ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተሳተፉበት የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ኢትዮጵያዊቷ አክቲቪስት የትነበርሽ ንጉሴ ተጋብዛለች። የትነበርሽ በዘንድሮው ጉባኤ የተጋበዘችው በማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ከተባሉ 30 ዓለም አቀፍ መሪዎች አንዷ ሆና በመመረጧ ነው።
የዓለም ግዙፍ ኩባንያዎች ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት እንዲሰጡ የሚወተውት እና “ችሎታን ዋጋ” እንስጥ የተሰኘ ዘመቻ በዛሬው ዕለት በስዊትዘርላንድ የዳቮስ ከተማ ይጀመራል። በዘመቻው ከ100 በላይ ግዙፍ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ። የ36 አመቷ ኢትዮጵያዊት የሰብዓዊ መብት ጠበቃ እና አራማጅ የትነበርሽ ንጉሴ ጉዳዩን በኃላፊነት ይዘው ከሚሰሩ መካከል አንዷ ነች።
የትነበርሽ ዘመቻው “ችሎታችንን እንጂ አካል ጉዳታችንን አትዩ” የሚል መልዕክት የማስተላለፍ ውጥን እንዳለው ለDW ተናግራለች። ኢትዮጵያዊቱ አራማጅ በዘንድሮው ጉባኤ የተጋበዘችው በማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ከተባሉ 30 ዓለም አቀፍ መሪዎች አንዷ በመመረጧ ነው።