በእስራኤል በጉብኝት ላይ የሚገኙ ከኢትዮጵያ የተጓዙ ጋዜጠኞች የእስራኤል ፖርላማ ወይም ኬኒሴትን በመጎብኘት ከሁለት ቤተእስራኤላውያን ሴት የፖርላማ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የእስራኤል ፖርላማ አፈጉባኤ ሚስተር አሚር ኦሃን የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በመጀመሪያ የእስራኤል ፖርላማ አባል ኢትዮ ትውልደ እስራኤላዊ ከሆኑት ከዶ/ር ፀጋ መላኩ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ፅጋ ከአርባ ዓመታት በፊት በኦፕሬሽን ሙሴ ወደ እስራኤል ከተጓዙ ቤተ እስራኤላውያን መሀከል አንዷ ሲሆኑ እስራኤል ከገቡ በኋላ በጋዜጠኝነትና በሕግ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ተምረው የመጀመሪያዋ ሴት የአማርኛ ጋዜጠኛ በመሆን እስከ ዳይሬክተርነት በደረሰ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ማገልገላቸውን ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በጋዜጠኞች የሙያ ስነምግባር ፖናል ላይ በዳኝነት የሰሩት ዶ/ር ፀጋ በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ፖርላማ ውስጥ ካሉት ሶስት ቤተእስራኤላውያን ውስጥ አንዷ ሆነው ለቤተ እስራኤላውያንና ሌሎች ማህበረሰቦች መብትና ጥቅም መከበር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስራኤል ላይ ከሁለት ዓመት በፊት በሃማስ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ ዙሪያ የተባበሩት መንግስትታት ድርጅት በጠራው ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከእስራኤል ጎን በመቆሙ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር ፀጋ በኢትዮጵያና በእስራኤል ህዝቦች መሀከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
የእስራኤል ፖርላማ አባልና የቤተ እስራኤላውያን ማህበረሰቦች ኢሚግሬሽንና ኢንተግሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ሌላኛዋ ቤተ እስራኤላዊት ፓኒያ ታማኖ ሽታ በበኩላቸው ወደ እስራኤል የሚገቡ ቤተ እስራኤላውንን በትምህርትና በኢኮኖሚ ዘርፎች ለመደገፍ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው በተለይም የትምህርት ዕድል ካላገኙ ሀገራት የሚመጡ ቤተ እስራኤላውያንን በትምህርትና በጤና ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ከኢትዮ ቤተ እስራኤላውያን ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በእስራኤል ያሉ ቤተ እስራኤላውያን ቁጥር 175 ሺ መድረሱን ያወሱት ሚኒስትሯ ከዚህ ውስጥ 83 ሺ ያህሉ እስራኤል ውስጥ የተወለዱ በመሆናቸው ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከውይይቱ ቀደም ብሎ ስለ እስራኤል መንግስት አመሰራረት፤ የፖርላማ አወቃቀርና የምርጫ ስርዓት እንዲሁም ስለ ፖርላማው የስብሰባ ሂደት ገለፃ ተሰጥቷል፡፡

