አትሌት እጅጋየሁ ታየያለ አግባብ በ5ሺ ሜትር ውድድር እንዳትሳተፍ መከልከሏን አስታወቀች።

“እንዳልሮጥ ተከልክያለኹ!!”
ያለ አግባብ በ5ሺ ሜትር ውድድር እንዳትሳተፍ መከልከሏን አትሌት እጅጋየሁ ታየ አስታወቀች።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን ከወከሉ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው አትሌት እጅጋየሁ ታየ ፣ በ5ሺ ሜትር ርቀት ከማናቸውም የቡድን አጋሮቿ በላይ የተሻለ ሰዓት ቢኖራትም ያለ አግባብ በውድድሩ እንዳትሳተፍ በፌዴሬሽኑ አመራሮች እንደተከለከለች ለአሜሪካ ድምጽ አስታውቃለች።
በኦሪገን ኢዩጂን እየተደረገ በሚገኘው ውድድር ፣ ኢትዮጵያ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር በ ለተሰንበት ግደይ አማካይነት የወርቅ ሜዳሊያ ባሸነፈችበት ቀን ፣ ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረገው “እልህ አስጨራሽ” የቡድን ስራ በነበራት ተሳትፎ ትኩረትን ያገኘችው አትሌት እጅጋየሁ ፣ በ5ሺ ሜትር ከቡድን አጋሮቿ የበለጠ ፣ በ10ሺ ሜትር ደግሞ ሁለተኛ የሚያደርጋት የቀደመ ውጤት እንዳላት ተናግራለች። ይሁንና በ10ሺ ሜትር የታየውን የቡድን ስራ በ5ሺ ሜትር ውድድር በመድገም ሀገሯን ዳግም ባለ ድል ለማድረግ በተዘጋጀችበት ሰዓት በቡድኑ ሳትካተት እንደቀረች ፣ በምትኩ በተጠባባቂነት የተያዘች ሌላ አትሌት ተሳታፊ እንደተደረገች በመጥቀስ ቅሬታዋን አቅርባለች ።
ወደ ኦሪገን ያቀናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተፋራ ሞላ በበኩላቸው የአሁኑ ውሳኔ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ከመነሳቱ በፊት ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ያወሳሉ።
አትሌቶች በዋነኝነት ሊወዳደሩ የሚፈልጉበትን አንድ ርቀት እንዲመርጡ ከተደረገ በኃላ ኦሪገን ላይ በሚደረጉ የቀደሙ ውድድሮች ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ፣ በተጨማሪ ርቀት እንዲወዳደሩ ይህ ካልሆነ ግን በየርቀቱ ቀድሞውኑ የተደለደሉ አትሌቶች ብቻ እንዲሳተፉ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ይናገራሉ።
በወቅቱ አትሌት እጅጋየሁ በ5ሺ ሜትር የተሻለ ውጤት ቢኖራትም በ10ሺ ሜትር ለመወዳደር እንደመረጠች የሚናገሩት አቶ ተፈራ ፣በቀደመው ስምምነት መሰረት አትሌት እጅጋየሁ አሁን ላይ በ10ሺ ሜትር ውድድር ካስመዘገበችው አንጻር በ5ሺ ሜትር ዳግም ለመወዳደር ብቁ እንደማያደርጋት አስረድተዋል።
በምትኩ በሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ እና በ5ሺ ሜትር ለመወዳደር ቀድመው ምርጫቸውን ያሳወቁ እና ብቁ የሆኑ አትሌቶች እንዲወዳደሩ እንደተወሰነ አብራርተዋል ።ይሄ አሰራር ፣ ከቀደመው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የአሎምፒክ ተሳትፎ ትምህርት በመውሰድ ፣ የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ቡድን ለተሻለ ውጤት ለማብቃት ያለመ መሆኑን እና በሁሉም ዘንድ የተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe