“ኬላ” ከተሰኘው የአሐዱ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተቋማቸው በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፎ እንዳደረገ ያምናል ወይ ? ተብለው ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ዳንኤል ተቋማቸው አሁን ላይ የምርመራው ስራ ሳይጠናቀቅ ሙሉ መደምደሚያ ላይ ላለመድረስ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
እስካሁን በተደረገው ምርመራ በምዕራብ ትግራይ የተወሰኑ የኤርትራ ወታደሮች/የኤርትራ ወታደር ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች/በአካባቢው የተመለከቷቸው ሰዎች የኤርትራ ወታደሮች ናቸው ብለው የገለጿቸው ሰዎች መኖራቸውን እንዳረጋገጡላቸው አሳውቀዋል።
አምንነስቲ ባቀረበው የአክሱም ሪፖርት ጉዳይም ፤ ኢሰመኮ እስካሁን ባደረገው ክትትል በአክሱም በተፈፀመው ክስተት የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች መሰብሰባቸውን ዶ/ር ዳንኤል ገልፀዋል።
ነገር ግን የስፋቱን መጠን፣ የተሳተፉት ሰዎች ብዛትና መጠን፣ የደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት መጠን፣ የሰብዓዊ ጥሰቱ ምንነት እና አይነት ፣ የኤርትራ ወታደሮች የተሳትፎ መጠን፣ ቁጥራቸው ስንት ነው የሚለውን ኢሰመኮ ምርመራውን ስላላጠናቀቀ ዝርዝር ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል።
ኢሰመኮ እያደረገ ባለው የምርመራና የክትትል ስራ ቦታው ላይ ተገኝቶ ሳያጣራና ሳያረጋግጥ መደምደሚያ ላይ መድረስ ስለሌለበት አሁንም በምርመራ ስራው መቀጠሉን ገልጾ ፤ ኮሚሽኑ የሚደርስበትን ግኝት ለህዝብ እንደሚያሳውቅ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል።