አንጋፋዋ አርቲስት ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች

ከ1935 – 2015 ሂሩት “የወርቃማዉ ዘመን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንግስት” ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ ባሉት አመታት ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መካከል አንዷና ተወዳጅ ድምፃዊ ነበረች።

ሂሩት በቀለ ከድምፃዊነት ባሻገር ተወዛዋዥና እንዲሁም የግጥምና የዜማ ደራሲ ነበረች። ሂሩት በቀለ የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዋቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት ድምፃዊያን ወደ ሙዚቃው አለም ለመሳብና እንዲሁም ለድምፃዊነት ብቃት መነሳሻና አቅም መፈተሻ መሆናቸው ግልጽ ነው። ሂሩት በቀለ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፈ በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደች:: እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዮን ት/ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ተከታትላለች::

ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎርና ራፕ ማድረግ ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1951 ዓ.ም. በ16 አመቷ ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ በ 1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኞ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች::

ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኃላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ: የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት:: ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል አንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው “#ኢትዮጵያ” አንዱ ነው:: ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የቴአትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ­­­200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች ሲሆኑ: በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች:: ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው 35 አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች: ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል: ማህሙድ አህመድ፣አለማየሁ እሸቴ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ታደለ በቀለ፣ መስፍን ሀይሌ፣ ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል። ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኃላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል ሙሉ ጊዜዋንና ህይወቷን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከ28 ዓመት በላይ አገልግላለች።ሂሩት በቀለ የመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስትያን አባል ስትሆን: ሶስት የመዝሙር አልበሞችንም ለክርስትያን ወገኖቿ አቅርባለች። ሂሩት በቀለ በሙዚቃ አለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደሰታንና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም: የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ አድርጎ ያስደስታታል:: ሂሩት ከሙዚቃ ስራዋና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ፥ በጨዋታ አዋቂነቷ በቅርብ የሚያውቇት የስራ ባልደረቦቿ: ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ ይናገራሉ:: ሂሩት በቀለ 7-ልጆችና 10-የልጅ ልጆችን አፍርታለች:: ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽዎ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል: 1ኛ) ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ 2ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽዎ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር 3ኛ) በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ 4ኛ) በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት ሐገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽዎ ከቀድሞዎ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃማርያም እጅ ሰርተፍኬት 5ኛ) ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት 6ኛ) ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት 7ኛ) ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር 8ኛ) ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዚዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ 9ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት 10ኛ) ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት 11ኛ) ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ወዘተ ይገኙበታል።

ምንጭ B.I.N Media

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe