‘ትሪዮጵያ’ የተሰኘ የመረጃ መስጫ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

‘ትሪዮጵያ’ የተሰኘ የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች እና ሆቴሎችን መረጃ ለጉብኚዎች የሚሰጥ መተግበሪያ ይፋ ተደረገ።
መተግበሪያው “በቴክኖሎጂ ዘርፍ የ1888 የዓድዋ ድልን መድገም” በሚል በዘርፉ የተሰማሩ ጀማሪ የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችን እና ድርጅቶችን ለመደግፍ በተቋቋመው 1888EC ስቱዲዮ የለማ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
‘ትሪዮጵያ’ የ1888EC ስቱዲዮ የመጀመሪያው የቴክኖሎጂ ምርቱ እንደሆነ ነው የተገለጸው።
1888EC ስቱዲዮ ለወጣት የቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ሐሳቦቻቸውን የሚያበለፅጉበት እና ወደ ንግድ የሚያስገቡበትን፣ የምክር አገልግሎት፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የጥምር ንግድ ሥርዓት በማመቻቸት በዘርፉ ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን ለመፍጠር የተቋቋመ መሆኑ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ተቋማቸው እንዲህ ያሉ በዘርፉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚሠሩ ተቋማትን እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
የ1888EC መሥራች አቶ ሰለሞን ካሳ ለቴክኖሎጂ አፍላቂዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እና በድህነት እና ኋላቀርነት ላይ አዲሱን ትውልድ ለማዝመን ስቱዲዮው መቋቋሙን ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “የዘመኑ ጋሻ እና ጦራችን በቴክኖሎጂና በዲጂታል ክህሎት የተገነባ የሰው ኃይል መሆን አለበት” ብለዋል።
“ዓድዋ ላይ ተባብረን ድል እንዳደረግነው ሁሉ በቴክኖሎጂው ዘርፍም በትብብር በመሥራት የራሳችንን የድል ታሪክ ማስመዝገብ አለብን” ሲሉም መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

SourceENA

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe