አቋርጬ ወጣሁ !

እነሆ ውድ እናቴ ወ/ሮ በለጡ ሄይ (እማሆይ)የክብር እንግዳ ሆና መጽሐፉን መርቃለች!
ወዳጆች ተገኝተዋል፤አንጋፎች ዳቦ ቆርሰዋል፤ካባ አልብሰዋል። ቅንጭብ ታሪኮች ተነበዋል።የመጽሐፍ ስጦታ ተበርክቷል።
ወዳጄ መላኩ ብርሃኑ ደግሞ በጽሑፉ ድጋሚ አስለቅሶኛል። እንዲህ ሲል
አቋርጬ ወጣሁ !
ትናንት ግሮቭ ጋርደን ዎክ ነበር ያመሸሁት ። መጽሃፍ ለመመረቅ ።
ታምራት ሃይሉ “ዜሮ አመት የስራ ልምድ” በሚል ርዕስ ያሳተመውን ባለአነስተኛ ጥራዝ የአጫጭር ወጎች መጽሃፍ መረቅን። በኹነቱ ለመታደም የመጣውን ጋዜጠኛ ብዛት ላየ የጋዜጠኞች ማህበር ስብሰባ እንጂ የመጽሃፍ ምረቃ አይመስለውም።
ከወዳጆች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ተለዋውጠን፣ የትናንት የዛሬን አውግተን …..መድረክ አጋፋሪው መሰለ ስነስርዓቱ መጀመሩን ሲያበስር ጸጥ አልን ። ከጥቂት የመጽሃፉ ቅንጭቦች በኋላ የመናገር ተራው ለባለማዕረጉ ሆነና ታምራት መድረክ ላይ ወጣ።
ታምራት ያደረገው ነገር ግን ቃል አልቦ አድርጎ ከዚያ በላይ መቀመጥና ፕሮግራሙን መከታተል እንዳልችል አደረገኝ። አቋርጬ ወጣሁ!
ታምራት መናገር ጀመረ…”በዚህ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው መጽሃፉን የሚመርቁልኝ የክብር እንግዳዬ እንደለመድነው እንግዳ አይነት አይደሉም። ይህንን መጽሃፍ የምትመርቅልኝ…. ….” ብሎ ማይክራፎኑን እንደያዘ ጸጥ አለ። መጀመሪያ አካባቢ ማይኩ ድምጽ አላሰማ ብሎት መስሎኝ ነበር። ለመናገር እየሞከረ መልሶ ጸጥ ይላል። ለካ ታሜ እያለቀሰ ነበር። ሳጉ ድምጹን ውጦበት…እንባውን ለመቆጣጠር እየሞከረ ነበር። አልቻለም።

With Melaku Berhanu
መሰለ ማይኩን ተቀበለው…ያኔ ነፍሴ አንድ ነገር ገመተች። የገመትኩት ልክ ሆኖ አገኘሁት።
የታሜ እናት!
ያ ሁሉ ጋዜጠኛ፣ የጥበብ ሰው፣ ደራሲ …ታዋቂ ፊት ያለው ሁሉ በተገኘበት …በዚያ ደማቅ ስነስርዓት ላይ ታሜ መጽሃፉን እንዲመርቁለት በክብር የጋበዛቸው እናቱ ናቸው። እምዬ…
ይህንን ስንሰማ ሁላችንም በአክብሮት ከመቀመጫችን ተነሳን። የታሜ እናት ስማቸው ሲጠራ ከመድረኩ በስተግራ …በአንድ ታዳጊ በዊልቼየር እየተገፉ ብቅ አሉ። (ልጁ መሰለኝ ያ ታዳጊ)
እምዬ እድሜ ተጭኗቸው…ጉልበት ከድቷቸው…ህመም ደቁሷቸው በተሽከርካሪ ወንበር እየተገፉ …የልጃቸውን ክብር ለማየት መጡ።የምንኩስና ቆባቸው ከልሏችው…የካሜራው መብራት እያጥበረበራቸው…ከሁላችን ፊት ነገሱ።
ትዕይንቱን መቋቋም የሚችል አቅም አጣሁ። ታሜን እያየሁት ነበር። ከዚያ በኋላ ቃል ከአፉ መውጣት አልቻለም። መሰለ ከእማሆይ ጋር ጥቂት ለማውጋት ሞከረ…”በትምህርቱ ጎበዝ ልጅ ነበር” አሉ ለልጃቸው ሲመሰክሩ።
መሰለ ደግሞ ታሜ ለእናቱ ያለውን ፍቅር በሚያውቀው ልክ ተናገረ። ታሜ እለእናቱ ሲያወራ እንባ እንደሚቀድመው ጭምር። አሁንም መድረክ ላይ ያየሁት ያንን ነው። እንባው ንግግሩን ዘግቶበት ቃል አልባ ሆኖ መድረክ ላይ ቆሞ አየሁት። “ታሜ የማስተርስ ዲግሪ መመረቂያ ጥናቱን ሲሰራ እናቱ ሌሊቱን አብረውት ተቀምጠው ያበረቱት ነበር…” አለ መሰለ። እኔ ደሞ በአይነ ህሊናዬ የእምዬን አንጀት እየፈተሽኩ ነበር….ይኼኔ “ልጄ አንገቱን ደፍቶ እየለፋ እንዴት እኔ እንቅልፍ ወስዶኝ ልተኛ” ብሎ ለስኬቱ በምኞትና ጸሎት በሚቃትት ልባቸው አጠገቡ ቁጭ ብለው አየኋቸው። የእናት አንጀታቸውን እያሰብኩ ።
ለክብራቸው ብዬ…የታሜ እናት መጽሃፉን መርቀው ከመድረክ እስኪወርዱ ድረስ በወንበሬ ላይ ቆየሁ። ከዚያ በላይ ግን አልቻልኩምና ሌላው መርሃግብር ሳይጀመር በፊት ተነስቼ ወጣሁ።
የሰው ፊት አይታ …ጠቁራና ከስታ…ወጥታና ወርዳ ልጇን ለዚህ ያበቃች እናት በሰው ፊት ምስጋናና ሞገስ ሲቸራት ማየትን የመሰለ ምን ጸጋ አለ?…ለሁላችን የዛሬ ስኬት ምሰሶ የሆነችው እናት “መልኳ ጠፋ ፣ ጠቆረች …ጃጀች ፣ አቅም ከዳት” ሳትባል በህዝብ ፊት ልጇ በኩራት ጠርቶ አደባባይ ሲያውላት ማየትን የመሰለ ምን ልብ የሚነካ ነገር አለ?
ታሜዋ…መጽሃፍ ስለመጻፍህ አላደንቅህም። እስካሁን መቆየትህም የኔው ስንፍና ተጋብቶብህ ነው እላለሁ። እናትህን ያከበርክበት መንገድ ግን እንዳከብርህም እንዳደንቅህም አድርጎኛል። ትንፋሻቸው ኖሮ ያሙቁህ!! ድምጻቸው ጠርቶ ያበርታህ። በማምሻ ዘመንህ ልጆችህ ክበር!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe