ከካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይና የገቢዎች ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት የተዘጋጀው ስልጠና ታክስን በኤሌክትሮኒክ አማራጮች ለመክፈል የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ይህ እስከ 10,000 የሚደርሱ ግብር ከፋዮች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው ስልጠና ግብር ከፋዩ ታክሱን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ የሚፈፅምበትን ስርዓት ለማስፋት እና የግብር ከፋዩንና የታክስ ተቋሙን የሥራ ጫናና ወጪ በመቀነስ የንግድ ሥራን ማሳለጥ አላማ ያደረገ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የሥልጠናውን መጀመር አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ታክስ ኦፐሬሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ እንዳሉት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት፣ በፍትሀዊነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መሰብሰብ የገቢዎች ሚኒስቴር ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀው፣ ይህን ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚቻለው ዲጂታል ስርዓትን መሰረት ያደረገ የገቢ አስተዳደር በመገንባት መሆኑን በማመን ቀደም ባሉ ዓመታት የታክስ አስተዳደር ስርዓቱን ለማዘመን የኤሌክትሮኒክ ታክስ ስርዓት በመዘርጋት ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ በበኩላቸው ባንኩ ዘመናዊ አሰራሮችን በመከተል በተለይም የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ለማስፋፋት ተግቶ በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም 53 በመቶ የሚሆነው የባንኩ እንቅስቃሴ የዲጂታል የክፍያ አማራጮች መሰረት አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ነው የገለፁት፡፡
በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት ግብር ከፋዮችም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም አገልግሎቱን ቢያገኙ ድካምና መጉላላትን የሚያስቀርና ወጪንም የሚቀንስ አማራጭ በመሆኑ እንዲጠቀሙበት ነው አቶ ኪዳኔ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት።