አይ ኤስ እና አልሸባብ የኢትዮጵያ ስጋቶች?

መነሻ

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿ ብዙ ናቸው፡፡ ያልተሰሩት የቤት ስራዎች ተከማችተውባታል፡፡ መሪዎቿና ህዝቧ ያከማቹላትን ፈተና በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሰርታ ለማጠናቀቅ የምትችል አልሆነችም፡፡ በአዲስ ተስፋ ማግስት እንኳ ባለችበት መርገጥን መርጣለች፡፡

አሁን በኢትዮጵያ አየሩን የተቆጣጠረው የከረረ የብሔርተኝነት መንፈስ ትልቁ የራስ ምታት ነው፡፡ ከሰሞኑ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይፋ እንዳደረገው ባለፈው 2011 ዓ.ም በመላ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች 1229 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በግጭቶቹ ሳቢያ 1,393 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይም የግድያ ሙከራ ተደርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ 2,290,490,159 (ሁለት ቢሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሚሊየን አራት መቶ ዘጠና ሺ አንድ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ብር ገደማ) የሚገመት የዜጎች ንብረት የወደመ ሲሆን፤ 1,200437(አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት) ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በግጭቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ 1323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ 645 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንና 667 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ እንዳልተያዙ፤ የ10 ተጠርጣሪዎች ክስም በምህረት መነሳቱን ተነግሯል፡፡

ጠቅላይ አቃቢ ህግ ለግጭቶቹ መነሻ የሆኑትን ነገሮች ባይገልጽም ከብሔር ጋር የተያያዙ እንደሆነ ግን መረዳ ይቻላል፡፡ ይህ ውስጣዊ ችግር እንዳለ ሆኖ ከውጭም ሌሎች ፈተናዎች ተደቅነዋል፡፡ የግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የምታነሳቸው ጸብጫሪ ጥያቄዎች አንዱ ሲሆን ሌላው ግን የአይኤስ እና የአልሸባብ አሸባሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ ነው፡፡ የዛሬው ሀተታም በዚሁ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡

አይኤስ እና አልሸባብ በኢትዮጵያ

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ላይ የነበሩ የተባሉ የአል-ሸባብና የአይ ኤስ ቡድን አባላት መያዛቸው የተገለጸው ከሰሞኑ ነው።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው አልሸባብ እና አይ ኤስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መግለጫ ከመውጣቱ አስቀድሞም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር ስላዋላቸው የአሸባሪ ቡድኑ አባላት መረጃ ሰጥቶ ነበር፡፡

የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጅግጅጋ፣ ድሬ ዳዋ፣ ሞያሌ እና ዶሎ ከተማዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ውስጥ መያዛቸው ታውቋል።

በተለያየ ሥፍራ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ የተጠየቁት ኮለኔሉ፤ “በቁጥር በጣም ብዙ ናቸው። መረጃው ገና ተጣርቶ አልደረሰንም” ብለው ነበር የኢታማዦር ሹሙ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮለኔል ተስፋዬ አያሌው።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሶማሊያ፣ የሶሪያ እና የየመን ዜጎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል። “አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች አማርኛ ቋንቋ ተምረው የተላኩ ናቸው” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አይኤስ በአማርኛ ቋንቋ የጽሑፍ መልዕክቶችን በቴሌግራም አማካኝነት ማስተላለፍ እንደሚጀምሩ ማስታወቂያ አሰራጭተው እንደነበረ ይታወሳል።

አይኤስ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ጫና እያሳደረ ነው? መከላከያስ ይህን ለመከላከል ምን እያደረገ ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮለኔል ተስፋዬ፤ “የአገራችን የደህንነት ጥበቃ ጠንካራ ስለሆነ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው መግባት ባለመቻላቸው፤ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነው የሚነዙት። ድንበር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እያደረግን ነው” ሲሉ መልሰዋል።

አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ለድንበር ቅርብ በሆኑ ከተሞች አቅራቢያ ከተቀጣጣይ መሣሪያዎች ጋር መያዛቸውን የሚናገሩት ኮለኔል ተስፋዬ፤ ከዚህ ቀደም የአይኤስ ተጠርጣሪ ነው ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል እንዳልነበረ ይገልጻሉ።

“ከዚህ ቀደም የአይኤስ አባላት የሆኑ ሰዎችን በሶማሊያ በቁጥጥር ሥር አውለናል። እነሱንም ለሶማሊያ መንግሥት ነው አሳልፈን የምንሰጠው” ብለዋል።

“ስልጠና ሲሰጣቸውና ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩም ጭምር መረጃው ነበረን” ያሉት ኮለኔል ተስፋዬ፤ የአይኤስ አባላት እንቅስቃሴን በተመለከተ መንግሥት መረጃ እንደነበረው ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በተለያያ ጊዜ እንደሆነ የተናገሩት ኮለኔል ተስፋዬ፤ ሁሉም የተያዙት አይኤስ በአማርኛ ቋንቋ ጽሑፎችን ማሰራጨት ከጀመረ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

“ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም፤ ሥራ ፍለጋ ከአገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገድ ላይ በመያዝ ‘ሥራ እንሰጣችኋላን’ በማለት እያታለሏቸው ስልጠና እየሰጧቸው ነው” የሚሉት ኮለኔል ተስፋዬ፤ “በኢትዮጵያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አብዛኛዎቹ የሶሪያ እና የየመን ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነማን ናቸው?

የመከላከያ መረጃ ይፋ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥጥር ስር የዋሉትን የአይኤስና አልሸባብ አባላትን ማንነት እና የት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት፤ የአል-ሸባብ የሽብር ቡድንን የሚመራው ሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት በሀሰተኛ ስሙ ያህያ አሊ ሃሰን በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የሙሐመድ አብዱላሂ ዱለት ግብረ አበሮች የሆኑት አብደክ መሃመድ ሁሴን፣ ሬድዋን መሃመድ ሁሴን እና በቅፅል ስሙ ስመተር መሀመድ ኢማን ዩሱፍ በመባል የሚታወቀው ጅቡቲ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከደቡባዊ ሶማሊያ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩት ይሳቅ አሊ አደን እና አደን ሙሃሙድ መሃመድ በቅፅል ስሙ አደን ቦራይ ሱማሊላንድ ውስጥ ተይዘዋል። ይሳቅ አሊ አደን ከሶማሌ ክልል ቦህ ወረዳ ጨርቃን ቀበሌ የተሰጠ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ የተገኘ ሲሆን፤ አደን ሙሃሙድ መሃመድ የሚባለው ተጠርጣሪ ደግሞ በስሙ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2.5 ሚሊዮን ተቀማጭ ብር ተገኝቷል።

መካከል ዒድ መሃመድ ዓሊ የተባለ ተጠርጣሪ በሶማሌ ክልል ጨርጨር ዞን አራርሶ ወረዳ፣ በሽር ዑስማን አብዲ በሶማሌ ክልል ፊቅ አከባቢ እንዲሁም ዑስማን አሊ ሁሴን በኦሮሚያ ክልል በሞያሌ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የአይ ኤስ አባል የሆነው ፋዕድ አብሽር የሱፍ ከቦሳሶ ሶማሊያ በሃርጌሳ ፑንትላንድ በኩል አድርጎ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በቁጥጥር ሥር ውሏል። ሙህመድ ጉሀድ ቡዲል የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ ሶማሌ ክልል በአፍዴር ዞን ምዕራብ ኢሚ ወረዳ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዉሏል።

ሌላ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባል የሆነ ሰይድ ዑመር ሸበሺ የተባለው ተጠርጣሪ በፀጥታ አካላት በአዋሽ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።

የሸብር ቡድኖችን በመከታተል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ በተካሄደው የኦፕሬሽን የጁቡቲ፣ የሶማሊላንድ፣ የፑንትላንድ፣ የአሜሪካ፤ የጣሊያን፣ የፈረንሳይና የስፔን የመረጃ ተቋማት እገዛ ማድረጋቸውን ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫው አሳውቋል።

የአይኤስ ታጣቂዎች ጥቃት

አሸባሪ ቡድኖቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እስካሁን ያደረሱት ጥቃት ባይኖርም በኢትዮጵያውያን ላይ ግን እጃቸውን መሰንዘር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ከአመታት በፊት በሊቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰውን ዘግናኝ ግድያ መርሳት አይቻልም፡፡

ከዚያ በተረፈ ደግሞ ባለፈው ዓመት በሶማሊያ የፑንትላንድ የንግድ ከተማ በሆነችው ቦሳሶ ውስጥ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በአይኤስ ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡ ቢያንስ አንድ ግለሰብ መቁሰሉም ተነግሮ ነበር።

ስለጥቃቱ በቀዳሚነት የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ታጣቂዎቹ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ይኖሩበታል በሚባለው ሳንቶስ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ ክፍል ውስጥ ባገኟቸው አራት ኢትዮጵያዊያን ላይ ተኩስ ከፍተው ነው ጥቃቱን የፈፀሙት።

አንድ ስማቸውን ያልጠቀሱ የአካባቢው ባለስልጣን ኢትዮጵያዊያኑ በተፈፀመባቸው ጥቃት መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ሲያረጋግጡ፤ አፍቃሬ አይኤስ የሆነ ቡድንም በትዊተር ገጹ ላይ ስለጥቃቱ አስፍሯል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የኤደን ባህረ ሰላጤን በትናንሽ ጀልባዎች በማቋረጥ ወደ የመንና የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት በህገ ወጥ መንገድ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች የቦሳሶን የባህር በር ይጠቀማሉ። በአካባቢውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እንደሚገኙ ተገልጿል።

እነዚህ በጥቃቱ የሞቱትና የቆሰሉት ኢትዮጵያዊያንም በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ባህሩን ተሻግረው በጦርነት ወደ የምትታመሰው የመን ለመጓዝ በቦታው የነበሩ ስደተኞች እንደሆኑ ይታመናል።

አልሸባብና የቂም ቋጠሮ

ምሥራቅ አፍሪካን በስፋት በሽብር ቀጠናነት ካስፈረጇትና ቀጠናውን የሥጋት ብሎም የጦርነት ቀጠና ካደረጉት በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል በሶማሊያ ወጣቶች የተመሰረተው “አል ሸባብ” የተሰኘ የሽብር ቡድን ነው። አል ሸባብ ሕንድ ውቅያኖስን ተንተርሶ የአፍሪካን ቀንድ በሥጋት ውሎ እንዲያድርና በምዕራባውያን ዘንድ “የሞት ቀጠና” እስከመባል የደረሰበት የሰላምና መረጋጋት እጦት ምንጭ መሆኑንም በርካቶች ይስማሙበታል።

ይህ ቡድን ውልደቱ ታላቋን ሶማሊያን ለመመስረት አስቦ ቅርብ ያደረውን የሶማሊያን አምባገነን መሪ ዚያድ ባሬ ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ አገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነቶች በመግባቷ ነበር። 1983 ግብዓተ መሬቱ የተፈፀመው የዚያድ ባሬ መንግሥት ሶማሊያን ግን ወደማትወጣበት እና የዕድሜ ልክ የቤት ሥራ አሸክሟት ነበር የሔደው።

በቀዳሚነት ሶማሊያን እና ጎረቤት አገራትን በተለይም ደግሞ ኬንያን እና ኢትዮጵያን የጦርነት ዓውድማ በማድረግ ግንባር ቀደሙ አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ የተባለው የዚያድ ባሬ መንግሥት ርዝራዥ ነበር። ይህንን ቡድን አሸባሪ ነው ብሎ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመፈረጅ አሜሪካንን የቀደማት አልነበረም። ጊዜው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር መንበረ መንግሥቱን በያዘበት ወቅት ላይ ነበር። ይህ እስላማዊ አክራሪ ድርጅት ኢትዮጵያን ለማተራመስ የቁጣ ሽመሉን በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ማሳረፍ የጀመረው። ለጦርነት እምብዛም አዲስ ያልነበረው የያኔው ኢሕአዴግ የጥቃት ቅልበሳውን በተሳካ ሁኔታ አሳክቶ በኦጋዴን አሸዋማ መሬቶች ላይ የአል ኢትሃድ አል ኢስላሚያን ግብዓተ መሬት ፈጽሟል።

የአል ኢትሃድን መዳከም ብሎም ወደ መቃብር መውረድ ተከትሎ ከደቡባዊ ሶማሊያ “አል ሸባብ” (የቃሉ ትርጉሙ ወጣቶቹ ማለት ነው) ጉልበቱን አጠንክሮ ብቅ አለ። ይህ ቡድን ከመንግሥት እኩል ግብር ይሰበስባል፣ የራሱ ምጣኔ ሀብት መደጎሚያ የንግድ ስርዓት አለው፣ በሕንድ ውቅያኖስ የሚያልፉ የኀያላን አገራት ንብረት የሆኑ የንግድ መርከቦችን ሳይቀር በማገት ተደራድሮ በርካታ ዶላሮችን ያፍሳል። ይህ ብቻ ሳይበቃው በሶማሊያ በተለይም ደግሞ ከመናገሻዋ ሞቃዲሾ እስከ ወደብ ከተማዋ ኪስማዮ ድረስ ጠንካራ መረቦችን ዘርግቶ የተለያዩ የኑሮ ስርዓቶችን በመገንባት የሕዝቡን ኑሮ በስቃይ የተሞላ እንዲሆን ማድረጉ የሚታወስ ነው።

አል ሸባብ በአገር ውስጥ ብቻ ሳያበቃ በኢትዮጵያ ላይ ከአንዴም ሰባት ጊዜያት ጅሃድ አውጇል።

የምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ክንፍ በማለት ራሱን ከአልቃይዳ ጋር የሚያስተሳስረው አል ሸባብ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000 ግን ቀጥተኛ እና የተደራጀ ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ በማወጅ እብሪቱን ጎረቤቱ በሆነቸው አገር ላይ አሳይቷል።

በዚህ ጊዜ ግን እንደቀደሙት ዓመታት ወራሪው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ እስኪገባ አልተጠበቀም። የጦርነቱ ዓውድማ በራሱ በአል ሸባብ ሜዳ ላይ ለማድረግ የኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሙሉ ትጥቁን ይዞ ወደ ሶማሊያ ተመመ። በርካታ ወታደሮችን ኢትዮጵያ መስዋዕት ብታደርግም፥ አል ሸባብ በስፋት ተቆጣጥሮት ከነበረው ሞቃዲሾ እና አካባቢዋ ለመሸሽ በመገደዱ ወደ ትውልድ አገሩ ኪስማዩ አፈግፍጓል።

ለቀጥታ ፍልሚያ ሶማሊያ የገባው የኢትዮጵያ ጦርም ሶማሊያን በማረጋጋቱ ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራትና የአገሪቱን የፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት በመመልመል እና በማሰልጠን በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ነፃ የወጡ መሬቶችን በማስረከብ ወደ መንግሥት አስተዳደር እንዲገቡ አድርጓል። በእነዚህ ዓመታት ግን ኢትዮጵያ ከአልሸባብ ጋር ባደረገችው የሞት ሽረት ትግል በርካታ የሰራዊት አባላትን ገብራለች፣ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብም ወጪ አድርጋለች።

ማንሰራራት

ከዓመታት በኋላ የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ከፍተኛ ተልዕኮ ያለውን የሰላም አስከባሪ ጦር በማዝመት የሶማሊያን ዘላቂ ሰላም ለማጎናጸፍ ያላሰለሰ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የሽብርተኛ ቡድን በቀደሙት ዓመታት የነበረውን የተዳከመ አቅም አሰባስቦ እያንሰራራ ብሎም እየጎለበተ ይመስላል። የገጠር ትግሉን በመተውም ከተማ ላይ በማተኮር የትርምስ ተግባሩን እያጧጧፈ ይገኛል።

ከጊዜ ወዲህ በዋና ዋና ከተሞች ላይ በዛው በሶማሊያ የሚያደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ከዚህ ቀደም ወደ ገጠሩ አካባቢ የነበረው ይዞታው በአሚሶም እና ጥምር ኀይሎች ስለተወሰደበት ወደ ከተማ አባላቶቹን አስርጎ በማስገባት ጥቃቶች እየፈፀመ ይገኛል፡፡

በቅርቡ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የከንቲባ ቢሮ አቅራቢያ በአንዲት እንስት አጥፍቶ ጠፊ በተፈፀመ ጥቃት የተማዋ ከንቲባ በፅኑ ጨምሮ በርካቶች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አለም አቀፍ የዜና አውታሮች እየተቀባበሉ ሲዘግቡት የነበረ ጉዳይ ነው። ጥቃቱንም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን የወጣቶቹ ቡድን አልሸባብ አፍታ ሳይቆይ መውሰዱን አስታውቋል።

በዚህ ጥቃት የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ አብድረህማን ኦማር ኡስማንን እስከ ወዲያኛው እንዲያሸልቡ አድርጓል። ከንቲባው ጥቃት በደረሰባቸው ወቅት ለተጨማሪ የሕክምና ዕርዳታ ወደ ኳታር አቅንተው የነበረ ቢሆንም ሐምሌ 25/ 2011 ከወደ ዶሃ ዜና ዕረፍታቸው ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ ስጋት

በሰላም ማስከበሩ ረገድ የተሰማሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦራቸውን መጠን በአንድ ሺሕ ለመቀነስ በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ላይ መወሰኑ አል ሸባብ ተመልሶ ቀድሞ ያጣቸውን ቦታዎች ለመያዝ ከፍተኛ ዕድል እንደሚሰጠው ይታመናል።

ከአዲስ ማለዳ መጽሔት ጋር ቆይታ ያደረጉት ማርቲን ፕላውት የኢትዮጵያ ኦጋዴንን ለመጠቅለል ታስቦ በነበረው ጦርነት ሶማሊያ ጦር በለስ ባይቀናው እና እንደተዳከመ ቢቆይም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ መከፋፈል የቀደመውን የሶማሊያን ምኞት ሊያሳካ የሚችልበትን ዕድል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደዒላማ አይኤስ ነፃ የሚያወጣቸውንና ካሊፌቱን የሚያውጅባቸውን አገራት በገለጸበት ካርታ ላይ እንዳስቀመጠው፣ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዒላማ ናት።

Ethiopia’s Strategic Importance: US National Security Interests at Risk in the Horn of Africa September

12 በሚል ርዕስ ላይ እንደሚነበበው ትንታኔ፣ ለአልቃኢዳ የሚታዘዘው አል ሸባብም ሆነ፣ አይኤስ ከኢትዮጵያ ግዛቶች ቆርሶ በመውሰድ ታላቋን ሶማሊያ መፍጠር ላይ ልዩነት የላቸውም። ኹለቱም እንግሊዞች ቀብረውት የሔዱትንና ኋላ ላይ ዚያድ ባሬ ሊያፈነዳው የሞከረውን የታላቋ ሶማሊያ ፕሮጀክት ይደግፉታል።

ይሁን እንጂ አል ሸባብ ከአይኤስ በበለጠ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመማረክ እየሠራ ነው። ለዚህም ከቡድኑ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ አፋን ኦሮሞ እንዲሆን ወስኖ በዚሁ ቋንቋም የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጣ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አል ሸባብ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ ለወትሮው ከሱማሊኛ በተጨማሪ ይጠቀም የነበረው ቋንቋ እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ስዋሒሊ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አፋን ኦሮሞም ተጨምሯል። ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና የተከፉ ወጣቶችን ትኩረት ለመሳብ የተከተለው ዘዴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በዚህ ረገድ አይኤስ ግልጽ ነገር የለውም። በሚታወቁት ልሳኖቹ (‘አማቅ’ እና ‘ዊላያት’) በሶማሊያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የለቀቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ሆኑ ጽሑፎች አዘውትሮ ከሚጠቀምበት ቋንቋ ተሻግሮ እንደ አል ሸባብ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ሲጠቀም አልተስተዋለም።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe