የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከእስር ለማምለጥ ሲሉ አሜሪካን ከኢራን ጋር ወደ ሌላ ጦርነት ለማስገባት እየሞከሩ ነው በማለት ወነጀሉ።
ሚኒስትሩ ዋሽንግተን አዲስ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ እሁድ ዕለት አስጠንቅቀዋል።
አራግቺ “ኔታንያሁ ከእስር ለማምለጥ ሲሉ አሜሪካን ወደ ሌላ ጦርነት እየገፏት ነው” ሲል በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ዳግም ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ የሚኖረውን መዘዝ ችላ ብለዋል ሲሉም አክለዋል።
“ባለፈው ጊዜ ማጠናቀቅ የሚፈልገው ስራ እንዳለ ተናግሮ፣ ኢራን የበለጠ ጠንካራ ሆና ብቅ አለች። ዕድልህን እንደገና መሞከር ትፈልጋለህ? እንግዲያው እንግዳችን እንድትሆን ተጋብዘሃል። ግን ተጠንቀቅ፤ እኛም ያልተጠናቀቁ ስራዎች አሉን” ሲሉ ዝተዋል።
ትራምፕ እሁድ ዕለት እስራኤል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 27 ከምታካሄደው ምርጫ በፊት ለኔታንያሁ ያላቸውን ድጋፍ ከገለጹ በኋላ፣ ከኢራን ጋር በነበራቸው ጦርነት ስላሳዩት አጋርነት አወድሰዋቸዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “እስራኤል የተሳሳተ መሪ ከመረጠች፣ ይህም ከቢቢ ውጪ ሌላ ማንም ቢሆን፣ አሜሪካ ይህንን ሥራ ራሷ መሥራት አለባት፣ እኔ እንደዚያ እንዲሆን አልፈልግም” ሲሉ ጽፈዋል።
ኔታንያሁ እአአ ከ2022 መጨረሻ ጀምሮ የአሁኑን መንግሥት ሲመሩ ቆይተዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነትን በመጣስ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል።
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በበኩሉ በእርሳቸው እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ በጦር ወንጀሎች ምክንያት የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
ኔታንያሁ ይህንን የፍርድ ቤቱን እርምጃ “ፀረ ሴማዊ” ሲሉ ማውገዛቸው ይታወሳል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኔታንያሁን መንግሥት ከሥልጣን ለማውረድ ትብብራቸውን አጠናክረዋል።
እስራኤል እና አሜሪካ ባለፈው ዓመት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ቴህራን ላይ በጋራ በመሆን ጦርነት ከፍተዋል። ይህም ቴህራን የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ እና በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ በሚሳኤል እና በድሮን የታገዘ ጥቃት እንድትፈጽም አድርጓታል።//

