የኢራን መከላከያ ምክር ቤት በደቡባዊ የሀገሪቱ የባሕር ዳርቻዎችና ደሴቶች ላይ ማንኛውም ዓይነት የምድር ወረራ የሚፈጸም ከሆነ፣ በመላው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ የባሕር ፈንጂዎችን እንደሚቀብርና መተላለፊያዎችን እንደሚዘጋ አስታውቋል።
የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ እንደዘገበው፣ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ለማስገደድ የኻርግ ደሴትን የመውረር ወይም የመዝጋት ዕቅድ እያጤነ ነው። ይህች ደሴት ለኢራን እጅግ ስትራቴጂካዊ ስፍራ ስትሆን፡
ኢራን ለውጭ ገበያ ከምትልከው ድፍድፍ ነዳጅ 90 በመቶው የሚተላለፈው በዚህች ደሴት በኩል ነው።
አሜሪካ ይህንን ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ ያለውን የኢራን ወታደራዊ አቅም የማዳከም ቅድመ ዝግጅት እንደምታደርግ ተጠቁሟል።
የኢራን መከላከያ ምክር ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ በባሕር ዳርቻዎች ወይም ደሴቶች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ፣ በመላው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና መተላለፊያ መንገዶች ላይ “ተንሳፋፊ ፈንጂዎችን” ጨምሮ የተለያዩ የባሕር ውስጥ ፈንጂዎች ይዘራሉ ብሏል።
ምክር ቤቱ በ1980ዎቹ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ፣ በወቅቱ ከ100 በላይ የባሕር ፈንጂ አምካኝ መርከቦች ጥቂት ፈንጂዎችን ማስወገድ ተስኗቸው እንደነበር ጠቅሶ፤ አሁንም የሚወሰደው እርምጃ የከፋ መዘዝ እንደሚኖረው አስጠንቅቋል።
ለሚፈጠረው ቀውስና ለረጅም ጊዜ ለሚዘጋው የባሕር መንገድ ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስዱት “አጥቂዎቹ” (አሜሪካ) መሆናቸውን ገልጿል።
ኢራን አክላም እንደገለጸችው፣ “ጠብ ጫሪ ያልሆኑ አገራት” በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በሰላም ማለፍ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ “ከኢራን ጋር መቀናጀትና መተባበር” ሲችሉ ብቻ እንደሆነ አሳስባለች።//
ኢራን በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ የባሕር ፈንጂ እንደምትቀብር አስታወቀች

