አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለ ክብር ዶክትሬት ዲግሪ አሰጣጥ ምን ይላል?

‹‹የክብር ማስትሬት ድግሪ እንደሚሰጥ ያውቃሉ?››
የሰሞኑን የዓመቱ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ታኮ አንዳንድ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ድግሪ በሙያቸው አስተዋፅኦ አድርገዋል ላሏቸው ግለሰቦች ሰጥተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ድግሪ ተሸላሚ ግለሰቦች ዙሪያ የተለያዩ ብዥታዎችን መነሻ በማድረግ ቁም ነገር መፅሔት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የክብር ዶክትሬት ድግሪ አመራረጥ መስፈርት ጠይቃለች፡፡
በዚሁ መሠረት ዩኒቨርሲቲው በፅሑፍ የላከልንን ማብራሪያ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡
ዓላማ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች ለሀገራቸውና ለመላው ዓለም በእውቀታቸውና በሙያቸው የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች እውቅና ለመስጠት የሚደረጉ ናቸው፡፡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ
1ኛ/ በተልእኮዎቹ ውስጥ ለተካተቱ የእውቀትና ሙያዊ የስራ ውጤቶች መርሆዎች መጠበቅ ያለውን ፅኑ አቋም ያረጋግጣል፤
2ኛ/ ለእውቀትና ለኪነጥበብ እድገትና መበልፀግ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች ክብርና እውቅናን ይሰጣል፤ እንዲሁም
3ኛ/ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸው ግንኙነትና ህብረት ለዩኒቨርሲቲው ክብርና እውቅናን ለሚያመጡ ግለሰቦች እውቅናን ይሰጣል፡፡
ትርጓሜ
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የከፍተኛ ትምህርት አንዱ ዋነኛ የስራ ፍሬ የሚገለጥበት ማረጋገጫ ነው፡፡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በአካዳሚኩ ዘርፍ የተለመዱትን መስፈርቶች ማለትም የትምህርት ኮርሶችን መውሰድንና ፈተና ማለፍን የመሳሰሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትን አይጠይቅም፡፡ ዲግሪው የዶክትሬት ዲግሪ አለያም ማስትሬት ዲግሪ ሊሆን ይችላል፡፡የክብር ዲግሪው ዶክትሬት ይሁን ወይስ ማስተርስ የሚለውን ሴኔቱ ይወስናል፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እጩዎች ከሌሎች ሰዎች የሚለያቸው የተለየ ባህርይና የስራ አፈፃፀም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው፤ የክብር ዲግሪውን በመቀበላቸው ለዩኒቨርሲቲው ክብርና ሞገስን የሚያመጡ ናቸው፡፡
መስፈርቶች
ለዩኒቨርሲቲው ዓላማዎች መሳካት የተሰጡ፤ ለአካባቢያቸው፤ ለሀገራቸውና ለመላው ዓለም በተለያዩ መስኮች ለምሳሌ በሕዝባዊ ማህበራት፤ በእውቀት ዘርፍ ስራዎች፤ በስፖርት፤ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ወይም በኪነ-ጥበብ የላቀ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ግለሰቦች ከሚከተሉት መስፈርቶች ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ካሟሉ ለክብር ዶክትሬት ዲግሪው ይታጫሉ፡፡
1. በተወሰነ የትምህርት /እውቀት/ መስክ ብልጫ ያለው /የላቀ መሆን፤
2. በሙያ ወይም በግል ችሎታ የላቀ የስራ ውጤት ያስመዘገበ መሆን፤
3. ለህብረተሰብ ጠቃሚ ዘላቂ አስተዋፅዖ ማበርከት፤
4. ለዩኒቨርሲቲው ወይም ለሀገር ወይም ለመላው ዓለም ጠቃሚ የሆኑ ልዩ የበጎ ፈቃድ ስራ ማከናወን፤
ለእጩነት የሚበቁ ተገቢውን መስፈርት በሚገባ የሚያሟሉ ግለሰቦች ለእጩነት ይበቃሉ፡፡
ለእጩነት የማይበቁ
1. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክና አስተዳደር ስታፍ አባላት ዩኒቨርሲቲውን ከለቀቁ ቢያንስ ሶስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በእጩነት ሊቀርቡ አይችሉም፤
2. ዩኒቨርሲቲው በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ ለመከላከል /ለመጠበቅ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በስራ ላይ ላሉ ፓርላማ አባላት፤ ለመንግሥት ባለስልጣናት፤ እያገለገሉ ላሉ የዩኒቨርሲቲው የአመራር ቦርድ አባላት እና ለከፍተኛ ትምህርት ባለስልጣናት አይሰጥም፤ እነዚህ በእጩነት ሊቀርቡ የሚችሉ የስራ ዘመናቸውን ጨርሰው ከሀላፊነታቸው ከለቀቁ ከሁለትና ከዚያ በላይ ዓመታት ከሆናቸው ብቻ ነው፤
3. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የEmeritus ማእረግ ያለው የአካዳሚክ አባል በላቀ የስራ ውጤት ወይም በሁለተኛ የሙያ /የሥራ መስክ የላቀ ውጤት ካላስመዘገበ በስተቀር በእጩነት ሊቀርብ አይችልም፤
4. ለክብር ዶክትሬት ዲግሪው የሚታጭ ሰው በሕይወት ያለ መሆን አለበት፤ ምናልባት ግለሰቡ ለሽልማቱ ከታጨ በኋላ ሽልማቱን ሳይቀበል ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ሽልማቱ ለቤተሰቡ ይሰጥለታል፤
5. በልዩ አስገዳጅ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸላሚዎች የሽልማቱ ስነ- ስርዓት በሚከናወንበት ስፍራ በአካል በመገኘት ሽልማቱን መቀበል አለባቸው፤ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሽልማቱ ስነ-ስርዓት ቦታ ለማይገኝ እጩ ተሸላሚ በሌለበት አይሰጥም፤
የዩኒቨርስቲው የእጩ አመራረጥ መመሪያ
1. ፕሬዚዳንቱ፤ ም/ፕሬዚዳንቶች እና የአካዳሚክ ስታፍ አባላት ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ እጩዎችን ይጠቁማሉ፤
2. ግለሰቦች ራሳቸው ለክብር ዶክትሬት ዲግሪው ሽልማት ማመልከት ይችላሉ ወይም ደግሞ በሌላ በሶስተኛ ወገን ሊጠቆሙ ይችላሉ፤
3. አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ፕሬዚዳንቱ የተጠቋሚዎችን ሰነዶች ለሚመለከታቸው ኮሌጆች ዲኖች በማቅረብ በኮሌጆቹ አካዳሚክ ኮሚሽን እንዲፀድቅ ሊያስደርግ ይችላል፤
4. ፕሬዚዳንቱ ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ጋር በመመካከር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል፤
5. የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ ጥቆማዎች እንዲያቀርቡ ጥሪ ያደርጋል፤ በኮሌጆችም በኩል ተገቢ የሆኑ ግለሰቦችን በመጠቆም የዩኒቨርሲቲውን ደረጃና ታላቅነት ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ መከናወን አለበት፡፡
6. እጩዎችን ለመጠቆም ከሚያስፈልጉ ሰነዶች ውስጥ የሚከተሉት መቅረብ አለባቸው፤ ሀ/ ጥቆማውን ከሚያደርገው የአካዳሚክ ስታፍ አባል የተጠቋሚውን አስተዋፅዖና ከሌሎች ለየት የሚያደርገውን የስራ ውጤት የሚያስረዳ የጥቆማ ደብዳቤ፤ ለ/ አስፈላጊ ከሆነ የኮሌጁ ዲን ጥቆማውን ያፀደቀበት ማስረጃ፤ ሐ/ የተጠቋሚው የሕይወት ታሪክ ወይም ካሪኩለም ቪቴ፤ መ/ የተጠቋሚውን ትምህርት ስልጠናና ልምድ በአጭሩ የሚያስረዳ አንድ ገፅ ማብራሪያ፤ ሠ/ የድጋፍ ደብዳቤዎች፤ ጥቆማው የፀደቀበትን ሰነዶች ሊያካትት ይችላል፤ ሰ/ ጠቋሚው ስለተጠቋሚው ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ ኮሚቴው በቃል አጭር መግለጫ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፡፡
7. ጥቆማዎች መደረግ ያለባቸው ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ነው፤ ፕሬዚዳንቱ ከዩኒቨርሲቲው ማኔጀመንት ኮሚቴ አባላት ጋር በመመካከር ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ ኮሚቴ ግብአት እንዲሆን ጥቆማዎችን እያጣራ ተጠቋሚዎችን ለይቶ ያስቀምጣል፤
8. የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ኮሚቴ የተጠቋሚዎችን የትምህርት ደረጃ ስልጠናና ልምድ ይመረምራል፤ ለፕሬዚዳንቱም ኮሚቴው በእጩነት የመረጣቸውን ያቀርባል፤ ኮሚቴው ለእጩነት የሚያቀርባቸውን ተጠቋሚዎች የሚመርጠው በድምፅ ብልጫ ነው፤
9. በክብር ዶክትሬት ዲግሪ ኮሚቴ ከተመረጡት እጩዎች ውስጥ ፕሬዚዳንቱ ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ኮሚቴ፤ ለሴኔት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ለሴኔት አጠቃላይ ጉባኤ የተመረጡትን እጩዎች ለማፅደቅ ያቀርባል፤
10. በሴኔቱ ከተመረጡት እጩዎች ውስጥ ፕሬዚዳንቱ እጩዎችን መርጦ ለአመራር ቦርዱ እንዲያፀድቅ ያቀርባል፤
11. አንድ እጩ ሽልማቱ እንዲሰጠው በተወሰነበት ዓመት ውስጥ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን መቀበል ካልቻለ በሚቀጥለው ሁለት ተከታታይ ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሽልማቱን ለመቀበል ይችላል፡፡
12. የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በተማሪዎች ምረቃ ስነሥርዓት ላይ ወይም ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ ስነስርዓት ላይ ይሰጣል፤
13. በአመራር ቦርዱ እስኪፀድቅ ድረስ ለክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተመረጡ እጩዎች ስም ዝርዝርና ጉዳይ በአጠቃላይ በምስጢር ተይዞ ይቆያል፡፡

የስም አጠራርንም በተመለከተ በግለሰቦቹ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በማዕረጉ መጠራት የሚፈልጉ ተሸላሚዎች ‹የክብር ዶክተር› የሚለውን በማስቀደም መጠራት የሚችሉ ሲሆን በአካዳሚው ዘርፍ  በጥናትና ምርምር ውስጥ አልፈው የሶስተኛ ዲግሪ እንዳገኙት ሰዎች ዶ/ር እከሌ ተብለው መጠራት አይችሉም፡፡  ለምሳሌ የክብር ዶክተር ጥላሁንን ገሠሠ / Honorable Dr. Tilahun Gessess/ማለት ይቻላል እንጂ ‹ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ› ብሎ መጥራት አይቻልም፡፡

ምንጩ:-  ቁምነገር መፅሔት 13 ኛ ዓመት ቅፅ 13 ቁጥር 184 2006/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe