ታሪካዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብሎ እንደሚያምን ኢዜማ ገለጸ

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብሎ እንደሚያምን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ገለጸ። ምርጫው እንደ ሀገር ውጤት እንዲታይበት እንዲሁም የእውነተኛ ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስጀመሪያ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት በመግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ምርጫ ለማከናወን ምቹ ሁኔታዎች አሉ ሲባል ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ናቸው አሊያም ያጋጠሙ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም ብለዋል።

ፓርቲው ለምርጫ በሚያደርገው ዝግጅት በእጩ መረጣ ወቅት በተለያዩ የምርጫ ወረዳዎች ችግሮች እንዳጋጠሙት ጠቁመው፣ ሆኖም ነገሩን ከማራገብ እና በሚድያ ከማጮህ ይልቅ አማራጭ መፍትሄዎችን በመጠቀም ችግሮቹን ለመፍታት መሞከሩን ገልፀዋል።

የፓርቲው የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ በበኩላቸው ፓርቲው ለምርጫው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ከእነዚህም አንዱ ከጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በየምርጫ ወረዳዎቹ ፓርቲውን ወክለው የሚሳተፉ የዕጩዎች ምርጫ መሆኑን አመልክተዋል።

በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 406 የምርጫ ወረዳዎች ፓርቲውን በመወከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች በመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ፓርቲው ማስመረጡን አስታውቀዋል።

ሂደቱ የፓርቲው ውስጠ ዲሞክራሲን ያስተማረና ዲሞክራሲያዊ ድርጅት መፍጠር ሳይቻል ዲሞክራሲያዊ ሃገር መፍጠር የማይቻል መሆኑን ስንናገር የነበረውን ለመተግበር ያለንን ቁርጠኝነት ያመላከተ ሆኖ ማለፉን ጠቁመዋል።

“ይህ ሂደት በፓርቲ የውስጥ የዴሞክራሲ ባህልን እንድንገነባ እና የዴሞክራሲ ባህል ልምምዳችን እንዲያድግ ረድቶናል ብለን እናምናለን” ብለዋል።

ፓርቲው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ በ435 ምርጫ ወረዳዎች ላይ መዋቅሮች የዘረጋ መሆኑን ገልጸው፣ ከ228 በላይ ቢሮዎችንም መክፈቱን አመልክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ አዲስ አደረጃጃትን ማስተዋወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ፓርቲው ለመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ በ100 ሚሊዮኖች የሚቆጥር ብር እንደሚያስፈልገው አቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe