ታሪክ ስናጁ እዝራ እጅጉ ፟ ‹የ8ኛው የአርአያ ሠው የግለ ታሪክ ዘርፍ ተመስጋኝ ›

ታሪክን በመሰነድ የሚታወቀው የሚድያ ሰው እዝራ እጅጉ በ1971 ዓ.ም መጋቢት 30 ነበር በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው፡፡ በ1982 ዓ..ም የ11 ዓመት ታዳጊና የ5ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው እዝራ በልጅነቱ የሥነ-ጽሁፍ እና የሚድያ ዝንባሌ አሳድሮ ስለነበር በጊዜው ይወጡ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን ያነብ ነበር፡፡ በተለይ ስለ ሀገሮች የሚያስረዳ የፈረንሳይኛ ኢንሳይክሎፒዲያ በታዳጊነቱ እያነበበ ስለ ሀገሮች የህዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያሰፍር ነበር፡፡
በ1985 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበረ ጊዜ ደግሞ በወቅቱ ነጻ ፕሬስ ታውጆ ስለነበር እጅግ በርካታ ጋዜጣ እና መጽሄቶች ለገበያ ይቀርቡ ነበር፡፡ እነዚህን የህትመት ውጤቶች በማንበብና አልፎ አልፎም በመሳተፍ የሚድያ ፍቅሩን ተወጣ፡፡ በተጨማሪም ፣ከ1986 እስከ 1992 ለ 6 ዓመታት በለገዳዲ ሬድዮ ላይ ያለ ምንም ክፍያ ጽሁፎችን ሲልክ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የልጆች መጽሄት ‹‹ኩኩሉ›› በ1986 ታትማ ለህትመት ስትበቃ ከጽሁፍ አቅራቢዎቹ አንዱ እዝራ እጅጉ ነበር፡፡
እዝራ እጅጉ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የቦሌ አጠቃላይ የሚኒ ሚዲያ አባል በመሆን ከ1986 እስከ 1989 ያገለገለ ሲሆን በተለይም በሚኒሚዲያ ቆይታው በኢቲቪ ይተላለፍ የነበረውን ‹‹አካፑልኮ ቤይ››ን ፊልም በሚኒ ሚድያው አማካይነት ለተማሪዎች ያቀርብ ነበር፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ታሪክን መሰነድ ከቲቪ እና ከሬድዮ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ማስቀመጥ ርካታ ይሰጠው እንደነበር እዝራ ይናገራል፡፡ ምናልባት እነዚህ ድምጾች እና ሰነዶች ነገ ይጠቅማሉ ብሎ ያጠራቅማቸው ነበር፡፡ አንድ ቀንም የራሴን ድርጅት መመስረቴ ስለማይቀር በወጉ ይቀመጡ በማለት እነዛ ታሪካዊ ሰነዶች ዛሬም ለስራው እየጠቀሙት ይገኛሉ፡፡
እዝራ እጅጉ፣ በ1990 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በ1993 አ.ም የተመረቀ ሲሆን በ1992 ዓ.ም የመጀመሪያ የቅጥር ሥራውን አግኝቶ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ባልደረባ ለመሆን ችሏል፡፡ በመቀጠልም፣ በአዲስ አድማስ ፣ በሩህ እና በዘፕሬስ ጋዜጦች ላይ እስከ 1995 አ.ም ሰርቷል፡፡ በ1995 የቁምነገርና ፋሽን መጽሄት ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን ያገለገለ ሲሆን በየካቲት 2 1996አ.ም ደግሞ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የተሰኘ ድርጅቱን ማቋቋም ችሏል፡፡
እዝራ የራሱን ድርጅት ከፍቶ ‹‹ተወዳጅ›› የተሰኘች በነጻ የምትሰራጭ የማስታወቂያ ጋዜጣን ከ1996 እስከ 2000 ሲያሳትም ቆይቷል፡፡
ዋናው የእዝራ ፍላጎት ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ ማቆየት በመሆኑ ከ2003 ጀምሮ ታሪክን እንዴት ሰንዶ ማቆየት ይቻላል በሚለው ላይ በቂ ጥናት በማድረግ 2008 ላይ ‹‹ታሪክን በሲዲ እና በዲቪዲ›› የሚለውን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
የግለሰቦችን ታሪክ በድምጽ እና በምስል አድርጎ በሲዲ አድርጎ ማቅረብ ብዙም ባልተለመደበት በዚህ ሀገር እዝራ በድርጅቱ አማካይነት የ46 የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በሲዲ አዘጋጅቶ አሰራጭቷል፡፡ ታሪካቸው ከተሰራላቸው መካከልም ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ፣ ጀነራል ጃገማ ኬሎ ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ከታተሙ ሥራዎች ውስጥ 19 ያህሉ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተመረቁ ሲሆን ለ32 ሰዎችም በዚህ ሥራ አማካይነት የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
በተጨማሪም በአገራችን ታዋቂ የሆኑ እንደ ማማ በሰማይ ፤ ማህሌት የአክሊሉ ማስታወሻ፤ የመሳሰሉት 30 የሚጠጉ መጽሀፎችን ወደ ድምጽ በመቀየር ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች እዝራ እና ድርጅቱ መላ ዘይደዋል፡፡
በሚያዝያ 2013 እዝራ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በሚል መሪ ሀሳብ መዝገበ አእምሮን እውን አደረገ፡፡ ‹‹መዝገበ አእምሮ›› በጠንካራ ሽፋን የተዘጋጀ የ180 የሚድያ ባለሙያዎችን ታሪክ የያዘ ባለ 600 ገጽ መጽሀፍ አዘጋጅቶ በሀምሌ 2014 አስመርቋል፡፡ በተጨማሪም የታዋቂ ኢትዮጵያን ታሪክ በባለታሪኮች እና በልጆቻቸው አሰሪነት ተጠይቆ 14 መጽሀፎችን አዘጋጅቷል፡፡
ከእነዚህም መካከል የአንኮበሩ ሰው በጂኒቫ ፤ወደ ራስ መመለስ ፤ኢትዮጵያ በድህነት ማነቆ ስር ፤ማሩ አበበ የልማት አርበኛ ዳዊት ያቺን ሰአት ፤ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በመዘጋጀት ላይ ያሉ የጀነራል አሰፋ አየነ ፤ የደጃዝማች የማነ ሀሰን ፤ ኢትዮጵያዊ በአትላንታ እና መዝገበ አእምሮ የሚድያ እና የስነጽሁፍ ሰዎች ታሪክ ይገኝበታል፡፡ እዝራ ታሪክን የሚሰንድበት የራሱን ድረገጽ፤ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ያለው ሲሆን ወደ ፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በ10 አመት ጊዜ ውስጥ በአንድ ገጽ ብቻ ታሪካቸውን ጽፈው እንዲልኩ እየጣረ ይገኛል፡፡
እዝራ እጅጉ በአሁኑ ሰአት ሙሉ ጊዜውን በግለሰቦች ታሪክ ላይ አተኩሮ እየሰራ ሲሆን ወደፊትም አጠናክሮ የመቀጠል ግብ አለው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe