አሜሪካ ለመጪው ምርጫ ማስፈጸሚያ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ልትለግስ ነው

የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች እንደሚልክ አረጋገጠ

አሜሪካ ዘንድሮ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ 30.4 ሚሊዮን ዶላር እንደምትለግስ አስታወቀች፡፡ ዓርብ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና የኤጀንሲው ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ይፋ ያደረጉት የአሜሪካና የኢትዮጵያ የጋራ የምርጫና የፖለቲካ ሒደት መርሐ ግብር፣ የተጠቀሰው መጠን ያለው ድጋፍ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ተቋሙን የማደራጀት፣ የማስተዳደር፣ ምርጫውን ነፃና ፍትሕ የማድረግ ተግባር ለማጠናከር ይውላል ተብሏል፡፡

በዚህ የትብብር ስምምነት መሠረት የአሜሪካ ድጋፍ ሚዲያው ሕዝቡን ስለምርጫው ግንዛቤ እንዲፈጥር፣ በፖለቲካ ሒደቱ ለዜጎች ግልጽነትን ከማረጋገጥና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የተገለሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

ኤጀንሲውና አጋሮቹ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት እንዲችሉ አቅማቸውን ማጎልበት ሌላው የድጋፉ ዓላማ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ከአሜሪካ የተሰጠው ድጋፍ መጪውን ምርጫ በስፋት ለማከናወን የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸው፣ ምርጫውን ለሁሉም ወገኖች ተዓማኒ ለማድረግ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ይህ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይህች አገር በሁሉም ሥፍራ ያሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድምፅ የሚሰማበት ሆና ሁነኛ ጉዞዋን እንድትቀጥል አጋር እንድንሆን በመጋበዛችን ኩራት ይሰማናል፤›› ያሉት የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጆንስ ናቸው፡፡

በምርጫ ቦርድና በኤጀንሲው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ከሚያደርገው የአቅም ግንባታ ዕቅድ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ መሠረት ለማጠናከር ትኩረት እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን ምርጫ አሜሪካ ለመደገፍ ለምን ይህንን ታደርጋለች ከተባለ መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ምርጫና የምርጫ ሒደት እውነተኞቹ የዴሞክራሲ ሕይወት ናቸው፡፡ ሁሉም ዜጎች ምኞታቸውንና ዓላማቸውን ለራሳቸው፣ ለማኅበረሰባቸውና ለአገራቸው መግለጽ የሚችሉባቸው ናቸው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት በመጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢዎች እንደሚልክ ማረጋገጫ ሰጠ፡፡ የኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባደረጉት ውይይት ነው ይህንን ያረጋገጡት፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ምርጫውን ከመታዘብ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ላለው ለውጥ ድጋፉን እንደሚያደርስ ቦሬል አስታውቀዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የምርጫ ታዛቢዎች መላኩ ይታወሳል፡፡

Source: Reporter

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe