ትራምፕ በሳውዲ አረቢያ ትልቅ የንግድ ስምምነትን በመፈለግ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸውን ጀመሩየሳውዲ አረቢያ ጉብኝት የአራት ቀናት ጉብኝት የመጀመሪያ ምዕራፍ ስትሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ያቀናሉ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ወደ ሳውዲ አረቢያ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው የመጀመርያውን የመንግስት ጉብኝት ሲጀምሩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉትን ተቀጣጣይ ጉዳዮች ለመፍታት የሚደረገው ሂደት አስቸጋሪ ቢሆንም ትልቅ የንግድ ስምምነትን ለማግኘት ይፈልጋሉ።
ትራምፕ ኳታርን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ የነዳጅ ሃብት ወደ ፈሰሰባቸው የባህረ ሰላጤ አገሮች በሚያደርጉት ጉብኝት የመጀመሪያ ማረፊያ በሆነችው ሪያድ ሲደርሱ የሳውዲ ተዋጊ ጀቶች ኤር ፎርስ ዋንን ከበው አሳርፈውታል።
ትራምፕ የሳውዲ አረቢያው ገዢ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እጃቸውን ለመጨበጥ ሲሄዱ ወታደራዊ ሰልፉን እየተመለከቱ የእጃቸውን ጡጫ ወደ አየር ከፍ አድርገው አወዛውዘዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካናዳ እንደ ኤር ፎርስ ዋን የሚጠቀሙበትን የኳታርን የቅንጦት 747 የአውሮፕላን ‘ስጦታ’ ለመቀበል አቅደዋል፤ ይህ ‘የሚበር ቤተ መንግስት’ በአሜሪካ መንግስት ከተቀበሉት እጅግ ውድ ስጦታዎች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡
“የኳታር መንግስት ለመከላከያ ሚኒስቴር አውሮፕላን በልግስና ለመለገስ አቅርቧል። የህግ ዝርዝሮች አሁንም እየተጣሩ ናቸው” ስትል የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለፎክስ ኒውስ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ተናግራለች።
ለዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ከተበረከቱት እጅግ ውድ ስጦታዎች መካከል የሚሆነው ይኸው የቅንጦት አውሮፕላን ትራምፕ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላ ለፕሬዚዳንታዊ ቤተ መፃህፍታቸው እንደሚበረከት ምንጩ ገልጿል። አዲስ የንግድ 747-8 አውሮፕላን ዋጋው ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው።
ትራምፕ እሁድ እለት በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ ይህንን ሃሳብ አረጋግጠዋል።
” የመከላከያ ሚኒስቴር የ40 አመት እድሜ ያለውን ኤር ፎርስ ዋንን በሌላ አውሮፕላን ለመተካት 747 አውሮፕላን በነጻ ስጦታ መቀበሉ ግልፅ እና ይፋ በሆነ ግብይት ውስጥ መሆኑ ዲሞክራቶችን በጣም ስላስቸገራቸው አውሮፕላኑን በከፍተኛ ዋጋ እንድንገዛ አጥብቀው እየጠየቁ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አውሮፕላኑን የጎበኙ ሲሆን ዲሞክራቶች እና የመልካም አስተዳደር ደጋፊዎች ኳታር እንዲህ ዓይነት ስጦታ መስጠቷ ሥነ ምግባር የጎደለው እና ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

