የእስራኤል እና የሊባኖስ አምባሳደሮች ልዩ የተባለ የሰላም ንግግር ዛሬ በዋሽንግተን ውስጥ እንደሚያደርጉ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለስልጣናት ለቀጥታ ንግግር ፊት ለፊት ሲገናኙ በአስርት ዓመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሩቢዮ ልዩ በሆነው የቀጥታ ንግግር እንደሚሳተፉ ይጠበቃል መባሉም ተሰምቷል፡፡
የሁለቱ ጎረቤት አገራት ንግግር አሜሪካ እና ኢራን የመካከለኛውን ምስራቅ ጦርነት ለመቋጨት ያደረጉት ስምምነት ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የሚደረግ ነው፡፡
መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአገራቱ መካከል የከፍተኛ ባለስልጣናት የቀጥታ ንግግር ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይም ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሊባኖስ ባለስልጣናት በመጀመሪያ እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ የከፈተችው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ የማስማማት ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል፡፡
ሄዝቦላህ የሁለቱ አገራትን ንግግር ውድቅ በማድረግ ስምምነት ለሚደረስበት ማንኛውም ጉዳይ እንደማይገዛ አስታውቋል፡፡//
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ወይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ዋና ጸሐፊው ይህን ጦርነት ለመቋጨት ወደ ሰላሙ መድረክ መምጣት እንዳለባቸው አገራቱን አሳስበዋል፡፡ ግልጽ የሆነው ነገር ጦርነትን ለመቋጨት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል መታወቅ አለበት በሚል ዋና ጸሐፊው አስገንዝበዋል፡፡
የተኩስ አቁሙ ተጠብቆ እንዲቆይ የጠየቁት ዋና ጸሐፊው ሁሉም ዓነት ጥሰቶች መቆም እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስምምነት ላይ ለመድረስ ወደ ድርድር ዋሽንግተን እና ቴህራን እንዲመጡ ጥሪ አቀርባለሁ ያሉ ሲሆን ከጦርነት የሚገኝ ምንም አይነት ትርፍ እንደማይኖር ተፋላሚዎች ሊረዱት ይገባል ብለዋል፡፡
ሁሉም ወገኖች የሆርሙዝ ሰርጥን ጨምሮ የመርከቦችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት እንዲያከብሩም ተጠይቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት የውሃ ላይ ምርምሮች እንዲሁም የመርከቦች ያለስጋት መንቀሳቀስ መብት ሊከበር እንደሚገባም ዋና ጸሐፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡//

