ታላቁ ተቃርኖ “አጼ ምኒልክ ሰርተው ያለፋት በትክክል ምንድነው?”
ርዕስ : ታላቁ ተቃርኖ
ደራሲ : ሃብታሙ አለባቸው
ዘውግ : ጥናታዊ የምርምር
የሕትመት ዓመት : 2009 ዓ ም
የገፅ ብዛት : 390
ታላቁ ተቃርኖ “አጼ ምኒልክ ሰርተው ያለፋት በትክክል ምንድነው?” በሚል ተጠየቅ ይጀምራል። በመግቢያው ላይ ለምን ይሄንን ጥናት ለማድረግ እንደ ተገፋፉ እንደሚከተለው ይጠቅሳል:- “በ2008 ዓ/ም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንግዳ ክስተቶችን ያስተናገደ ነበር። የጽጥታ መደፍረስና የሕዝብ ቁጣ ማየል አገራዊ መዋቅሩን ተፈታትኖታል። ምንም እንኳ አመጹ ገና ደርዝ ያላቸው ጥናቶች ያልተሰሩበት ቢሆንም የበርካታ ፖለቲካ ተንታኞች ምልከታ አልተነፈገውም። ዓለም አቀፍ መገናኛ ሚዲያዎች ሰፊ ጥናት ሰጥተውታል። በመጋቢት ወር 2008 ላይ የአልጀዚራ ጣቢያ ስለ ሁከቱ በስፋት ሲዘግብ ያስቀመጠው መጠየቅ ለእኔ አንኳር የምርምር መነሻ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። Does it mean that Ethiopia’s model has failed? ይለል የመጠይቁ አስኳል።” በማለት ይጀምራል። ደራሲው በጥያቄ ይጀምረና ለጥያቄዎቹ በቂና የተብራራ ምላሽ በሰፊው እየሰጠበት ይሄዳል። ለምሳሌ አገር ማለት ምንድነው? አገሮች ሲመሰረቱ አምስት ዓይነት አላባዊያን አሉት ኢትዮጵያ ከአምስቱ የቱን አመስራረት ተከተለች? እያለ በዘመን እየከፈለ ይተነትናል። በአጭሩ ሲገለጽ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ከሆነች በኋላ ኔሽን ቢውልድንግ አላደረገችም ነው። ሕዝቦቹን ወይም ብሔሮቹን ከማቀራረብ ይልቅ እንዲገፋፉ ተድርጓል ነው።
ታላቁ ተቃርኖ በ 15 ምዕራፎች ተከፋፍሎ እና በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጠ ፖለቲካዊ ታሪካቸውን እና ተቃርኖአቸውን ይዞ የመጣ ሲሆን በአንደኛው ምዕራፍ ከመጀመሪያው ሩብ ክ/ዘመን እስከ ፍፃሜ ኃይለሥላሴ ወዲህ፣ በምዕራፍ 2 ከአገር ምስረታ እስከ ታላቁ ተቃርኖ (የዕይታ ማዕዘን)፣ በምዕራፍ 3 የኢትዮጲያ ሐገረ-መንግስት ምስረታ ታሪካዊ ዳሰሳ፣ በምዕራፍ 4 “የታላቁ ተቃርኖ” ዕድገት፣ ኢትዮጲያ ምን ይታይሃል፣ እስከ አቅመ-ሐገረ መንግስት፣ በምዕራፍ 5 አዲሱ “የብሔር ግንባታ ተግባር” ተልዕኮ እና “ዘ ፎረም ኢትዮጲያነም” እስከ አፄ ኃይለሥላሴና የጨዋታው ህግ አጠቃቀም፣ በምዕራፍ 6 የጨዋታው ህግ አፈፃፀም፣ እኛና ሌሎች እስከ ወንዙ ቢሞላም ባይሞላም፣ ምዕራፍ 7 “አዘማኝነት”፣ ፖሊሲውና ውጤቱ እስከ የውድቀቱ ዋዜማ፣ ምዕራፍ 8 ከብሔር ግንባታ አዲስ ፕሮጀክትና ኀልዮታዊ እሰጣ ገባው እሰከ ኢትዮጲያ በፍሬ-ነገርነት እንዴት ትገለፃለች፣ ምዕራፍ 9 የታሪክ ትምህርትና የታሪክ አጻጻፍ ውርሳችን እሰከ ትውፊታዊ ጽንሰ-ሀሳቦች በዘመናዊ ዓለም ውስጥ፣ ምዕራፍ 10 የአፄ ምኒልክ ታሪክ አተረጓጎምና ውዝግቡ እሰከ ታክና ማራል ምንና ምን ናቸው፣ ምዕራፍ 11 ኢትዮጲያ፣ ታላቁ ተቃርኖና ኀልዮት ፍለጋው፣ ደርግስ ምን ይላል እስከ ከመሀል ወደ ዳር የማገንገጥ ዝንባሌ፣ ምዕራፍ 12 ህወሓት እና ታላቁ ተቃርኖ፣ የህወሓት የኤርትራ ፖሊሲ እስከ “ተምኔታዊው ማኀበረሰቡ፣ ምዕራፍ 13 ጉዞ ወደ መሃል አገር፣ መዋቅራዊ አተያይ/መልስ እስከ ከደቡብ አንጻር፣ ምዕራፍ 14 ኢህአዴግ/ ህወሓት ሦስተኛው “ሬዢም”፣ ድህረ-1983 እስከ ፌዴራሊዝም አዲሱ የጨዋታ ሕግ፣ ምዕራፍ 15 ኢትዮጲያ ዛሬና ነገ፣ ዕድገትና ተቃርኟዊ መዘዞቹ እስከ ዞጋዊ የሐብት ክፍፍልና ፖለቲካዊ ጦሱ በሚሉ ምዕራፎች ተከፋፍሎ ተቀምጧል፡፡
ሃብታሙ ተወደደም ተጠላ፣ ኳሷ የምትገኘው በኢሕአዴግ ሜዳ ላይ እንደሆነ ያመላክትና ተመትታ ስትንከባለል ወይም ስትለጋ የምትይዘው አቅጣጫ ከተጋጣሚው ተቃራኒ ቡድን አንጻር በኢሕአዴግ በራሱ የጨዋታ ብቃት፣ እውነተኛ ቅንነትና ዉስጣዊ አንድነት (Integrity) ይወሰናል ይላል። ኳሷ አራት አቅጣጫዎችን ይዛ ልትንከባለል ትችላለች በማለት ትንቢታዊ ሃሳብ ያቀርባል።
“አንደኛው፣ በግሩም የጨዋታ ብልጫ ተቃራኒ ቡድንን አልፋ መረብ ላይ ታርፋለች። ሁለተኛው፣ _ እጅግ ደካማ በሆነ የአጨዋዎት ብቃት ምክንያት ኳሷ በኢሕአዴግ የዓመታት ስህተት በራሱ ግብ ላይ ልታርፍም ትችላለች፡፡ ሦስተኛው፣ በዚያው በኢሕአዴግ ሜዳ ላይ በተጫወቾቹ ዐቅም መስተካከል፣ የተጫዋችና የአሰላለፍ ለውጥ በማድረግ ወይም በሌላ ምክንያት ኳሷ ወደ ፊትም ወደ ኋላም ሳትመታ _ ባለችበት ስትሆን ነው። አራተኛው፣ _ ከሜዳ ውጭበመለጋቷ፣ በብልሐት ማነስ፣ በዲስፒሊን ጉድለት፣ በተጫዋቾች ወይም በተመልካች ብጥብጥ ወይም ከጨዋታው ሕግ በተቃራኒ በተፈጠረ ችግርምክንያት ጨዋታው ለአጭር _ ወይም ለረጅም ጊዜ ሲቋረጥ ነው። አነዚህ አራት አቅጣጫዎች የኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ኩነቶች (Scenarios) መነሻ ማእዘኖች አድርገን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡”
በዚህ መፅሐፍ ምዕራፍ አራት ላይ ከ”ታላቁ ተቃርኖ እድገት” ቀንጭበን ስንመለከት “አንደኛው የንጉሠ-ነግሥቱ አገዛዝ ራሱ ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ ያለው ወቅት ነው ይህም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ የቀለጠ ነው ማት ይቻል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከህልፈታቸው በኋላ እስከ አሁን ዘመንና ወቅት ድረስ የታየው የታሪክ አተረጓጎም፣ ግጭትን ቅራኔ ነው፡፡ ሁለቱ ዘመናት በብዙ ምክንያቶች በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡፡ ዘመናዊነት ሐገረ-ኢትዮጲያን የመፍጠሩ ሂደት በታሪካዊ መገጣጠም ምክንያት በአፄ ምኒሊክ ዘመነ-መንግስት ከሞላ ጎደል መጠናቀቁ ምራንን የሚለያይ አይመስለኝም የእሳቸው ተተኪዎች ይህ ኃላፊነት አልነበረባቸውም፡፡ የእነርሱ ዋነኛ ተልዕኮ ብሔረ-ኢትዮጲያን መገንባ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን የ20ኛው ክፍለ-ዘመን ታሪካችን ከዚህ በተቃራኒ የሚገልጽ ነው፡፡ ቀጥለው የመጡ መንግስታትና ትውልዶች ከብሔር-ግንባታ ይልቅ “አለቀ፣ደቀቀ….” በተባው በሐገረ-መንግስት ምሥረታ ሥራ የተጠመደ መሆኑን እናያለን፡፡ ይህም የኢትዮፒን በሕልውና ማስቀጠል ተብሎ ሊገለፅ ይችላ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? በምዕራፍ አንድ የተመለከትናቸው ልዩነቶችና መራራ ወቀሳዎች እስከመቼ ይቀጥላሉ? እነዚህ ቅሬዎች ሊደበቁ ወይም እንደሌሉ ሊቆጠሩ አይችሉም፡፡ ከትውልድ ትውልድ መተላፋቸውንም ማንም ሊገታው አይችልም በመንፈሳዊ ኩትኮታ ለሐገረ-መንግስቱ ሕልውና ፈተና እንዳይሆኑ ማድረግ ግን ከአቅም በላይ የሆነ ሥራ ወይም ተልዕኮ አይደለም፡፡ ይህንን በንቃት እየተከታተሉ ማከናወንን ነው እንግዲ የኢትዮጲያ የብሔር-ግንባታ ሠራ ምሶሶ ነው የምንለው፡፡ ስለዚህም የአፄ ምልክ ወራሾችና ተተኪዎች እስከአሁኗ ኢትዮጲያ ድረስ ተልዕኳቸው ይህ ነው፡፡ ብሐየር ግንባ በየትኛውም ዓለም ተመሳሳይት አለው ቢባልም ልዩነት የለም ማት ግን አይደለም፡፡ አሜሪካና ሶማሊያ የህሐየር ግንባታ ሥራቸው በምንም መለኪያ ተመሳሳይ ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡” እያለ ይቀጥላል፡፡
ሀብታሙ አጼ ምኒልክ ታላቁን የመንግስት ምስረታ ቢያሳኩም ከዚያ በኋላ የመጡት መሪዎች ስለአንደነታችን አልስበኩም ሲል ይሞግታል ፡፡“አሁን ላይ ጥያቄው አገሪቱን ከአስፈሪው መጻኢ አደጋ ለመታደግ በቂ ጊዜ አለን ወይ ነው? ጥያቄው በዚህ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥም ኾኖ አገራችን ጀምራ ያላጠናቀቀችውን ብሔረ-ኢትዮጵያ-ግንባታን ለማጠቃለል የሚረዳትን ሰላም፣ ዕድልና ሁኔታ መፍጠር የሚችል ብልህ መሪ አላት ወይ? ነው።” በዚህ ጥያቄ ሐሳቡን የሚዘጋው ታላቁ ተቃርኖ የሀገረ መንግስቱን ምስረታ እና ግንባታ ፣ ከታሪክ ፣ ከማሕበራዊ፣ ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሳይንሳዊ ምልከታዎች ጋር እያዛመደ እውቀት ያስጨብጠናል።
Reviewer : Permanent staff editor at Think Ethiopia

