ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም ምሽት 4:30 ሰዓት አካባቢ የሰሜን ዕዝ፣ አዲስ አበባ ከተማ ተቀምጠው በሕወሓት ሕገወጥ የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈጸምበት አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ዛሬ ታህሣሥ 21 ቀን 2013 ዓም ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
ከሕወሓት ሕገወጥ ቡድን ተልዕኮ በመቀበል አዲስ አበባ ተቀምጠው በሰሜን ዕዝን ላይ ጥቃት እንዲፈጽምበት አድርገዋል ተብለው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት፣ ሻለቃ እብዪ ገብረመድህን፣ ሌተናል ኮሎኔል አስረስ በርለሄ፣፶ አለቃገብረመድሕን ማዕረግ ንጉሴና ኮሎኔል ሰለሞን ገብረሚካዔል ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ስለተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ከህወሓት ሕገወጥ አባላት ተልዕኮ በመቀበል በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም አዲስ አበባ ተቀምጠው ሲያመቻቹ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን አስታውቋል። ሻለቃ ዕብዩ ገብረመድሕን የተባሉት ተጠርጣሪ፣ በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ላልተገባ ተግባር በማዋል በወንጀል ድርጊቱ መሳተፋቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መሰብሰቡን አክሏል።
ተጠርጣሪው የመከላከያ ኮንስትራክሽን መስሪያ ቤት የስካቫተር ኦፕሬተር ሆነው በሚሰሩበት ወቅት በአፋር አካባቢ ከሚገኙ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ጋር በመተባበር፣ ምሽጎችን ሲገነቡ እንደነበርም አክሏል።
ኮሎኔል ሰለሞን ገብረሚካኤል የተባሉት ተጠርጣሪ፣ ደግሞ የደቡብ ዕዝ የራዲዮ መገናኛ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን መርማሪ ቡድኑ አክሏል።ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማካሔድ፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የመርማሪ ቡድኑን ሪፖርት በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የተቃውሞ አቤቱታ እንደተናገሩት፣ መርማሪ ቡድኑ “ጠረጠርኳቸው ፣ያለው ወንጀል እኛን የሚገልጽ አይደለም፣ በመሆኑም መንግስት በነፃ ወይም በዋስትና ሊለቀን ይገባል” ሲሉ ተከራክረዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ “ተጠርጣሪዎቹ ከነበራቸው ወታደራዊ ጥበብና ሃላፊነት አንፃር ማስረጃ ሊያጠፉ ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸው ሊከበር አይገባም” በማለት ተከራክሯል።
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት፣የተጠርጣሪዎቹን የክርክር ሃሳብ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናት ፈቅዶ ለጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

