አራቱ የወላጅነት ፈተናዎች

አራቱ የወላጅነት ፈተናዎች

ወላጆች እንደልጆቻቸው ጸባይ በተለያዩ መንገዶች ይፈተናሉ፡፡ ዕድለኛ የሆኑትና በራሳቸው አስተሳሰብ ልጆቻቸውን ለመምራት በቁርጠኝነት የሚተጉት ወላጆች ድካማቸው የተሻለ ይሆናል፡፡ በርግጥ እያንዳንዱን ወላጅ ብትጠይቁት በልጅ አስተዳደግ የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ይነግራችኋል፡፡ ከጾታ ልዩነት ጀምሮ፣ የጤና ኹኔታ፣ ተፈጥሯዊ ጸባይ፣ ማኅበራዊ ትስስርና የተለያዩ ምክንያቶች አንዱ ልጅ ከሌላው ልጅ የበለጠ አስቸጋሪ እንዲኾን ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡

ለመኾኑ ልጅ ወልደው ለማሳደግ ዝግጁ የኾኑ ወላጆች በዋነኝነት ትኩረት ሊያደርጉባቸው የሚገቡት ጉዳዮች ምን ምን ይኾኑ?

  1. ጤና

የጤና ጉዳይ ከጨቅላነት ዕድሜ ጀምሮ በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የሚገጥም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ወላጆች በየትኛውም አጋጣሚ ለሚፈጠሩ የልጆቻቸው የጤና እክሎች ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ህፃናት የሚመገቧት እያንዳንዷ ምግብ ሳትቀር ለጤናቸው ተስማሚ መሆኗን ማረጋገጥ፣ የንፅህናቸው ሁኔታ፣ የሚጫወቱበት አካባቢና ሌሎችም ነገሮች ለጤናቸው መታወክ የራሳቸው አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው ወላጆች በንቃት የልጆቻቸውን ሁኔታ መከታተል የውዴታ ግዴታቸው ሊሆን ይገባል፡፡ የራስዎን ጤንነት በሚጠብቁት ልክ ለልጆችዎም ጎጂውን ከጠቃሚው በመለየት በደስተኝነትና በጤናማነት ያድጉ ዘንድ መሠረታዊውን የጤና ክትትልና እንክብካቤ ሳይሰለቹ ያድርሷቸው፡፡

  1. ትምህርት

የትምህርት ጉዳይም ወላጆች ለልጆቻቸው ማሟላት ከሚገባቸው መሠረታዊ ግዴታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች የቀለም ዕውቀትና ማኅበራዊ ክህሎቶች ለማስጨበጥ የሚረዱ የልጆች ሁለተኛ ቤቶች ናቸው፡፡ ግንኙነታቸውን ለማጎልበትና ጥሩ ፀባይ ለመቅሰምም ይጠቅሟቸዋል፡፡ ስለዚህ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት የሚያገኙባቸውን ዕድሎች በማመቻቸት ለነገው የልጆችዎ ሕይወት ዛሬን በትጋት ኃላፊነትዎን ይወጡ፡፡

  1. ፀባይ

እንደወላጅ ሁላችንም ልጆቻችን ‹ትናንሽ መላእክት› ቢሆኑልን እንመኛለን፡፡ ነገር ግን በእኛም ይሁን በአካባቢያችን ተፅዕኖ ምክንያት ፀባያቸው አስቸጋሪና ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ፈተናችንን የሚያከብድባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ በዚህ ወቅት ራስን መለስ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ‹ለመሆኑ ልጄ ከኔ ፀባይ ምን ይማራል? ፤ አካባቢዬስ ልጄ መልካም ፀባይ ኖሮት እንዲያድግ የሚኖረው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው?› የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የችግሩን ምንጭ ይገንዘቡ፡፡ ከጓደኞቻቸው ማንነት ጀምሮ፣ የሚመርጧቸው የጨዋታ ዓይነቶችና ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቅርርብ በበጎም ሆነ በመጥፎ እንዲቀረፁ ያደርጋሉና በልዩ ትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡

  1. የቁጥር ጉዳይ

የአንድ ልጅ እናት ወይም አባት መሆን አንድ ጊዜ በሙሉ ልብ ተቀብለው በደስታና ኃላፊነትን በመወጣት በንቁ ስሜት የሚፈፅሙት የወላጅነት ተግባር ነው፡፡ ልጆችዎ በተቀራራቢ ዕድሜ የሚገኙና ቁጥራቸው ከአንድ በላይ ሲሆን ግን ፈተናዎም መጠኑ ይጨምራል፡፡ ለአንዱ የገዙትን ነገር ለሌላዋ አለመግዛት በልጅ ዘንድ አድሏዊ ሆነው እንዲታዩ ስለሚያደርግ ምንም ዓይነት ማበላለጥ ውስጥ እንዳይገቡ ይጠንቀቁ፡፡ ልጆችዎ ከእርስዎ በሚያገኙት ፍቅር፣ በየዕለቱ በሚደረግላቸው እንክብካቤና በተለያዩ መንገዶች አንዳቸው ሌላቸውን በልጠው ለመገኘት ስለሚጥሩ እርስዎ ከማገዝና መንገድ ከመምራት ባለፈ በፉክክራቸው መሐል ባይገቡ ይመረጣል፡፡

በአጠቃላይ ጥሩ ወላጅ መሆን ፈተናው እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለሚኖርባት ዓለም ብሎም ለተወለደበት ማኅበረሰብ አንዳች ቁም ነገር ማበርከት የሚችል ልጅ እንዲኖርዎ ጥሩ ወላጅ ለመሆን ራስዎን ያለማምዱ፡፡ ጥሩ ወላጅ የልጆቹን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች አሟልቶ በዕለት ተዕለት ሩጫቸው በጎውን መንገድ እያሳየ ወደ አሸናፊነት ሰገነት የሚያወጣ ነው፡፡ የእነኚህ ሁሉ ፈተናዎች ድል የሚሆነውም እርሱ ነውና ለፈተናዎቹ አሁኑኑ ታጥቀው ይነሱ፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe