላሁን ዘፈን በጣም ከባድ ከሚባሉት ዘፈኖቹ መሀከል ይጠቀሳል፤ እንዴት ደፈርከው?

ታረቀኝ፡-ትክለክል ነው፤ ሁሉም የጋሽ ጥላሁን ስራዎች ከባዶች ናቸው፡፡ ጥላሁን በጣም ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፤ ጥላሁን እኮ ንግግርን ዘፈን ማድረግ የሚችል ሰው ነው፡፡ ያው እንደማንኛው ሰው ለጥላሁን  የተለየ አክብሮት አለኝ፤ ከልጅነቴ ጀምሮም የጥላሁንን ዘፈኖችን እየሰማሁ ነው ያድግሁት፤የተለያዩ ቦታዎች ስዘፍን የሚሰሙ ሰዎች ልጅነቴን ሁሉ እያዩ ትንሹ ጥላሁን ይሉኝ ነበር፤ይህንን ዘፈን የተለያዩ ቦታዎች ክለቦች ላይ የምዘፍነው ቢሆንም ወስኜ ልዝፈነው ስል አንድ ወር አልፈጀብኝም፡፡ድፍረት አይደለም ግን እግዚአብሔር ስለፈቀደ መሰለኝ እንደወጣ ብዙ ሰው ጆሮ ገባው፡፡ የሚገርም ከዱባይ መጥቼ ነው የሰወራሁት፤ በወቅቱ ዱባይ ስለነበር የምዘፍነው አቤል ሙሉጌታ የሰጠኝን አዘፈን ለመስራት ወደ አዲስ አበባ ልመጣ ስል ለምን ለአንድ ዘፍን ብቻ ብዬ እሄዳለሁ ብዬ ነው የሰራሁት፤ክሊፑም በጣም አሪፍ ስለሆነ ሰው ወደደው፤

ቁም ነገር፡- ይሄ ዘፍን ያሳወቀህን ያህል ጥያቄም አስነስቶብሃል?

ታረቀኝ፡-ትክክል ነው፤ ያው ደራሲዎቹ ጋር ጥያቄ ነተነስቷል፡፡ የዜማው ደራሲ አበበ መለሰ፤ የግጥሙ ደራሲ ደግሞ ይልማ ገ/አብ ናቸው፡፡ ሁሉቱም ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ትልቅ አሻራ ያላቸው በጣም የማከብራቸው  ሙያተኞች ናቸው፡፡ በመድፈር ሳይሆን ለእነርሱ ካለኝ አክብሮት የተነሳ እና ዘፈኑን የትም ቦታ እዘፍነው ስለነበር ነው የዘፈንኩት ብዬ በወቅቱ በህዝብ ፊት ቆሜ ይቅርታ ጠይቄያለሁ፡፡

ቁም ነገር፡-ጥላሁን ገሠሠ ካለፈ 10 ዓመቱ ነው፤ በህይወት እያለ ግን እሱ ፊት የመዝፈን አጋጣሚ አግኝተህ ነበር?

ታረቀኝ፡- መድረክ ላይ ዕድሉን አላገኘሁም፤ በግሉ ግን በኤፍ ኤም ራዲዮ ላይ ልደቱ ሲከበር በስልክ የእሱን ዘፈን ዘፍኜለታለሁ፤በመጀመሪያ የዘፈንኩት‹ እንደ ወንዝ ድንጋይ አሳ እንደላሰው› የሚለውን ዘፍን ነበር፡ ፀጥ ብሎ ሲሰማኝ ቆይቶ ‹ግሩም ነው› አለኝ፤ ምናልባት ከዕድሜዬም አንፃር ያንን ዘፈን እንዴት መረጠው? ሳይል አልቀረም፤ እንደገና ሌላ ዘፈን ሲለኝ ግሩም ነው ብሎ የሰጠን አድናቆት ስሜቴን ረበሸው መሰለኝ ሁለተኛውን ዘፈን ‹ያን ሲያማ› የሚለውን ነበር የዘፈንኩት፡፡ሰማኝና ይሄ ዘፈን የሚዘፈነው እንደዚህ ነው ብሎ በስልክ ሲለቀው ምን ውስጥ ልግባ? ጥላሁን ልዩ ሰው ነው፤ በነገራቸን ላይ ድሮ ሪቼ አካባቢ ነዳጅ ማደያ ስለነበረው ከሰፈር እየሄድን መስታወት ውስጥ ቁጭ ሲል እናየው ነበር፤በህይወቴ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ሰው ነው ጥሌ፤ ነፍሱን በገነት ያቆይልን፡፡

ቁም ነገር፡- እስካሁን ስንት ነጠላ ዜማዎች ሰራህ ማለት ነው?

ታረቀኝ፡-አራት ዘፈኖች ሰርቻለሁ፤

ቁም ነገር፡- ሁሉም ክሊፕ አላቸው፤ ዩ ቲዩብ ላይ እንዴት ነው?

ታረቀኝ፡-ጥሩ ነው፤ በባይተዋር ጎጆ ብቻ እስካሁን ከስድስት ሚሊየን ሰው  በላይ አይቶታል፤ ፍቅርሽ ገብቶ በደሜ እስከ አምስት ሚሊየን ሰው አይቶታል፡፡

ቁም ነገር፤- ያቺ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማህስ?

ታረቀኝ፡- እሷ አሁን ከአንድ ሚሊየን በላይ ታይቷል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ዘፈን በጣም መልዕእክ ያለው ዘፈን በመሆኑ አሁን በሚቀጥለው በምሰራው አልበሜ ውስጥ እንደገና እጫወተዋለሁ፤

‹የፍቅር ገበያው ቀዝቅዞ እንደ ዋዛ

ምነው ተራርቆ ክፉ ነገር በዛ

የሰው ልጅ እንደ ዕቃ ባለው ተመዝኖ

ታላቅ ታናሽ ሆነ ክብር በኪስ ሆኖ

ካለን ስናካፍል ባለን ይጨመራል

የቄሳር ለቄሳር ፍቅር ይሻለናል› ነው የሚለው፡፡ በጣም የምወደው ስራ በመሆኑ እንደገና እጫወተዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የአልበም ስራህስ?

ታረቀኝ፡-እንግዲህ እየሰራሁ ነው፡፤ ግን ቀደም ሲል እንዳልኩህ አምስት ስድስት ክለቦች ውስጥ ነው የምዘፍነው አሁን፤ ትንሽ ቢዚ ነኝ፤ ግን ከድሮ ጀምሮ እጄ ላይ ያሉ ጥሩ ጥሩ ስራዎች ስላሉ እነርሱን መልክ አስይዞ መስራት ነው የማስበው፡፡ ለምሳሌ ነፍሱን ይማረውና ታምራት ደስታ የሰጠኝ ስራ አለ፤ አብዱ ኪያር፤ አቤል ሙሉጌታ ብዙ ስራዎች እጄ ላይ አሉ፤ እነዚህን  የማምንባቸውን ስራዎች ስቱዲዮ ታምሩ አማረ ጋር ይዤ ገብቼ መጨረስ ነው የማስበው፤

ቁም ነገር፡-መቼ?

ታረቀኝ፡-መቼ? እንግዲህ አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን ዘንድሮ ዓመቱ እያለቀ ነው፤ በቀጣዩ ዓመት ግን ይደርሳል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በነጠላ ብቻ አንቀርም/ሳቅ/

ቁም ነገር፡- የበጎ አድራገት ስራዎች ላይ አትጠፋም ይባላል?

ታረቀኝ፡- አዎ፤ እንግዲህ ባለኝ ሙያ ማድረግ ያለብኝን ነገር ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ደብረማርቆስ ነበርኩ ለበጎ አድራጎት ስራ ነው፡፡ ሌላም ለጌዲዮ ስራ ልትባል ትችላለህ፤ በሙያችን ህዝብን ማገልገል አለብን ብዬ አስባለሁ፤ አልበም ስናወጣም የሚገዛን ይኸው ህዝብ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ውጭ ሀገር የት የት ሀገር ሰርተሃል?

ታረቀኝ፡-ብዙ ሀገሮች ሄጃለሁ፤ ጀርመን ፤እስራኤል፤ዱባይ፤ጣሊያን፤ቤሩት፤ባህሬን ወዘተ ሄጃለሁ፤ ጥሩ ጥሩ መድረኮች ነበሩ፡፡

ቁም ነገር፡- ቀጠሮ ላይ ታረቀኝ ብዙ አይሞላለትም ለዚህም መድረክ ላይ አንድ የተለየ ሽልማት በተደጋጋሚ ይሰጠዋል ይባላል፤ ምንድነው?

ታረቀኝ፡-ቀጠሮ እንደምንም ለማክበር እጥራለሁ፤ ምናልባት ሌሊት ሰርቼ ጠዋት የሆነ ቀጠሮ ካልሆነ በስተቀር ለመድረስ እሞክራለሁ፤ ከተሰጡኝ ሽልማቶች መሀከል ሰዓት ይበዛል፤ ወደ ሰላሳ ሰዓት አለኝ በሽልማት ያገኘሁት/ሳቅ/ ወርቅም ብዙ ጊዜ ይሰጠኛል፤

ቁም ነገር፡- ሌላም የተለየ ሽልማት አግኝተሃል ይባላል?

ታረቀኝ፡-አዎ፤ አንድ ልጅ መድረክ ላይ መጥቶ በኪሱ ውስጥ ያለውን ብር ሽልማት ከሰጠኝ በኋላ የቀበሌ መታወቂያውን አውጥቶ  ሸለመኝ/ሳቅ/ መታወቂያውን ሳየው ማመን ነው ያቃተኝ፤ደግሞ በቅርብ ጊዜ ነው መታወቂያውን ያወጣው፤

ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?

ታረቀኝ፡-በመጨረሻ በጎኔ ሆነው ለረዱኝ በሙሉ እግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡ ከአድናቂዎቼ ጋር ደግሞ በሙሉ አልበም ለመገናኘት እየሰራሁ ነው፡፡ከጥላሁን ዘፈን ጋር በተያያዘ ይልማ ገ/አብና አበበ መለሰን በድጋሚ ይቅርታ እላለሁ፤ ትላልቅ ሙያተኞች ናቸው፡፡ እነርሱ ብዙ ሊያስተምሩን የሚችሉት ነገር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ስራውን ስለወደድኩት ነው የሰራሁት ብያለሁ፡፡ ወጣትነቴን አይተው ከድፍረት እንዳይቆጥሩብኝ እጠይቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ዘፈን የወጣው በ1983 ዓ.ም ነው፤ እኔ የተወለድኩት በ1979  ነው፡፡ እንግዲህ አስበው አራት ኣመቴ ነው ዘፈኑ ሲወጣ፡፡ ከጥላሁን ከእነዛ ሁሉ ዘፈኖች መሀከል ይሄ ዘፈን ከአድማጭ ጋር አስተዋውቆኛል፡፡ ዘፈኑ እኔን ይጠብቅ ነበር ማለት ብዬ አስባለሁ፡፡ የእግዚአብሔር ባይፈቅድ ከእኔ በፊት ብዙ አርቲስቶች ነበሩ አንዳቸው ሊዘፍኑት ይችሉ ነበር፤ ለማንኛውን እግዚአብሔር የፈቀደው ነገር ነው የሆነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe